በመስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመው ደኢሕዴን – ብሩክ አብዱ


ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል ድርጅቶች አንዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን ሲያስተዳድር 26 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

ከ20 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የተዋቀሩ የብሔር ፓርቲዎች ውህድ ሆኖ የተዋቀረው ንቅናቄ፣ ከስምንት ወራት በፊት በኢሕአዴግ ውስጥ የተደረገውን የአመራር ለውጥ ተከትሎ በአዳዲስ አመራሮች የተዋቀረ ሲሆን፣ አሁን በፓርቲው ውስጥ ያሉ አመራሮች ወጣቶችና ለአዳዲስ ሐሳቦች ቅን ናቸው ሲሉ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ይሁንና በፓርቲው ውስጥ በአባልነት የቆዩ ቢሆኑም፣ በከፍተኛ የአመራርነት ሥፍራ ያላቸው ልምድ አነስተኛ በመሆኑ ለከባድ ፈተናዎች ተጋልጠዋል የሚሉ አልጠፉም፡፡

ያም ሆነ ይህ በደቡብ ክልል በመንግሥትም ሆነ በክልሉ ገዥ ፓርቲ ውስጥ ከላይ እስከ ታች አመራሮችን መቀየር ለፓርቲውም ሆነ ለክልሉ መንግሥት በስፋት በክልሉ ለሚነሱ ጥያቄዎች ማስተንፈሻ ይሆን ዘንድ፣ የታለመ ታክቲካዊ አካሄድ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ በዚህም በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ያሉ ነባር አመራሮች ከሕዝቡ ፍላጎት በመነሳት የአመራር ለውጥ መደረጉን ፓርቲው የገለጸ ሲሆን፣ በዚህም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት አንድ ዕርምጃ መራመዳቸውን የፓርቲውና የክልሉ አመራሮች ይናገራሉ፡፡
ከዚህ መሳ ለመሳ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎችን እንደገና በማደራጀት የልማትና የአገልግሎት ማዕከላት ተደራሽነትን ለማስፈን፣ ሦስት አዳዲስ ዞኖችና 44 አዳዲስ ወረዳዎች ቢደራጁም በክልሉ ያሉ ጥያቄዎች ለገዥው ፓርቲ ፈተና መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡

ከእነዚህ ፈተናዎች በቀዳሚነት የሚነሳው በክልሉ ካሉ ዞኖች ከሰባት በላይ የሚሆኑት እያቀረቡት ያለው የክልልነት ጥያቄ ነው፡፡ የሲዳማ ዞን ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበው የክልልነት ጥያቄ መሠረት ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ፣ በተለያዩ ዞኖች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ የተነሱ ሲሆን፣ የዞኖች ምክር ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሰጡት የድጋፍ ድምፅ ለክልል ምክር ቤት የክልል እንሁን ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበርልን የሚሉ ጥያቄዎች ተደራርበው ጎርፈዋል፡፡
የክልሉ መንግሥትም ሆነ ደኢሕዴግ የእነዚህን ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊነት እንደሚያከብሩ በተደጋጋሚ የገለጹ ቢሆንም፣ ለአፈጻጸምና ለአስተዳዳር አያመችምና ጥናት ተጠንቶ መፍትሔ ይቀመጥ በማለት ተስማምተዋል፡፡ ይሁንና ይኼ ስምምነት ሁልጊዜ ሲከበር አይታይም፡፡ ወደኋላም የሚመለሰበት ወቅት አልጠፋም፡፡

ለዚህ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችለው ከየካቲት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በሐዋሳ ሲደረግ በነበረው የንቅናቄው ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተፈጠረው ግርግርና በአመራሮች ላይ የተፈጸመው ድብደባ ነው፡፡ ስብሰባው በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በዘጠኝ ቡድኖች ተከፋፍለው ስብሰባ ሲያደርጉ ከነበሩ አመራሮች መሀል፣ የሲዳማ ዞን አመራሮች የዞኑ የክልልነት ጥያቄ ተንኳስሶ ቀርቧል በሚል ምክንያት ስብሰባውን ጥለው በመውጣት እንዲበተን ያደረጉ ሲሆን፣ በተወሰኑ አመራሮች ላይም ድብደባ ተፈጽሟል፡፡ ድብደባውን የፈጸሙት ተደራጅተው ወደ ስብሰባ አዳራሽ የገቡ ቡድኖች መኖራቸውን ንቅናቄው በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡

ለውይይት የቀረበውን ሰነድ አስመልክቶ የተዛቡ መረጃዎች ለኅብረተሰቡ በመተላለፋቸው የተፈጠረ ችግር መሆኑ እንደታወቀ የገለጸው ደኢሕዴን፣ ‹‹ሰነዱ በድርጅቱ ባህል መሠረት ዝርዝር ጉዳዮች የተፈተሹበትና ችግሮችን አንጥሮ ያወጣ ሲሆን፣ በሰነዱ ላይ የተመላከተው ዝርዝር ግምገማ ያልጣማቸው ግለሰቦች የሚፈጥሩት ውዥንብር እንደሆነ ደኢሕዴን ማስገንዘብ ይወዳል፤›› ሲልም አስታውቋል፡፡
ይኼ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ክፍፍልና ‹‹የሐሳብና የተግባር አንድነት›› ለማምጣት እየተጋሁ ነው ለሚለው ድርጅት እምብዛም ፈቅ ያላለ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ሲሉ የሚተቹ አሉ፡፡ በዚህም ውሳኔዎች በእኩል ተቀባይነት አግኝተው እንደማይተገበሩ ታይቷል ሲሉም ይተቻሉ፡፡ የዚህ አንደኛው መገለጫም በጋራ ጥናት ለማድረግ ተወስኖ ሲያበቃ፣ ለጋራ ውሳኔ ዘብ መቆም ያለመቻላቸው ያመጣው አጠያያቂነት ነው ይላሉ፡፡

ሆኖም ደኢሕዴን የክልልነት ጥያቄዎችን የሚያጠናው መረጃ ለመሰብሰብ፣ ለመተንተንና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማቅረብና የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ ለዚህም የተቋቋመው አጥኚ ቡድን በአምስት ዋነኛ ነጥቦች ላይ ያተኩራል፡፡ እነዚህም፣ ‹‹የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት አመራርነት ሒደት ምን እንደሚመስልና እንዴትና ለምን እንተደመሠረተ መዳሰስ፣ የክልሉ ሕዝቦች አብረው በቆዩባቸው ዓመታት ያገኟቸውን ትሩፋቶችና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች መዳሰስ፣ በክልሉ ሕዝብ ዘንድ እየተነሱ ያሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎች መንስዔዎች ምን እንደሆኑ መዳሰስ፣ እንደኛ ያሉ ብዝኃነት ባለባቸው የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች ተመሳሳይነት ያላቸው ጥያቄዎች በሚነሱበት ጊዜ እንዴት እንደሚፈቱ ያለውን ተሞክሮ መዳሰስና በክልሉ ለተነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች የመፍትሔ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ፤›› ናቸው፡፡
የጥናቱን ምንነት አስመልክተው ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የደኢሕዴንና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር) ጥያቄዎቹ በደኢሕዴን ብቻ የሚመለሱ ሳይሆኑ፣ ‹‹እንደ መሪ ፓርቲ ግዴታም ስላለበት ነው ይኼንን ጥናት የሚያደርገው፤›› በማለት፣ ጥናቱ ሕገ መንግሥታዊ መንገዶችን ለመጣስ የሚደረግ እንዳልሆነም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከሕዝቦች ጋር ውይይት ተደርጎ ደመነፍሳዊ የሆነ መለያየት እንዳይሆን ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ስለሚያምን ነው ደኢሕዴን ጥናት የሚያደርገው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን በሐዋሳ ስብሰባ ወቅት በነበረው ግርግር ከድርጅቱ አመራሮች ሳይቀር ‹‹ደኢሕዴን አይወክለንም›› የሚሉ ድምፆች ሲሰሙ እንደነበር፣ በስብሰባው የተሳተፉ አንድ አመራር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እሳቸው ክልል ከመሆን ይልቅ ሕጉ ቀበሌ መሆንን በመጠየቅ እንደሚያደርግና እንደሚከብደው፣ የክልልነት ጥያቄ የሚታየው ግን በመቅደምና በመዘግየት መጠየቅን መሠረት አድርጎ ሳይሆን፣ የጥያቄዎቹን አግባብነት በማየት ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

አደረጃጀት በተወሰኑ ቦታዎች የቴክኒክ ጥያቄ፣ በተወሰኑ ቦታዎች ደግሞ በፌዴራል መንግሥት ውስጥ በቀጥታ ድምፅ ይኑረኝ፣ የራሴ ሕግ አውጪ ይኑረኝ ከሚሉ ትኩረት የማግኘት ፍላጎቶች የሚመነጩ እንደሆነ የገለጹት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ ‹‹ደኢሕዴን እያጠና ያለው ራሱ የሚመራቸውን ክልሎች ለመመሥረት ነው፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ይኼም የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ሆነው ከአንድ በላይ ክልሎችን የሚመሩ ድርጅቶች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ተመሳሳይ ተሞክሮ መተግበር እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን ደቡብ በሚል ስም መጠራትን እየሸሹና የክልሉንም ሰንደቅ ዓላማ እያወረዱ የተለያዩ ዓርማዎችን የሚሰቅሉ ቡድኖች ባሉበት፣ እንዲሁም በንቅናቄው አመራሮች ጭምር በተለያዩ ሥፍራዎች በሚደረጉ ሠልፎች ደኢሕዴን አይወክለንም የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ፣ ይኼንን ዕውን ማድረግ እንደሚነገረው ቀላል ላይሆን ይችላል የሚሉ አሉ፡፡

‹‹አመራር ሆኖ ደኢሕዴን አይወክለኝም የሚል ካለ እዚህ ምን ይሠራል?›› ሲሉ ጌታሁን (ዶ/ር) ይጠይቃሉ፡፡ በተለያዩ የክልሉ ዞኖችም የሚቋቋሙ ፓርቲዎች እየበዙ የመጡ በመሆናቸው ለደኢሕዴን ሕልውናም ከባድ ፈተናዎች ሊሆኑበት እንደሚችሉ ቢነገርም፣ ጌታሁን (ዶ/ር) ግን ፓርቲዎቹ መመሥረታቸው የሰፋውን የፖለቲካ ምኅዳር እንደሚያሳይ በማውሳት፣ ‹‹ደኢሕዴን የሚፈልገው ተወዳድሮ ሕዝቡ መርጦት መምራት ነው እንጂ ብቸኛ ሆኖ በበላይነት መቆጣጠር አይደለም፤›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

ወጣቱና የተማረው ኃይልም ራሳቸውን በፓርቲ ባደራጁ ቡድኖች መካከል በመገኘት እንደሚከታተልና እንደሚጠይቅ በመጥቀስ፣ ሰዎች ምርጫ ተከልክለው ሳይሆን መርጠው መውጣት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑም ያስረዳሉ፡፡

‹‹ነገር ግን ደኢሕዴን በመዳከሙ ነው እነዚህ ፓርቲዎች እየበዙ የመጡት፣ በክልሉም ችግሮች እየታዩ ያሉት ማለት አይደለም፤›› በማለትም ይከራከራሉ፡፡

አዲሱ አመራር ከመጣ ወዲህ በክልሉ በሁሉም ቦታዎች የነበሩ ብጥብጦች ረግበው አሁን በውስን አካባቢዎች ብቻ መታየታቸውን በመጥቀስ፣ እንዲያውም በአንፃሩ ከሌሎች ክልሎች የተረጋጋ ክልል ደቡብ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን በየአካባቢው ያሉ ችግሮች የተጠረቃቀሙና የደኢሕዴግ ብቻ አለመሆናቸውን በማውሳት፣ ‹‹እየተከፈለ ያለው የተጠራቀመ ዋጋ ነው፤›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡ ‹‹ችግሮች ቀንሰዋል እንጂ አልጨመሩም፤›› ሲሉም ይሟገታሉ፡፡

ነገር ግን በፓርቲው ጉባዔ ጥናት ተደርጎ የአደረጃጀት ጥያቄዎች እንዲፈቱ የተወሰነና የጋራ አቋም የተያዘበት ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ በየወቅቱ በሚደረጉ የካድሬ ስብሰባዎች ላይ እንደ አዲስ እየተነሳ ውይይት ይደረግበታል፡፡ ይኼም ተቃርኖ የሚታይበት አካሄድ እንደሆነም ይተቻል፡፡ ነገር ግን የፓርቲው አመራሮች የሕዝብ ተወካዮችም በመሆናቸው ጭምር ባገኙት መድረክ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው አግባብ ነው የሚሉት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ መድረኮቹ በየጊዜው የማይገኙ በመሆናቸው ጥያቄዎቹ መነሳታቸው እምብዛም ችግር ፈጣሪ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በንቅናቄው በጎራ ተከፍለው ያሉ አመራሮች ጉዳይ የድርጅቱን መዳከም እንደሚያሳይ፣ ከጥያቄዎች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ አመራሮች የየራሳቸውን ዞኖች ጥያቄዎች የሚደግፉ የሌሎች ዞኖችን አመራሮች በማሠለፍ፣ የእከክልኝ ልከክልህ ጨዋታም መኖሩ አሳሳቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡

አመራሩ ባለበት መከፋፈልም ድርጅቱ ካሁን ቀደም ጉልህ ሚና ሳይኖረው በኢሕአዴግ ውስጥ ከቆየበት ጊዜ በላይ፣ አሁን ኢሕአዴግ ሲነሳ የማይታወስ አባል ድርጅት እየሆነ የመጣ ንቅናቄ እንደሆነ በመግለጽ፣ በድርጅቱ ውስጥ ያለው ክፍፍል በህልውናው ላይ የተደቀነ አደጋን ያመላክታል የሚሉ ተቺዎች ተበራክተዋል፡፡

በሌላ በኩል በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተጠፍንጎ የቆየ ድርጅት በለውጥ ወቅት ልቀቅ የሚል ሁኔታ ቢያጋጥመውም፣ ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በሰፊው ምኅዳር ውስጥ ማለፉ የግዴታ ነው የሚሉም አሉ፡፡

(ሪፖርተር)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.