ለኦዴፓዎች በዘላቂነት የሚቀርቧቸው ህወሃቶች እንጅ አዴፓዎች ሊሆኑ አይችሉም!!!   (ከህዝባዊ ሰልፉ)

ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የህወሃት ሰዎችን አንባገነንነት፣ ያለአግባብ ተጠቃሚነት አድሏዊ አሰራር እንዲሁም የበላይነት ዝንባሌ ፊት ለፊት ሲጋፈጡ የነበሩት አነሰም አደገ የብአዴን (አዴፓ) ሰዎች እንደነበሩ ይነገራል። በአንፃሩ የደኢህዴን ሰዎች የተባሉትንና የታዘዙትን ከመፈፀም ያለፈ ሚና አልነበራቸውም የሚል ስሞታ የሚቀርብባቸው ናቸው። የኦዴፓ (ኦህዴድ) ሰዎችም ቢሆኑ በራሳቸው የውስጥ ችግር ተተብትበው ስለነበረ የህወሓት ሰዎችን ሴራ በመታገል ረገድ ጉልህ ሚና ነበራቸው ለማለት አይቻልም በሚል የሚገልፁ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ የኦዴፓ ሰዎች አንገታቸውን ቀና ማድረግ የጀመሩት አቶ ሙክታር ከድርንና ሌሎች ቆየት ያሉ አመራሮችን በዘመቻና በተደራጀ መንገድ አስወግደው እነአቶ ለማ መገርሳ ድርጅቱን መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው ማለት ይቻላል።

እነአቶ ለማም ቢሆኑ ድርጅቱን ለመምራት ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ሲያልሙ፣ ሲያስቡ፣ ሲያውጠነጥኑና ሲያቅዱ የነበረው እንዴት አድርገን የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን እንቆጣጠርው በሚለው አብይ አጀንዳ ዙሪያ እንደነበር ከእንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ በመነሳት ለማወቅ ከባድ አይደለም። ይህን ለማድረግ ደግሞ የህወሓትን ሰዎች በሚገባ ማዳከም እንዳለባቸው መገንዘባቸው አልቀረም። በዚህም መሰረት በመሰረታዊ አቋሞቻቸው ዙሪያ ጠንካራ የሆነ አንድነት ሊኖራቸው እንደማይችል ቢረዱም እንኳ ቢያንስ የህወሃት ሰዎችን አከርካሪ ለመስበር ይረዱናል ከሚሏቸው የአዴፓ ሰዎች ጋ ግንባር ለመፍጠር የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ተሳክቶላቸዋል።

በአቶ ለማ የሚመሩት የኦዴፓ ሰዎች አላማቸውን ለማሳካት ይችሉ ዘንድ ያግዙናል የሏቸውን የአዴፓ አመራሮች ለማማለል ኢትዮጵያዊነት የሚለውን መሪ ቃል (Catch Phrase) መጠቀም እንዳለባቸው ሁሉ ቀደም ብለው ተረድተዋል። ለዚህም ነው የኦዴፓ ሰዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር የሚል አጀንዳ ቀርፀው ባህርዳር በመጓዝ “ኢትዮጵያ ሱሴ ነች፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ህይወት አይታሰብም” የሚል ዲስኩር በማሰማት በአማራውም ይሁን በሌሎች ብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሰርስረው መግባት የቻሉት።

ከዚህ ጎን ለጎንም ዶ/ር አብይና አቶ ለማ ስብዕናቸውን ለመገንባት የቻሉትን ሁሉ አደረጉ። ከማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ጀምሮ እነሱ እስከሚቆጣጠሯቸው እንደ ኦ ቢ ኤን (OBN) ያሉ የመገናኛ ብዙሃንን በሚገባ ተጠቀሙባቸው። አርቲስቶችም ዶ/ር አብይንና አቶ ለማን የሚያወድሱ ነጠላ ዜማዎች እንዲለቁ ተደረገ። እረ ስንቱ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች “ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፤ ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ አኔ አላማረኝም” የሚለውን የጥላሁን ገሠሠን ሙዚቃ እያንጎራጎሩ ኧረ ቀስ በሉ ሲሉ ይደመጡ ጀመር።

ወጣም ወረደ የኦዴፓ ሰዎች የሚያደርጉትን ሁሉ አድርገው እንዳሰቡትና እንዳቀዱት የአዴፓን ሰዎችም ወሳኝ የሆነ ድጋፍ በማግኘት የፌዴራል መንግስቱን ተቆጣጠሩት። ከዚህ በኋላ ያደረጉትን ሁሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታዝቦታል። ሲጀምሩ አገር የመምራቱን ሂደት ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋ አመሳሰሉትና ዶ/ር አብይን የፊት አጥቂ አደረጉት። አቶ ለማም የመሃል ሜዳ አከፋፋይ በመሆን የራሱን ቦታ አደላደለ። ሌሎቹ የኦዴፓ ሰዎችም የክንፍ፣ የተከላካይና የበረኝነት ቦታን ተረከቡ። እነጅዋር ደግሞ ድሮም ሲያደርጉት እንደነበረው የአሰልጣኝነቱን ቦታ ተቆጣጠሩት። ቄሮ የተባለው ሃይል በበኩሉ በደጋፊነት ተፈርጆ ሆይ ሆይ እያለ የሚፈልገውን ነገር እንዲያስፈፅም እድሉ ተመቻቸለት። ይህ ቄሮ ተብሎ የሚታወቅ ሃይል በደጋፊነት ሚናው ሲፈልግ በጩኸት ሲያሻው ደግሞ በገጀራና በቆመጥ እያሳፈራራ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ መጠየቅና ማስፈፀም ይችል ዘንድ የህዝብ ጥያቄ በሚል ጋቢ እንዲጀቦን ተደረገ። የአዴፓ ሰዎች በበኩላቸው በዶ/ር አብይና በአቶ ለማ ዲስኩሮች እንዲማልሉ ተደርገው የአጃቢነት ሚና ተሰጣቸው። በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ የኦዴፓ ሰዎች የፌዴራል መንግስቱን መሪነት የተቆናጠጡት።

ኦዴፓዎች የፌደራል መንግስቱን መሪነት እጃቸው ውስጥ ካስገቡ በኋላ ሳይውሉ ሳያድሩ ልክ እንደህወሓት ሰዎች ሁሉ ምናልባትም እርቃኑን በወጣ መንገድ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች ሁሉ እጃቸውን ማስረዘም ጀመሩ። በዚህም መሰረት የመከላከያ ዋና ዋና ቦታወችን፣ ሌሎች የፌዴራል መንግስት ቁልፍ የሆኑ ተቋማትን፣ የአዲስ አበባን አጠቃላይ መዋቅር በጃቸው ውስጥ ለማስገባት ሰፊ ስራ ሰሩ።  በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ የውጭ ግንኙነት ስራዎች ሁሉ ተሌቪዥን ላይ የምናያቸው ፊቶች የኦዴፓዎቹን ዶ/ር አብይ፣ ዶ/ር ወርቅነህና አቶ ሽመልስ አብዲሳን ሆኗል። ይህ የሚያስታውሰን ደግሞ የህወሃቶቹን አቶ መለስን አቶ ስዩምንና አቶ ገረንስኤን ነው። በንዲህ አይነት ሁኔታዎች ስንደመም ደግም የኦዴፓ/ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ ቀጢሳ “በግልፅ አንነግራችሁም እንጅ ኦሮሞን የሚጠቅም ብዙ ስራ እየሰራን ነው፤ በዚህ በኩል ልታምኑን ይገባል በሚል ለኦሮሞ አትሌቶችና አርቲስቶች ተናገሩ” የሚል ዜና ሰማን።  ከዚህ ይባስ ብለው ደግሞ የአዲስ አበባንና የኦሮሚያን የወሰን ጉዳይ እልባት እንዲሰጥ የኦዴፓ ሰዎችና አጫፋሪዎቻቸው የበዙበት ኮሚቴ አቋቋሙ።

በነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች  ለውጡ የሃገሪቱን ህዝቦች በእኩልነት የሚያይ ሳይሆን ስልጣንንና ተጠቃሚነትን ከህወሃት ሰዎች እጅ አውጥቶ ወደ ኦዴፓ ሰዎች ለማሸጋገር የተደረግ እርምጃ እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎች እየበረከቱ መጡ። እንዲያውም ዶ/ር አብይና አቶ ለማን ከእግዚአብሄር የተላኩ መላዕክታን አድርጎ ሲደግፋቸው የነብረው በርካታው ሃይል ክህደት እንደተፈፀመበት በመቁጠር ቅሬታውን በመግለፅና ተቃውሞውን በማሰማት ላይ ይገኛል።

ይህ የኦዴፓ ሰዎች ሁሉንም የማግበስበስና የኔ ነው የማለት ብሎም የበላይ የመሆን ዝንባሌ የአዴፓ ሰዎችንም ቢሆን ያስደሰተ አይመስልም። ይህ መሆኑን የምንረዳው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ያሉ የአዴፓ ሰዎች በአደባባይ ሳይቀር በኦዴፓ ሰዎች አሰራር ላይ ቅሬታ እያቀረቡ እንደሆነ እያየን በመሆኑ ነው። በነገራችን ላይ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ችግር ይህ እየተፈጠረ ያለ ቅሬታ ብቻ አይደለም። በመሰረታዊ አቋሞቻቸው ዙሪያም ቢሆን ጠንካራ የሆነ አንድነት ያላቸው አይመስሉም። የመሰረታዊ አቋሞች ጉዳይ ከተነሳ የኦዴፓ ሰዎች አቋም የሚቀርበው ለህወሃት ሰዎች እንጅ ለአዴፓ ሰዎች አይመስልም። በዚህ ዙሪያ የተወሰኑ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ሁኔታዎን የበለጠ ግልፅ ማድረግ ይቻላል።

የመጀመሪያው ማሳያ በህገመንግስቱ ላይ የኦዴፓና የህወሃት ስዎች ተመሳሳይ አቋም ያላቸው መሆኑ ነው። ሁለቱም ቡድኖች ህገመንግስቱ ዘላቂ ጥቅማችን የሚያረጋግጥልን የቃል ኪዳን ሰነድ ነው ብለው ያምናሉ። በአዴፓ ሰዎች በኩል ግን ህገመንግስቱ የአማራን ህዝብ ጥቅም አያስከብርም የሚል ዝንባሌ እንዳላቸው የሚያሳዩ ምልክቶችን እያየን ነው።

ፌዴራሊዝምን በተመለከተም ህወሓትም ሆነ ኦዴፓ ያላቸው አቋም የማይናወጥ ነው። ሁለቱም ቡድኖች ያለፌዴራሊዝም ስርዓቱ መኖር እንደማይችሉ በየበኩላቸው ከሚያወጧቸው መግለጫወች መረዳት ይቻላል። ወደ አዴፓዎች ስንመጣ ግን ዝንባሌያቸው አህዳዊነት ወደሚለው ያደላ የሚመስልበት ሁኔታ እንዳለ ከሚያርምዱት አቋም መረዳት ይቻላል።

ሌላው ጉዳይ የህወሓትም ሆነ የኦዴፓ ሰዎች የአማራ ገዥ መደብ እንዲያውም አንዳንዶቹ የአማራ ህዝብ በደል አድርሶብናል ብለው ያምናሉ። ይህን በተመለከተ ሁለቱም ቡድኖች በአማራ ነገስታት በተለይም በአፄ ሚኒሊክ ላይ የከረረ ጥላቻ እንዳላቸው የሚገልፁበት አጋጣሚ ቀላል አደለም። በአንፃሩ የአዴፓ ሰዎች አፄ ቴዎድሮስና አፄ ሚኒሊክ የነፃነትና የስልጣኔ ቀንዲል ናቸው በሚል ይገልጿቸዋል።

በተጨማሪም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የህወሃትና የኦዴፓ ሰዎች ከኢህአዴግ በፊት የነበሩት ስርዓቶች የአማራን ጥቅም ለማስከበር የቆሙ ናቸው ብለው ያምናሉ። የአዴፓ ሰዎች በበኩላቸው ያለፉት ስርዓቶች ከስም በዘለለ የአማራን መሰረታዊ ጥቅሞች የሚያስክብሩ አልነበሩም ብለው ይከራከራሉ። ከዚህ ጋ ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ የሀወሓትና የኦዴፓ የትግል ማጠንጠኛ ከብሄራዊ ጭቆና ጋ የተያያዘ ሲሆን የአዴፓዎች ግን በመሰረቱ መደባዊ ባህሪ የሚንፀባረቅበት መሆኑ ነው።

በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይም ቢሆን ህወሃቶች እስከአሁን ግልፅ የሆነ አቋማቸውን አላሳወቁም።  እንዲያውም ህወሃቶች ይህን የአዲስ አበባ ጉዳይ በአዴፓና በኦዴፓ መካከል ያለው መቃቃር እንዲሰፋ ለማድረግ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። አንዳንድ ፍንጮች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው። ለምሳሌ የተለያዩ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባን ሲጠሯት “ፊንፊኔ” እያሉ እንደሆነ ስንሰማ ለጥርጣሪያችን መነሻ ነው።

ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ሁኔታዎች መገንዘብ የሚቻለው ትልቅ ቁም ነገር ጠንካራ ግንኙነትና ትስስር ካለም ሊኖር የሚችለው በኦዴፓና በወሓት ሰዎች መካከል እንጅ በኦዴፓዎችና በአዴፓዎች መካከል አይመስልም።  እስካሁን ድረስ በኦዴፓዎችና በአዴፓዎች መካካል ተመስርቶ የነበረው ግንኙነትም ኦዴፓ የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን ከህወሃቶች ለመንጠቅ የተጠቀመበት የሴራ ፖለቲካ እንጅ በመርህ ላይ የተመሰረተና ተቋማዊ ነው ማለት እንደማይቻል አሁን እየታዩ ካሉ ልዩነቶች ለመረዳት ከባድ አይሆንም። በህወሃትና በኦዴፓ ደጋፊዎች መካከል ግንኙነት ለመፍጠር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴም የዚሁ አንድ አካል ነው።  በመሆኑም የኦዴፓ ሰዎች የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን በወሳኝነት ተቆጣጥረናል ብለው ባሰቡ ጊዜ መሰረታዊ አቋሞችቻቸውን ለማስፈፀም ይችሉ ዘንድ በለመዱት የሞኛሞኝ ብልጠት የተሞላበት የሴራ ፖለቲካቸው የአዴፓን ስዎች ገሸሽ አድርገው ከህወሃት ሰዎች ጋ ግንባር ለመፍጠር መሞከራቸው አይቀርም። ለዚህም ነው ለኦዴፓዎች በዘላቂነት የሚቀርቧቸው ህወሃቶች እንጅ አዴፓዎች ሊሆኑ አይችሉም ማለት የሚቻለው።

 

3 COMMENTS

 1. ለህዝባዊ ሰልፉ ከባድ መርዶ!!!

  አቶ ዮሐንስ ቧያለው በአዴፓ እና ኦዴፓም ሆነ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል:: ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታፍኖ የነበረ በመሆኑ የልዩነት ሐሳብ ቅራኔ ይመስላል፤ ግን ጤናማ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ በድሮ ኢህአዴግ ብዙ የታፈኑ ድምፆች ስለነበሩ ልዩነቶች አይንፀባረቁም፤ ሕዝቡም አልለመደውም፡፡ አሁን እነዚህ የዴሞክራሲ እና የሐሳብ ብዝኃነቶች ሲስተናገዱ ሕዝቡ ሊደናገጥ አይገባም፡፡ በእኛ እና ኦዴፓ መካከል ልዩነት የተፈጠረ መስሏቸው የሚቦርቁም አሉ፤ ለእነዚህ መርዷቸውን ንገሯቸው፡፡ እኛ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድል ብሩህ ለማድረግ እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡

  ከኦዴፓና አዴፓ የበለጠ ህውሀትን የሚያውቅ አይኖርም::

 2. 1. “ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት … ጠንካራ ግንኙነትና ትስስር ካለም ሊኖር የሚችለው በኦዴፓና በወሓት ሰዎች መካከል እንጅ በኦዴፓዎችና በአዴፓዎች መካከል አይመስልም።”

  2. “እስካሁን ድረስ በኦዴፓዎችና በአዴፓዎች መካካል ተመስርቶ የነበረው ግንኙነትም ኦዴፓ የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን ከህወሃቶች ለመንጠቅ የተጠቀመበት የሴራ ፖለቲካ እንጅ በመርህ ላይ የተመሰረተና ተቋማዊ ነው ማለት እንደማይቻል አሁን እየታዩ ካሉ ልዩነቶች ለመረዳት ከባድ አይሆንም።”
  Hey, in the first scenario, you might be right. Because the so called Amhara is anti both oppressed nations at least before some 30 years.

  In the second scenario, however, the coalition was made based on the request by your ANDM. The purpose was not aimed to overthrow TPLF but to block freedom of Oromo Nation. ANDM seems to anticipate real power was going to true sons of Oromo Nation while Qeerroo was to overthrow habesha government. Hence, according to ANDM’s calculation, the link between ANDM and OPDO was important to get time before it goes to the hand of true sons of Oromo Nation. It is clear most OPDO members are the mixed sons of habesha.
  the good thing is that Oromia’s freedom is inevitable. It is coming very soon. Enjoy!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.