የአዲስ አበባ ጉዳይ ለእነ ዐቢይ መንግስት የእግር ሳት ሆኗል- ጌታቸው ሽፈራው

“…በዚህ እርግጠኛ ነኝ!”
——
“የባለ አደራው ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት መግለጫ የማይሰጥባቸው ምክንያቶች!

የአዲስ አበባ ጉዳይ ለእነ ዐቢይ መንግስት የእግር ሳት ሆኗል። ብዙ ሴራ እየተጎነጎነበት ነው። የእግር ሳት ከመሆኑ የተነሳ “በፍቅር እንደመር” እያሉ “ወደ ግልፅ ጦርነት እንገባለን” አስብሏቸዋል። የእነ እስክንድር ጉዳይ እጅግ አስጨናቂ ሆኗል። አሁን እየታሰበ ያለው ጉዳዩን በሴራና በደባ ማለፍ ነው። እንደ ሕወሓት አዳራሽ መከልከል የባሰ እንደሚያሳጣቸው እያዩት ነው። ለአብነት ያህል ጠሚ ዐቢይ እስክንድርን ለማግኘት ቀጠሮ ይዞ ነበር። ነገር ግን የዛሬው ክልከላ እስክንድር ዐቢይን ለማግኘት እንዳይችል ያደርገዋል። በእርግጠኝነትም አዳራሽ እየተከለከለ ሊያገኘው አይደፍርም። ይህ ለእነ አብይ ፈተና ነው። እስክንድር ለአብይ እንደሚሽቆጠቆጥለት አብዛኛው ፖለቲከኛ፣ ጋዜጠኛ……… አይደለም።

በመሆኑም ማደናገሪያ መፈለግ አስፈለጋቸው። ሴራ መሸረብ አማራጭ የሌለው አማራጭ ሆነ። ከዛሬው ሴራዎች መካከል አንደኛው በ Seyoum Teshome በኩል የተለቀቀው ነው። ስዩም በየዋህነት ሰተት ብሎ ለሴራቸው ተጋላጭ ሆኗል። አዳራሽ ሲከለክሉ የሰነበቱት ሰዎች “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ወይም ፓርላማ አዳራሽ መግለጫ መስጠት ይችላል ብለው ቀለዱ። የቀልዱ አስቂኝነት ደግሞ መግለጫው የተከለከለው ለእስክንድር ደሕንነት ነው ተብሎ ነው ማለታቸው ነው። ይህ ቀልድ ብቻ አይደለም። ሴራ ነው። የባለ አደራ ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ወይንም በፓርላማው መግለጫ እንደማይሰጥ ያውቁታል።

1) የባለ አደራ ምክር ቤት አዲስ አበባን ሊውጧት ካሰፈሰፉት ስግብግቦች ለማዳን የተመሰረተ ምክር ቤት ነው። አዲስ አበባን ለማዳን እየሰራ አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ሆቴል ውስጥ መግለጫ ለመስጠት እሰጋለሁ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ወይንም ፓርላማው ጋር ሄዶ በግዞት መግለጫ ሊሰጥ አይችልም። አዲስ አበባን ነፃ ለማውጣት፣ አዲስ አበባን ሊቀራመቱ ካሰፈሰፉት ቡድኖች ፅ/ቤትና ቢሮ ተጠልሎ መግለጫ እንደማይሰጥ ያውቁታል። በተለይ በተለይ እስክንድርን በሚገባ ያውቁታል። እስክንድር ነጋ ማለት ከገዥዎቹ ጋር ምንም አይነት ቅርበት የማይፈልግ ሰው ነው። ራሱን ከገዥ የሚያርቅ የመርህ ሰው ነው። ለመርህ ዋጋ የሚከፍል እንጅ ነፃ ለማውጣት የቆመለት ከተማን አደባባይና ሆቴሎች ውስጥ መግለጫ መስጠት ፈርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በግዞት መግለጫ እንደማይሰጥ ጠንቅቀው ያውቁታል።

2) የዛሬው ስብሰባ የፀጥታ ስጋት አልነበረበትም። እነ እስክንድር ለሆቴል ኪራይ ከፍለዋል። ፖሊስ ወይ የደሕንነት ሰራተኛ ግን እስክንድርን “ደሕንነትህ ያሰጋኛል” ብሎ አልደወለለትም፣ አላናገረውም። የተደረገው የአፈና ስራ ነው። ፖሊስና የደሕንነት ሰራተኛ የሄደው ስጋት አለበት ወደተባለው እስክንድር ሳይሆን ወደራስ ሆቴል ነው። ወደ ሆቴሉ ሄደውም እንዳታስገቡ ነው ያሉት። ስለ እስክንድር ሳይሆን እስክንድር ስለሚሰጠው መግለጫ ነበር የተጨነቁት። ወደራስ ሆቴል እንዳይገባ ከመከልከል ውጭ ለእስክንድር ምንም አይነት ከለላ ወይ ጥበቃ አላደረጉለትም። ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ፖሊስ እንቅፋት ሲፈጥር የሆቴሉ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ተንከራትቷል። ከራስ ሆቴል ካሳንቺስ ፖሊስ መምርያ ሲንከራተት ፖሊስ “ደሕንነትህ ያሰጋኛል” ብሎ አልተከተለውም። አልጠበቀውም። የፖሊስ ብቸኛው ስራ ወደ ራስ ሆቴል እንዳይገቡ እንጅ እስክንድርን መጠበቅ አልነበረም። ፖሊስ ለእስክንድር ደሕንነት ተጨንቆ ሊጠብቀው ቀርቶ ወደ ራስ ሆቴል እንዳይገባ ሲከለክል የሚያሳይ ቪዲዮ አለ። አሥራት ሰርቶታል። ከራስ ሆቴል እንዳይገቡ ከተከለከሉ በኋላም ለፖሊስ የእስክንድር ደሕንነት ጉዳዩ አልነበረም። ሲጠብቀው አልነበረም። በእስክንድር ላይ የደሕንነት ስጋት ነበር ቢባል እንኳ ይህ ለፖሊስ ትኩረቱ አልነበረም።

3) እስክንድር የደሕንነት ስጋት ነበረበት ቢባል የፖሊስ ስራ የሚሆነው መጠበቅ እንጅ ስብሰባ መከልከል አልነበረም። አዲስ አበባን ነፃ ለማውጣት የሚሰራውና በነፃነት የሚንቀሳቀሰው እስክንድር ቀርቶ የመንግስት ባለስልጣናት በየ ሆቴሉ መግለጫ ሲሰጡ ነው የሚውሉት። አንድ መንግስት ደግሞ የዜጎችን ደሕንነት የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። የደሕንነት ስጋት ቢኖር ሆቴሉን መፈተሽና መጠበቅ እንጅ አላስገባም ማለት መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ስጋት ያለበት የመብት አራማጅ ደሕንነቱ ይጠበቃል እንጅ ቤተ መንግስት ሊከርም አይችልም። ይህን እንደ ምክንያት ማቅረብም ድንቁርና እንጅ ምንም ሊባል አይችልም። ነገሩ ግን ወዲህ ነው። ሴራ ነው።

4) እነ እስክንድር ለአዲስ አበባ ነፃነት እየሰሩ ፈርተው በግዞት፣ ገዥዎቹ ጋር ተደብቀው መግለጫ እንደማይሰጡ እሙን ነው። ሴራው እዚህ ጋር ነው። አዳራሽ በመከልከል የተወገዘው የዐቢይ መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፅ/ቤት ፈቀደ ሲባል ጭራሽ በአዲስ አበባ ላይ መስራቱን ቀርቶ ለአዲስ አበባ ለሚሰሩት ቀናኢ ነው ሊባል ነው። እነ እስክንድር ይጎዳሉ ብዬ ነው እንጅ አዲስ አበባማ ሱሴ ነው እንዳለ ለማስመሰል ነው። እነ እስክንድር አዲስ አበባን ነፃ ለማውጣት “እናንተ አዲስ አበባን ለመዋጥ የተዘጋጃችሁ ሰዎች ጋር ተሸጉጠን መግለጫ አንሰጥም” ሲሉ ደግሞ ለሕዝብ ሊያስመቱ ነው። “እኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሳይቀር ፈቀድንላቸው፣ እነሱ ግን አሻፈረኝ አሉ” ብለው በሕዝብ ለማስተቸት ነው።

5) እነ እስክንድር ነጋ በተባለው ተስማምተው በጠ/ሚ ፅ/ቤት ወይ ፓርላማ መግለጫ ቢሰጡ ለእነ አብይ ትልቅ ድል ነው። የመጀመርያው አዲስ አበባ ላይ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሊቃወሙ ቀርቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፅ/ቤት ፈቅደው “መግለጫ ስጡበት” እስከማለት መድረሳቸውን ታይቶ የማይታወቅ ለጋስነት ሊያደርጉት ነው። እነ እስክንድር “እሽ ባላችሁን መሰረት መግለጫውን እንሰጣለን” ቢሉ ደግሞ ሴራው ግቡን መታ ማለት ነው። የባለ አደራ ምክር ቤቱን ከአዲስ አበባ አራቁት ማለት ነው። ነፃ ለማውጣት ከሚሰራላት አዲስ አበባ ሸሽቶ ገዥዎቹ ጋር ተደብቆ መግለጫ ሰጠ ብለው ያስወሩበታል። ነፃ ለማውጣት ለሚሰራላት አዲስ አበባ ባዕድ ያደርጉታል። የጠ/ሚ ፅ/ቤት አዳራሽ ተስቶት “እሽ” ቢል የአዲስ አበባ ሆቴሎች ላይ፣ አደባባይ ላይ ስብሰባም ሰልፍም መጥራት የደሕንነት ችግር ያስከትላል የሚለው ያልተፃፈ የአፋኞች፣ የከልካዮች ሕግ ላይ ማሕተም አስመቱት ማለት ነው። የባለ አደራ ምክር ቤቱ ከጠቅላይ ሚ/ር ፅ/ቤትና ከፓርላማው ውጭ መግለጫ አይሰጥም የሚል ያልተፃፈ ሕግ አፀደቁ ማለት ነው። ከምንም በላይ ለከተማዋና ለሕዝብ የሚሰራው ምክር ቤት በሕዝብና በራሱ ከመተማመን ይልቅ አዲስ አበባን ለመዋጥ ያቆበቆበውን ቡድን መከታ አደረገ ማለት ነው። ትልቁ ሴራ ይህ ነው።

6) በእነ ዐብይ ሴራ መሰረት እነ እስክንድር ከተፈቀደላቸው ሁለት ቦታዎች በአንዱ መግለጫ ሰጡ እንበል። የአዲስ አበባ ሆቴሎችና አደባባዮች ግን ባልተፃፈ ሕግ ሰልፍና ስብሰባ የማይደረግባቸው ይሆናሉ። የጠ/ሚ ፅ/ቤትም ሆነ ፓርላማው ደግሞ ከአንድ ቀን ውጭ መግለጫ እንዲሰጡ ሊፈቅድላቸው አይችልም። ስለሆነም ባለ አደራ ምክር ቤቱ የአዲስ አበባ ሆቴሎችና አደባባዮች ላይ ስብሰባና ሰልፍ ማድረግ አይቻልም የሚለውን ያልተፃፈ ሕግ አፅድቆ አንድ ቀን ብቻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት መግለጫ ሰጥቶ ያቆማል ማለት ነው። ስራው ከዚህ ላይ አከተመ ማለት ነው። በአንድ መግለጫ ቀጩት ማለት ነው። እሱንም “እሽ መግለጫውን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት እንሰጣለን” ብለው ጎል ውስጥ ከገቡ በኋላ ሰበብ ፈልገው “አይቻልም” ካላሉ ነው። የአዲስ አበባ ሆቴሎችና አደባባዮች የደሕንነት ስጋት አለባቸው ስለተባለ ከአሁን በኋላ የማይታሰቡ ይሆናሉ ማለት ነው። የጠቅላይ ሚ/ር ፅ/ቤት ደግሞ ያልተፃፈውን ሕግ እስኪያፀድቅ ድረስ ለአንድ ቀን ፈቅዱ “ወግድ” ይላል። ያንም ከፈቀደ! የባለ አደራ ምክር ቤቱ ከአንድ መግለጫ በኋላ ከስራ ውጭ ሆነ ማለት ነው። ሴራው ይሄ ነው።

መንግስት አንድ ግዴታ አለበት። ዜጎችን መጠበቅ። አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን እነ ዐቢይ ለመሄድ እንፈራለት ያሉበት ወለጋም ቢሆን ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸው መከበር አለበት። መንግስት ደሕንነታቸውን የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። በሕዝብ እምነት እንዲያጡ ሴራ እየጎነጎነ አጀንዳ ማድረግ የመንግስት ተግባር አይደለም። ሽፍትነት ነው። ሽፍትነት ደግሞ መቅረት አለበት።

በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ባለ አደራ ምክር ቤቱ ለአዲስ አበባ እየታገለ ከአዲስ አበባ ሆቴሎችና አደባባዮች ሸሽቶ ከገዥዎች ተጠልሎ መግለጫ እሰጣለሁ ብሎ ራሱን አንቆ አይገድልም። በዚህ እርግጠኛ ነኝ!”

3 COMMENTS

  1. ያንተ ጀብደኝነት ዬትም አያደርሳችሁም:: ወይንም ጋዜጠኝነቱን ተዉና እንደ ሌባኖን የፈላንጅና የሄዝቦላ መንግስታት የጎበዝ አለቃ አዋቅሩ:: በዬትም ሀገር ህጋዊ መንግስት እያለ ባለአደራ መንግስት አይቋቋምም:: ዐቢይ አሕመድ አሁንም በለጣችሁ :: ይህ በአስቸኳይ ኦሮሞንና አማራውን ለማጋጨት የምትዘውሩት ባፍጢሙ እየተደፋ ነው:: ሌላ ዘዴ ፈልጉ:: ያንተ ተአማኒነት ደቼ የገባው ደመቀ መኮንን ለሱዳን የአማራን መሬት ሰጠ ብለህ ያልተረጋገጠ ስትፅፍ ተቃውሜህም ነበር:: ስሜታዊነት ይነዳሀል:: ሀገር የምትፈልገው የሰከኑ ሰዎችን ነው::

  2. አዲስ አበባ የኗሪዋ ነች። ሆኖም ጭንብል ተከናንቦ በነእስክንድር ስር ተሰግስጎ ያለ; የአዲስ አበባ ዋና ተጠቃሚና አቀንቃኝ የቀን ጅቦችና ወያነ ነው። በነዋሪነት ስም የባልደራስ ም/ቤት አማካሪዎች 27 አመት ሲዘርፉ የኖሩት ናቸው። ይህ ምንም እንኳ ለእስክንድር tactical move ቢሆንም ከሞት ለተረፉት ለእነ ዶ/ር አብይ ግን ስጋት ነው ። ዶክተር አቢይ እስክንድርን አነጋግረዋለሁ ባለ ማግስት ትእግስት እንጂ እንዲህ ያለ ጥድፊያና ቆረጣ ነገር ይኖረዋል ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.