ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የኢፌዲሪ ትራንስፖርት ሚኒስትር የአውሮፕላኑ አደጋ መርማሪ ቡድን ቅድመ ሪፖርት

‹‹ የተከሰከሰው አውሮፕላን አብራሪዎች ተገቢ ብቃትና የበረራ ፈቃድ አላቸው፡፡›› ትራንስፖርት ሚኒስቴር

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2011ዓ.ም (አብመድ) የተከሰከሰውን ንብረትነቱ የኢትዮጵያ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በተመለከተ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ መግለጫ እየሰጡ ነው፡፡

በመግለጫቸውም የመጀመሪያ የምርመራ ውጤቱን ይፋ አድርገዋል፡፡
ጉዳዩን ለማጣራት በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር ያለ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ተሰይሞ ወደ ተግባር ገብቷል፤ ሂደቱም አለማቀፍ አሰራሮችን ተከትሎ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

የምርመራ ሂደቱ ዓለማቀፍ ልምድ ያላቸውን ድርጅቶች ጨምሮ በጋራ የተሠራ መሆኑን ያሳወቁት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የመጀመሪያ ደረጃ የግኝት መረጃ በዓለማ ዓቀፍ መስፈርት መሠረት በአንድ ወር ውስጥ መውጣት ስላለበት መረጃው ይፋ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ይህንን መሠረት ያደረገ የተጠቃለለ መረጃም ዓለማቀፍ መስፈርቶችን በመከተል ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ የተጠቃለለው የአደጋ መረጃ ውጤት በአንድ ዓመት ውስጥ ይፋ መደረግ እንዳለበት ዓለማቀፍ መስፈርቱ ያሳያል፡፡

የምርመራ ውጤቱ እንዳመላከተውም፡-

1.አውሮፕላኑ መብረር የሚያስችል ማስረጃ አለው፣
2.አብራሪዎችም ተገቢ ብቃትና የበረራ ፈቃድ አላቸው፣
3.አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ በትክክለኛ መስመር እና ለመብረር የሚያስችለው ደረጃ ላይ ነበር፣
4.አብራሪዎቹ ለማብረር የሚያስችለውን ሂደት ተከትለው ለመቆጣጠር የሰሩ ቢሆንም መቆጣጠር አለመቻላቸው ታውቋል፡፡

እነዚህን የመጀመሪያ የምርመራ ውጤቶች መሰረት በማድረግም ለቀጣይ ምክረ ሀሳቦች ተሰጥተዋል፡፡

1.አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስቸገረ ሙከራ ስለነበረ የበረራ ቁጥጥር ስርዓቱን አምራቹ በድጋሜ ሊፈትሸው እንደሚገባ፣

2.የአውሮፕላን ስሪቱ ወደ በረራ ከመመለሱ በፊት በበረራ ወቅት የሚያስቸግረውን ክፍል ኩባንያው በድጋሜ ሊያስተካክል እንደሚገባ የደህንነት ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡

መጋቢት 1/2011 ዓ.ም በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል።

በአስማማው በቀለ

ፎቶ፡- በጌትነት ገደፋው/AMMG

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.