የፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የሜዲካል ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የሜዲካል ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ተመረቀ፡፡

የፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የሜዲካል ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ምረቃ በተከናወነው ስነ ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የጤና ሚኒሰትር ዶክተር አሚር አማን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውና ሌሎች ክፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ማዕከሉ ኦክስጅን አገልግሎትን ተደራሽነት ለመጨመር የጤና ሚኒስቴር 13 የኦክጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ለመገንባት ከያዘው እቅድ አንዱ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የኦክስጅን አገልግሎት መስጠት ከተቻለ በእርግዝና ወቅት የሚሞቱ 11 ሺህ ሴቶች፣ በተወለዱ የመጀመሪያ ወራቶች የሚሞቱ 60 ሺህ ህፃናትንና በየዓመቱ በሳንብ ምች የተነሳ የሚሞቱ 30 ሺህ ህፃናትን መታደግ ይቻላል ብለዋል።

በባህር ዳር የተገነባው ይህ የኦክስጅን ማዕከልም ወደ ፊት እነዚህን ችግሮች በመፍታት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ፣ ሳልትስ ፕሮጀክት፣ ጂኢ ፋውንዴሽንና ግራንድ ቻሌንጅ ካናዳን ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በቀጣዩ አመት መጨረሻ የቀሩት 7 የሜዲካል ኦክስጅን ማምረቻ ማዕከላት ግንባታ እንደሚጠናቀቅ ዶክተር አሚር ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አንባቸው መኮንን በበኩላቸው ማዕከሉ በኦክስጅን አገልግሎት እጥረት ምክንያት ረጅም ዕድሜ መኖር እየቻሉ በአጭር የሚቀጩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለመታደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ/አብመድ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.