በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ የሚፈፀመው ድብደባ ቀጥሏል

ነገረ ኢትዮጵያ

ምርጫውን ተከትሎ በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ የሚፈፀመው ድብደባ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ ትናንት ሚያዝያ 21/ 2007 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ፀኃፊ የሆነው አቶ ሳሙኤል አወቀ በደህንነቶች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት ኃላፊው ገልጾአል፡፡ አቶ ሳሙኤል ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ ወደ ቤቱ እየገባ በነበረበት ወቅት ሁለት ደህንነቶች አፍነው በመውሰድ ከሌሎች አራት ደህንነቶች ጋር በመሆን ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውበታል፡፡ ደህንነቶች ‹‹እንፈልግሃለን!›› ብለው ከወሰዱት በኋላ ‹‹ለምን አርፈህ አትቀመጥም?›› እያሉ ድብደባ እንደፈፀሙበትም አቶ ሳሙኤል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ የደ/ጎ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢና የፎገራ ወረዳ የተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ አቶ አለማየሁ አደመ ላይ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እንደተፈፀመበት ተገልጾአል፡፡ ደህንነቶች አቶ አለማየሁ በሚኖርበት ደራ ወረዳ አርብ ገበያ ከተማ ሚያዝያ 20/2007 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ደብደባ ፈጽመውበታል፡፡ አቶ አለማየሁ ድብደባው በተፈፀመበት አርብ ገበያ ጤና ጣቢያ እየተረዳ የነበር ቢሆንም ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ባህርዳር ሪፈራል ሆስፒታል መዛወሩ ታውቋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተባባሪ የሆነው አቶ አዲሱ ጌታነህ መንግስት አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን ግድያ ለመቃወም ባህርዳር ከተማ ላይ በጠራው ሰልፍ ተገኝቶ ከተመለሰ በኋላ ምሽት ላይ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.