እሽሩሩ ኦነግ (ከአንተነህ መርዕድ)

አፕሪል 2019

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ለኦሮሞ ህዝብ መብት የተነሳሁ ነኝ ቢልም ባለፉ አርባ ዓመታት ለምን እንደቆመ ተግባሩ እያሳየን ነው። በተለይም በዚህ የለውጥ ጊዜ ኢትዮጵያን ወደየት ይዟት ሊሄድ እንደፈለገ በተግባር ያሳየን ስለሆነ ዛሬ ሁሉም በሚገባ ያውቀዋል። ሁሉን አካታች የሆነው የኦሮሞ ህዝብ በስሙ በሚካሄድ ወንጀል የአገሩ ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ ከሌላው ወገኑ ጋርም በፍቅር የሚኖርበትን ሁኔታ እየተበላሸ ነው።

ከሁሉም በላይ ስልጣን ላይ ያለው የለውጥ ሃይል ኦነግን እሽሩሩ የሚልበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው። አምስት መቶ የማይሞላ ታጣቂ አለኝ ባለ በወሩ በአስር ሺዎች ታጣቂ አለኝ ሲልና ትጥቅ አልፈታም ብሎ ለያዥ ለገራዥ ሲያስቸግር ዝም ተባለ። ኦነግ ሲያልማት የኖራትን የተገነጠለች ኦሮምያ ሪፐብሊክ ለመመስረት ሁሉንም ለመዋጥ ሲያዛጋ እያየን ነው። አሁን ግን ከማዛጋት አልፎ እየነከሰም እያደማም ነው። ሶማልያ ለተፈፀመው እልቂትና ስደት ከአብዲ ኢሌ የበለጠ እንጂ ያነሰ ሚና አልነበረውም። ሃረርንና ድሬደዋን ለመሰልቀጥ በከባባ ነዋሪዎቹ ስቃይ ላይ ናቸው። በመቶ ሺህ የሚቆጠር የጌድዮ ህዝብ ላይ የተፈፅመው ዘኛኝ ግፍ አይደለም በድርጊቱ የተሳተፉትን ስልጣን ላይ ሆነው በቸልታ የተመለከቱትን ነገ ማስጠየቁ የማይቀር ነው። ኦነግ በደቡብ ለሚገኙ ሌሎችም ማህበረሰቦች የስጋት ምንጭ ነው። ቡራዩ የተካሄደው ዘኛኝ ጭፍጨፋ በግልፅ ለመናገር የዘርማጥፋት ወንጀል በሚገባ በመረጃ ተደግፎ የተቀመጠ ወንጀል ስለሆነ ነገ የሚወጣ እውነት ነው። አዲስ አበባን በመዳፉ ለማድረግና ነዋሪዋን ቅኝ ለመግዛት የተሄደበት ግልፅና ስውር ደባ የሚሳካ ባይሆንም ብዙ የሚያስከፍለን አደጋ ነው። ሞያሌ እንዲሁም ምዕራብ ወለጋ በዜጎች ላይ የተደረገው ግድያ፣ ዘረፋና የንብረት ማውደም ለሌላው ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለሁ ለሚለው ለኦሮሞው ህዝብም የማይመለስ አረመኔ ድርጂት መሆኑን በአደባባይ አስመስክሯል። አስራ ስምንት የህዝብ ባንክ ሲዘርፍ፣ የህዝብ መጠቀምያ የሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮችና መስሪያ ቤቶች ሲያወድም፤ የአካባቢ ተወላጁን ኢንቨስተር ከውጭ ባለሙያዎቹ ጋር ገድሎ ሲያቃጥል ኦነግ ለኦሮሞ ህዝብ ቆሟል የሚል ካለ ጤነኛ አይደለም።

የቤንሻንጉል ባለስልጣናትን በመግደል በኦሮሞዎች ጉረሮ ላይ ቆሞ በመቶ ሺዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሲሆን አሁን  ደግሞ ወደ አማራው ሰሜን ሸዋና ወሎ ዘልቆ ከመንግስት የውስጥ ደጋፊዎቹ ባስታጠቁት ከባድ መሳርያ ንፁህ ኢትዮጵያውያንን ሲገድል ኦሮሞው ከሌላው ወገኑ ጋር በሰላም እንዳይኖር እያዘጋጀው ያለው አደጋ የማይታየው ካለ የሞተ ብቻ ነው።

ባለፉት ሶስት የትንቅንቅ ዓመታት በወያኔ ስናይፐር ሺ ወጣቶች በአደባባይ ሲረፈረፉ አንዲት ጥይት መተኮስ ሳይችል በኢሳያስ ጉያ የነበረ ልፍስፍስ ድርጂት ዛሬ ሺ ንፁሃንን የሚገድልበት ጉልበትና ችሎታ የት አገኘ? መልሱ ቀላል ነው። ኦህዴድ ውስጥ ተጠልለው የኖሩ ዘራፊና ፈሪ ዘረኞች መሳርያውን፣ ገንዘቡን፣ መንግስታዊ ተቋሙንም ከፍተው አቅም ሰጥተውታል። ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እነሱንም እንዳይጠራርግ ህወሃት ትቶት የሄደውን ስልጣንና የሃብት ምንጭ ተቆጣጥረው ተረኛ አምባገነን መሆን ያለሙ ለናቸው በእያንዳንዷ ክፍት ቦታ ራሳቸውን ሲሞሉ እያየን ነው።

ትናንት የአገር ጠላት ህወሃት መራሹ ጨካኝና ዘራፊ ቡድን ነበረ። በህዝብ ትግል ተወግዷል። ዛሬ ደግሞ ጎልቶ ያልወጣ ቢመስልም በኦነግ ዓላማ ዙርያ ኢትዮጵያን ቀፍዶ የሚይዝ ሌላ ዘረኛና ዘራፊ አምባገነን ስርዓት ለመትከል ቅርፅ እየያዘ የመጣ ሃይል በተረኛነት በኢትዮጵያ አድማስ ላይ ይታያል። ከዓመት በፊት የተለኮሰውን ተስፋ ሊያደበዝዝ ጥላውን ዕያጠላ ያለው አስፈሪ ዘረኝነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመርና የፍቅር እንዲሁም የለማ መገርሳ ኢትዮጵያ ሱሴ አማላይ ሰበካ የሚወገድ አይደለም። ያዘናጋን እንደሆነ እንጂ።

መፍትሄው በህዝቡ እጅ ነው። መንግስት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ እተሳነውና የተደራጀ ዘረኛ ቡድን ተስፋፊ ፍላጎቱን በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ለመጫን እድል እየሰጠው ስለሆነ ራሱን መጠበቅና ለውጡን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ማስኬድ የህዝቡ ሃላፊነት ነው። ስለሆነም

 • ህዝቡ መንግስት የአገሪቱን ፀጥታ እንዲያስከብር ጠንክሮ መጠየቅ፣ መታገልና ማስገደድ፤
 • ህዝቡ በየአካባቢው በመደራጀት የአካባቢውን ፀጥታ መጠበቅና ግጭቶች እንዳይነሱ መከላከል፣ ከአጎራባች ህዝብ ጋር መልካም ግንኙነት መቀጠል፣ ለጋራ ደህንነት መተባበር፤
 • በፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በዘር ልዩነት የሚራገቡ ቅስቀሳዎችን ማስወገድ፤ ይህንን ልዩነት የሚሰብኩትን እንዲያቆሙ ማስገደድ፤
 • በተፈጠረው ቀውስ የተፈናቀሉትን ማቋቋም፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ፤
 • የአገሪቱ ኤኮኖሚ አደጋ ላይ ስለሆነ ምርት እንዲጠናከር፣ ገበያ እንዲስፋፋ፣ የህዝብ ግንኙነት እንዲሳለጥ ማድረግ። የምርት ቋማት ላይ የሚደረግን ጥቃት መከላከል፤
 • በባህላችንም፣ በእምነታችንም ያልነበረውን እየተለመደ የመጣውን ጭካኔ ማውገዝና መከላከል ያስፈልጋል

መንግስት ኦነግን እሽሩሩ የሚልበት እንቀልባ እስኪበጠስ በትዕግስት ስንጠብቅ አገራችንን እናጣታለን። ዛሬ መንግስት የምንለው ሃይል የጠራ አቋም ወይንም አቅም ያለው አይመስልም። አቋሙ ሆነ አቅሙ የህዝቡን ፍላጎት ማካተት የሚችለው ህዝባዊ ትግሉ ሲቀጥል ነው። አሁን “ፖለቲከኛ” ነኝ የሚለው አማተርም ሆነ ህዝቡ የለውጥ ሃይል ከሚባለው አካል ብዙ ይጠብቃል። ጨርሶ ስህተት ነው። እነዚህ ሰዎች በህዝብ ትግል ተገድደው አገልጋይነቱም ሰልችቷቸው ትግሉን ተቀላቀሉ እንጂ በተፈጥሮአቸው የለውጥ ሃይል አይደሉም። በህዝብ ሙቀትና ጭብጨባ የጀመሩት እስክስታ ከውስጣቸው የመነጨ አለመሆኑን ተግባራቸው እያሳየን ነው። ዋናውን ስራቸውን ትተው አሁንም ድቢ እየመታን እንድናጂባቸው እንጂ ስህተታቸውን እንድንነግራቸው ፍላጎት እያሳዩ አይደለም። ቀዝቀዝ ስናደርግ ሲቆጡና ሲደናገራቸው፣ እልፎ እልፎም የከፈሉትን መስዋዕትነት ሊሰብኩን ይዳዳቸዋል። ልጆቻቸው በስናይፐር ከተገደሉባቸው ወላጆች ወይንም ጥፍራቸው በፒንሳ፣ ብልታቸው በሃይላንደር ከተጎተቱት በላይ መስዋዕት ከፍለናል ሊሉን ምንም አልቀራቸውም። ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን እንደሚባለው የትናንቱን ረስተን ወደ ወደፊት እንሂድ ያለን ህዝብ የዛሬ ጥፋታቸውን እንዲያርሙ ሊነገራቸው ሲሞከር ትናንት የሰሩትን “ገድል” ሊሰብኩን ይዳዳቸዋል። ህወሃትም የአስራ ሰባት ዓመት ገድልና የስልሳ ሺህ መስዋዕት ለሃያ ሰባት ዓመት ሰብኮ አልጨረሰውም። አላሳመነንም። ከህዝብ የተደበቀ መስዋዕት ሆነ ወንጀል የለም። አንበሳ ጦጣን “ነይ ውረጅ አልበላሽም” ሲላት “አልበላሽምን ምን አመጣው?” ብላለች። “ትናንት ይህን አድርገናል” የሚል የውለታ ጥያቄ የዛሬን ስህተት አይሸፍንም።

አብይ ሆይ ያለምንም ዋስትና ከሰንሰለት የለቀቅከው ኦነግ ዛሬ ህዝብና አገር እያደማ ነው። አንተንና ጓዶችህን ለመብላት እንደማይመለስ ልቦናህ ያውቀዋል። የጊዜ ጉዳይ ነው። ትናንት በአንቀልባ እሹሩሩ የተባለው ኦነግ ዛሬ በመግዘፉ አንቀልባውን በጥሶ አዛዩን ሊያጠቃ ምንም አልቀረውም። አዝሎት ያመጣውን ያጠፋ እነደሆነ እንጂ ኢትዮጵያና ህዝቧ ራሳቸውን ለመጠበቅ ይገደዳሉ።

1 COMMENT

 1. እሽሩሩ አሹሩሩ እስክንድር እሹሩሩ !!!

  የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰብ መኖሪያ ፡ የፌድራል መንግስት መቀመጫ ና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በሆነችው በአዲስ አበባ እስክንድር ነጋ በአዲስ አበባ ኗሪ ስም ባለአደራ ምክር ቤት የሚል ህጋዊ እውቅና የሌለው ቡድን አደራጅቶ እራሱን በመሾም መቶ በመቶ የአማራ ተወላጅ ወጣቶችን በዙሪያው በማሠባሰብ ና በማደራጀት በስመ አዲስ አበባ ኗሪ ለድብቅ አላማ ከዉጭ ሀገር ካሉ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የተሸሸጉ አክራሪ የአማራ ብሔረተኞች ጋር በመጣመር እየሠራ መሆኑን ኗሪው ማወቅ አለበት፡፡

  ይህ በአዲስ አበባ ህዝብ ስም ምንም ውክልና የሌለው በእስክንድር ዙሪያው በተሰባሰቡ የአማራ ተወላጆች የተቋቋመ የአማራ ባለአደራ ምክር ቤት እንጂ የአዲስ አበባን ህዝብ የማይወክል የዘር ቡድን መሆኑን ድብቅ የስልጣን አላማውን ለማሳካት የአአ ህዝብ የፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ ህዝቡን ከመንግስት ጋር እና ከወንድሙ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ለማጋጨት ና አጣበቂኝ ውስጥ ለመክተት እየሠራ ያለ እንጂ ለህዝቡ ጥቅም ያለመሆኑን በመረዳት አምርሮ በመታገል እኩይ አላማውን ማክሸፍ አለበት፡፡

  አለበለዚያ ይህ በእስክንድር የተጀመረው የአማራ ባለአደራ ምክር ቤት ማስቆም ካልተቻለ እንዲቀጥል ከተደረገ በእርግጠኝነት በአጭር ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የሌሎች ብሔሮች ባለአደራዎች መፈልፈላቸው እንደማይቀር ና ውጤቱንም ደግሞ የከፋ ስለሆነ መንግስት የህዝቡን ሠለም የማስከበር ሀላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡

  እውነት ምን ጊዜም ታሸንፋለች !!!.

  በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የተሸሸገ ብሔረተኝነት ሐገር ሲያፈርስ እያየን ዝም አንበል !!!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.