የአዲስ አበባን ነገር . . . (ከናፍቆት ገላው)

በአንድም በሌላ መልኩ ከወሰን አከላለል እና ከማንነት ጋር በተያያዘ በየአቅጣጫው የሚነሱ አለመረጋጋቶች፤ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በተደጋጋሚ ሲያንገዳግዱት አይተናል። በዚህ ሰሞን ከአዲስ አበባ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ትንቅንቅ ያህል ግን ለውጡን በኃይል የናጠ ፍጥጫ ያጋጠመን አይመስለኝም። አዲስ አበባን በተመለከተ የሚነሳው አለመግባባት፤ መሰረታዊ የሀሳብ ልዮነት ያዘለ መሆኑ የሚካድ አይደለም። ሆኖም፤ ሁኔታው ወደ መጋጋል የማደጉ ምክንያት ከሀሳብ ልዮነቱ ግዝፈት የሚነሳ ነው የሚል እምነት የለኝም። በእኔ እይታ፤ ልዮነቱን ወደ አልተፈለገ መካረር እንዲያመራ ትልቁን ሚና የተጫወተው፤ በሁሉም ወገን ያሉ የፖለቲካው ተዋናዮች የተያያዙት ከራእይ ይልቅ ቁጣ እና እልኸ የሚዘውረው ፖለቲካ ነው። ነገሩን አርግቦ፤ ለውጡን ለመታደግም፤ ፈር የለቀቀውን ግብ ግብ ወደ ተረጋጋ ወይይት መግራት ወሳኝ ይመስለኛል።

በአዲስ አበባ ዙርያ የተቀሰቀሰው ውጥረት፤ በአንድ ቀን የፈነዳ አይደለም። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ፤ የተለያዮ ክስተቶችን ታኮ ሲንተከተክ የከረመ ነው። ወደ ኋላ ተመልሰን ካየን፤ በቡራዮ የደረሰውን ጥቃት ያስተናገድንበት አግባብ፤ ነገሮች ባልተፈለገ አቅጣጫ እንዲፈሱ አሉታዊ እርሾ የጣለ አንዱ አጋጣሚ ይመስለኛል። አደጋ እንደ አያያዙ ነው። ወይ ያሰባስባል ወይ ይበትናል። የቡራዮ ጥቃት፤ አላሰባሰበንም። በአደጋው ማግስት፤ ጥቃቱን በአንድ ድምጽ ከማውገዝ እና ለተጎጂዎቹ በሕብረት ከመድረስ ይልቅ፤ የጥቃቱ መንሰኤ እከሌ የሚባል ግለሰብ ቀስቃሽ ንግግር ነው፤ ጥቃቱን ያደረሰው በመደመር ስም ሀገር ውስጥ የገባ እንደዚህ የሚባል ቡድን ነው። በሌላም በኩል፤ የእኛን ስም ለማጠልሸት እንዲህ የተባለ ቡድን ያቀናበረው አደጋ ነው እና በመሰል መወነጃጀሎች ተጠመደን ነው ያሳለፍነው። ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚያደርጉት ቅስቀሳ ለጥቃቱ መንሰኤ ሆኖል የሚል እምነት ካለ፤ መፍትሄው፤ ሕብረተሰቡ ውስጥ ለጠብ እና ግጭት እድል የሚሰጥ ድባብ እንዳይሰፍን አብሮነትን የሚያንጽ ስራ መስራት ነው። በተረፈ፤ ቀጥተኛ እና የሚያስተማምን መረጃ በሌለበት፤ ተጠያቂው ይሄኛው ወይም ያኛው ቡድን ነው የሚል መረጃ በሚዲያ ማቀበል ህዝብን ስሜታዊ ለሆነ አጸፋዊ መልስ በማነሳሳት ለማያባራ የግጭት አዙሪት በር መክፈት ይሆናል። እዛም ካላዳረሰን፤ መወነጃጀሉ የሚጋብዘው አላስፈላጊ እሰጣገባ በቀጣይ የሚገጥሙ ልዮንቶች የሚስተናገዱበትን መንፈስ ያሻክራል።

የቡራዮን አደጋ ተከትሎ፤ በአንዳንድ የኦሮሚያ ህንጻዎች ላይ የተሞከሩ ጥቃቶች፤ በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ የግለሰቦችን ስም እየጠሩ ይውጣልን ሲሉ የተሰሙ ድምጾች፤ አግባብ ያልነበሩ እና ውግዘት የሚገባቸው ድርጊቶች ነበሩ። አንዳንድ አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞች፤ በአደጋው ዙርያ ሲያቀርቡት የነበረው ጥንቃቄ የጎደለው ትንተና፤ ለክስተቱ አስተዋፆኦ አድርጎም ይሆናል። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ በወቅቱ ድርጊቱን ለማውገዝ፤ አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ፖርቲዎች በህብረት ያወጡት መግለጫ፤ በስሜታዊነት እና በግርግር መኃል፤ ቁጥራቸው እዚህ ግባ በማይባል ግለሰቦች ተሳትፎ የተፈጠረን ክስተት ወደ “ኦሮሞነትን ከአዲስ አበባ የመግፋት፤ ኦሮሞ ጠል እንቅስቃሴ” አድጎ የቀረበበት ሁኔታ ሚዛን የሳተ ነበር ባይ ነኝ። የኦሮሞ የአዲስ አበባ ባለቤትነት፤ መግለጫው አስረግጦ ካለፈው መልክቶች ዋናው ነበር። መግለጫው አያይዞም ሌሎች ብሔሮች አብረው መኖር እንደሚችሉ ያስቀምጣል። በወቅቱ፤ አቶ በቀለ ገርባ ከኤልቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ ይህን አቋም በመግለጫው ውስጥ ማካተት ለምን እንዳስፈለገ በሰጡት ማብራሪያ፤ በአዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሞ መሰረት ባላቸው ድርጅቶች ላይ በተቃጣው ጥቃት ምክንያት፤ መሬቱ የማን እንደሆነ ማስታውሱ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኙት መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ ሌላ ርእስ ሆኖ፤ አዲስ አበባ ኦሮሞነትን ትገፋለች የሚል ስጋት ግን ትክክለኛ እይታ ነው ብየ አላስብም። ለውጥ ላይ እንደመሆናችን ፖለቲካችን የተረጋጋ አይደለም። ባልተረጋጋ ፖለቲካ ግጭቶች ይኖራሉ። ፖለቲካችን ብሔር ተኮር እንደመሆኑ ግጭቶቹ የብሔር መልክ መያዛቸው አያስገርምም። ሆኖም እነዚህ ግጭቶች ምንጫቸው ግዚያዊ ፍራቻ እና ቁጣ እንጅ ስር የሰደደ ጥላቻ አይደለም። በአንድነት፤ በስምምነት መንፈስ ውስጥ ስንሆን፤ ለኦሮሞነት እንግዳ ያልሆነው አዲሳቤ አይደለም፤ የባህርዳር ህዝብ፤ ለማ መገርሳ አማራ ክልል በሄዱበት ወቅት፤ የእኛስ ልጆች ለምን ኦሮመኛ አይማሩም፤ የኦሮሞ ባህል ማእከል ከተማችን ውስጥ ይገንባልን የሚል ጥያቄ ሲያስተጋባ አይተናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ እየተወራረሰ ነው የኖረው። አንድነቱ እስከተጠበቀለት ድረስ ይህን አጠናክሮ መቀጠል አይገደውም። ኦሮሞነት አዲስአበቤነት ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፈ ማንነት ነው። ወደፊትም አዲስ አበባ ኦሮሞነትን ይበልጥ ተላብሳ እንዳትቀጥል የሚቸግራት ነገር አይኖርም። ነገር ግን፤ አያት ቅድመ አያቶቻችን በጋራ አቅንተው፤ በጋራ ጠብቀው ባወረሱን ሀገር፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ላይ፤ አንዱን ባለቤት አድርጎ፤ የተቀርውን በገዛ ሀገሩ የመኖር ፈቃድ የሚሰጥ አስተሳሰብ አብሮነትን የሚረዳ አይደልም።

በከንቲባው ሹመት ዙርያ የሚነሳው ውዝግብ፤ ሌላው የአዲስ አበባን አጀንዳ አለቅጥ የወጠረው ጉዳይ ይመስለኛል። በመጀመርያ ደረጃ አዲስ አበቤነትን የሰራው ኢትዮጵያዊነት ነው። የአዲስ አበባ ከንቲባ ለመሆን ኢትዮጵያዊ መሆን በቂ መስፈርት ነው። ለኔ፤ ከዚህ በተቃራኒ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች፤ አዲስአበቤነትን አጥቦ ከመረዳት የሚመነጩ ሆነው ነው የሚታዩኝ። የከንቲባው ሹመት ህጋዊነት ላይ የሚነሱ ቅሪታዎች፤ በተናጠል ከመዘንናቸው፤ አሳማኝ ሆነው ሊታዮ ይችላሉ። አጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አውድ ውስጥ ከተን ካየናቸው ግን ያን ያህል ትርጉም የሚሰጡ አይደሉም። አሁን ባለው ኢሕአዲጋዊ የመንግስት ስርአት፤ ከንቲባዎች ይሾማሉ እንጅ አይመረጡም። ይሄ ለአዲስ አበባ የተለየ አይደለም። የሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች ነባራዊ ሁኔታ ነው። ወደፊት ህዝብ መሪዎቹን በቀጥታ የሚመርጥበት ስርአት እንዲኖር መታገል ተገቢ ነው። ነገር ግን፤ አንድ ሀገር ውስጥ ዲሞክራሲ ወጣ ገባ ሆኖ ሊተገበር የሚችልበት ሁኔታ የለም። አዲስ አበባ ከንቲባዋን የምትመርጥበት ቀን፤ የጅማ ወይም የጎንደር ነዋሪዎች ከንቲባቸውን በቀጥታ ከሚመርጡበት ቀን ቀድሞ ሊመጣ አይችልም። ይሄ እውን የሚሆነው ደግሞ፤ በሀገር ደረጃ ስምምነት ፈጥሮ አስተማማኝ ዲሞክራሲ መዘርጋት ሲቻል ብቻ ነው። መሰረቱ ሲስተካከል ሁሉም ነገር ቦታ ቦታውን ይይዛል። በአንጻሩ፤ እንዲህ አይነት ቁንፅል ነገሮች ላይ መቸንከር፤ ወሳኙን ዲሞክራሲያዊ ተቋማት የመገንባት አጀንዳ ወደ ኋላ እየገፋ፤ በምርጫ በተመረጠ መንግስት የምንተደደርበትን ግዜ ይባስኑ ያርቀዋል።

መንግስት ህግ የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነቱን እንዳይዘነጋ የማያቋርጥ ጫና መፍጥር አስፈላጊ ነው። አግባብነት የሌላቸው ድርጊቶች ሲፈጠሩም እርምት መጠየቅ ይገባል። ከዛ ባለፈ ግን፤ የመንግስትን አስተዳደራዊ ኃላፊነት የሚጋፋ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ትክክል አይሆንም። የኢሕአዲግ ስልጣን ከምርጫ ኮሮጆ እንዳልመጣ፤ ሁሉም የሚያውቀው እውነት ነው። የኢሕአዲግን አስተዳደር እውቅና የመስጠቱ አስፈላጊነት፤ ውክልና አለው የለውም ከሚል ክርክር የሚነሳ አይደለም። ተወደደም ተጠላም፤ ባለፉት ሦስት አስርት አመታት ኢሕአዲግ ሀገር ሆኖል። አስተሳስሮ ያኖረን ሀገራዊ አንድነት ከምንግዜውም በላይ በላላበት፤ ምንም አይነት ነጻ መንግስታዊ ተቋማት በሌሉበት፤ ሀገረ መንግስቱ ተደግፎት የቆመው ብቸኛ ባላ የኢሕአዲግ መዋቅር ነው። የተናደው አንድነታችን በቅጡ ሳይጠገን፤ የዲሞክራሲ መሰረተ ልማት ሳይዘረጋ፤ ኢሕአዲግ በዚህም በዚያም ተገዝግዞ ህልውናውን ቢያጣ፤ ሀገር በላያችን ላይ ላለመደርመሱ እርግጠኞች አይደለንም። እየዘነጋን ካልሆነ፤ ኢሕአዲግ ከስሩ ተነቅሎ ከመውደቁ በፊት፤ ከውስጡ ተራማጅ ቡድን ወጥቶ፤ ያለብዙ እንገጭ እንጎ የለውጥ ምዕራፍ ሲከፈት፤ እንደዛ በደስታ ያሰከረን ቁምነገር ከዚህ የሀገር መፍረስ አደጋ እፎይታ ማግኝታችን ነበር።

በመንግስት አካላት በኩል የታዮ ክፍተቶች፤ የአሰራር ግልጽነት መጉደል፤ እንዲሁም የደህንነት ስጋት የሆኑ የጎዳና ላይ እንቅስቃሴዎችን ከመከላከለ ሆነ ከመኮነን አንጻር የነበረው ቸለተኝነት፤ የአዲስ አበባ ዙርያ ለተነሱ አለመግባባቶች መጋጋል የራሱ አስተዋፆ ነበረው። ሆኖም፤ መንግስት በነጻ ሀሳብን የማሰማት እና በሀገራቸን ጉዳይ ላይ የመሳተፍ መብታችን እስካላገደ ድረስ፤ አሁንም የሚሻለው ተቀራርቦ፥ መንግስት አሰራሩን ለህዝብ ቅርብ እንዲያደርግ፤ የተወሰኑ ግለሰቦች ሆነ ቡድኖች ከህግ ውጭ እንዳሻቸው ትዛዝ ሊያስተላልፉ የሚችሉበትን እድል እንዲዘጋ፤ ሕብረተሰቡ በአግባቡ ቅሪታውን አሰምቶ እርምት የሚያገኝበት አሰራር እንዲያመቻች፤ ጸጥታ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ አጠቃላይ በህዝብ እና በመንግስት መኃል አለመተማመን የሚፈጥሩ ክፍተቶን እንዲያጠብ በትብብር መስራት ነው። የኢሕአዲግ የለውጥ ኃይል፤ ከተለመደው የመገፋፋት ፖለቲካ ወጥቶ፤ ለጋራ አላማ ተደጋግፎ ለመቆም፤ ተቀናቃኝ ሀሳቦችን አስታርቆ ሀገራዊ አንድነትን ለማነጽ ያሳየው ቁርጠኝነት ብዙ እርቀት አራምዶናል። ይሄ መሆን የቻለው፤ ገዥ ሀሳብ ገፍተው የህዝብን አመኔታ ማተርፍ ስለቻሉ ነው። ወደፊትም፤ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የያዙትን ማዕከላዊ ሚና አስጠበቀው ለመቀጥል፤ ሚዛን የሚያሳጣቸውን የውስጥም የውጭም ችግር አጥርተው፤ የመጡበትን መንገድ አጠናክሮ መቀጠል ከነሱ የሚጠበቅ ይሆናል።

 

አዲስ አበባን ተንተርሶ የሚነሳ ማንኛውም አለመግባባት፤ እራሱን ችሎ የቆመ አይደለም። ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ውስብስብ የፖለቲካ ሁነት የሚመዘዝ ነው። የሀገሪቱ ፖለቲካ ከመሰረቱ እየተደላደለ ሲሄድ፤ አዲስ አበባ ተኮር የሆኑ ልዮነቶችን መፍታት ቀላል ይሆናል። በተቃራኒው፤ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ፖለቲካ እምብርት እንደመሆኖ፤ አዲስ አበባ ላይ ነገር ከተበላሸ አጠቃላዮን የሀገር ፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ የመክተት አቅም አለው። ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። የአዲስ አበባን ጉዳይ መጠላለፍ ውስጥ ያስገባው አንዱ ምክንያት፤ ነገሩ ከአጠቃላዮ ፖለቲካ በጣም ተነጥሎ የተራገበበት ሁኔታ በመፈጥሩ ይመስለኛል። እይታችን አንድ ነገር ላይ ያለቅጥ በተተከለ ቁጥር፤ ሚዛን እንስታለን። ይህ እንዳይሆን፤ አካባቢያዊ ስጋቶችን ለመቅረፍ ሆነ ፍላጎታችንን ለማስፈጸም የምንሄድበት መንገድ፤ ከሀገራዊው ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባት ራእይ ጋር ማናበብ ጠቃሚ ይሆናል። ዙሪያ ገባውን ያማከለ እይታ፤ ለችግሮቻችን ትክክለኛ እና ዘላቂ የመፍትሄ አማራጮችን የማየት እድላችንን ያሰፋዋል።

ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማቆም ስንሞክር እኛ የመጀመርያዎች አይደለንም። የሰው ልጅ ያላለፈበት አዲስ ፈተና አልገጠመንም። መሸናነፍ እንደማንችል በግዜ ተረድተን ለመገናዘብ መነጋገር ብንችል፤ ከመካሰስ ይልቅ ያላግባባንን ነገር ከምንጩ ተረድተን መፍትሄ ለማፈላለግ ብንተጋ፤ መላ የማይገኝለት ነገር አይኖርም። እንደ እኔ፤ ይህን እንዳናደርግ እንቅፋት እየሆነብን ያለው እልኸ እና ቁጣ የሚያጠቃው ፖለቲካችን ነው። በድርድር ፍላጎቶቻችንን ለማጣጣም፤ ስጋታችንን ለመቅረፍ የሚያስችል ጤናማ የመስተጋብር ዘይቤ ስላላዳበርን፤ ለሁሉም ችግር መልሳችን ቁጣ ሆኖል። በዚህም በዛም የሚወረወሩ ኃይለ ቃሎች፤ መግለጫዎች፤ ከይዘታቸው ይበልጥ ድምጸታቸው ይጎረብጣል። “ለተቃራኒ ቡድን” የመልስ ምት ከመሆን ተሻግረው፤ አለመግባባቱን ከማስታረቅ አንጻር ሊኖራቸው የሚገባው ዋጋ የታሰበበት አይመስልም። በዚህ ምክንያት፤ አንዱ የሌላውን እልኸ እና ቁጣ ያለማቆረጥ የሚቀሰቅስበት አዙሪት ውስጥ እየገባን ነው። ከዚህ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ስሜታዊነትን አሸንፈን፤ አካሄዳችንን ለራእይ የማስገዛት አቅም መፍጥር ይኖርብናል። መለያየትን በመቀራረብ፤ ፉክክርን በመተጋገዝ መንፈስ ለማሸነፍ ቁርጠኛነቱ ያስፈልገናል። ቀላል አይደለም። ነገር ግን፤ ሁለት ወዶ አይሆንም። ቁጣ ሀገር አይገነባም። ሀገር ይኑረን ካልን፤ ወደ መግባባት የሚያደርሰንን መንገድ ለይተን መያዝ ግድ ይላል።

ከናፍቆት ገላው

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.