የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ እንደቀጠለ ነው፤ ከ700 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍልም ተጎድቷል

መጋቢት 30 ቀን 2011ዓ.ም በድጋሜ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ያጋጠመው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለአምስተኛ ቀን ሲቃጠል ውሏል።

ከግጭ የተነሳው እሳቱ በፓርኩ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ገደላማው ክፍል ገብቷል። በሂደት የታችኛውን የፓርኩ ደን መያዝ ከጀመረ አስከፊ ውድመት ሊያደርስ ይችላል። ገደላማ በመሆኑም በሰው ኃይልም ለመቆጣጠር የሚቻል አይሆንም።

የኢፌዴሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሪት ካሳው የሚመሩት ልዑክ ዛሬ ፓርኩን ሲጎበኝ ውሏል። የመፍትሔ ሐሳብ ለማስቀመጥ ማምሻውን ቡድኑ ቀን የተመለከተውን እንደሚገመግምም ታውቋል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላን ከኬንያና ደቡብ አፍሪካ ለማምጣት ጥረት መጀመሩ ቢያስታውቅም የኬንያው በራሷ ፓርክ ቃጠሎ በመነሳቱ አልተሳካም። የደቡብ አፍሪካዎቹም ጉዞ ስለመጀመር አለመጀመራቸው የተባለ ነገር የለም፤ በረራው ግን ከ15 ሰዓታት በላይ እንደሚወስድ ታውቋል። አንዳንድ ምንጮች አውሮፕላኖቹ ከማክሰኞ በፊት የመምጣት ዕድል እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው።

ማምሻውን ቃጠሎው ባለበት የፓርኩ የተወሰነ አካባቢ መጠነኛ ዝናብ ጥሎ በደቂቃዎች ቆሟል። ከቦታው ከደቂቃዎች በፊት ባገኘነው መረጃ መሠረት የጣለው ዝናብ በጣም ዝቅተኛ ነው። አንዳንዶች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቁት “ከፍተኛ ዝናብ ጥሏል” የሚል ኃላፊነት የጎደለው መረጃ በሰው ኃይል የሚደረገውን እሳቱን የመቆጣጠር ሂደት እንዳያቀዛቅዝ ተሰግቷል። ከመጋቢት 19 እስከ 26 በነበረው ቃጠሎ ዝናብ እንደጣለ በመግለጽ የሚያዘናጉ ነበሩና።

በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከ700 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል ተጎድቷል፤ በአጥቢ እንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተገለጸ ነገር የለም። የአዕዋፋት እንቁላሎችና አነስተኛ እንስሳት ግን ተጎድተው መመልከታቸውን በእሳት ማጥፋቱ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ነግረውናል።

ዘጋቢ፦ አብርሃም በዕውቀት/አብመድ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.