ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ማን ናቸው?

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 የተወለዱት በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በሕዝብ አስተዳደር ወስደዋል የአንዲት ሴት ልጅም እናት ናቸው ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ።

ወይዘሪት ብርቱካን የፌዴራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር እንዲሁም የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትም ነበሩ።

በዳኝነቱም ይሁን በፖለቲካው መስክ ትልቅ ስም ያላቸው ወይዘሪት ብርቱካን በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲከበር በከፈሉት ዋጋ በብዙዎች ዘንድ በጥንካሬያቸውና በከፈሉት መስዋዕትነት በአርአያነት ይጠቀሳሉ።

ፖለቲካውን ከመቀላቀላቸው በፊት በአዲስ አበባ የፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው አገልግለዋል።

በወቅቱ በሙስና ወንጀል በህግ ቁጥጥር ስር የነበሩትን የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትር ስዬ አብርሃ ጉዳይ እንዲመለከቱ የክስ መዝገብ ቀርቦላቸው ነበር።

በብዙዎች ዘንድ የፖለቲካ እስር ተደርጎ የሚገለጸውና በሙስና ተሳቦ እንደታሰሩ የሚነገርላቸውን የአቶ ስዬን ጉዳይ መመልከት ለዳኛ ብርቱካን የጥንካሬያቸው መለኪያና ለሙያቸው ያላቸውንም ታማኝነት የሚያሳዩበትን አጋጣሚ የፈጠረ ነበር።

ወይዘሪት ብርቱካን ወደ ፖለቲካው የመጡት በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ላይ ሲሆን በቀስተ ደመና ፓርቲ በኋላም በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ውስጥ በመሳተፍ በወቅቱ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ፖለቲከኞች አንዷ ለመሆን በቅተዋል።

የ1997 ምርጫ ቀውስን ተከትሎ አገር መክዳት በሚል ወንጀል ተከሰው ለሁለት ዓመት በእስር የቆዩት ወይዘሪት ብርቱካን በወቅቱ መንግስት በይቅርታ እንዲፈቱ ያቀረበላቸውን የይቅርታ ሰነድ አልፈርምም በማለት በአቋማቸው ከጸኑት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ከእስር ከተለቀቁ በኋላም አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲን በመመስረትና በመምራት በፖለቲካው ዓለም ቆይተዋል።

ከእስር ቤት የወጡበትን ትክክለኛ ምክንያት ስዊድን ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በመግለጻቸውም በድጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።

በ2002 ዓ.ም በድጋሚ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመያዝ ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ በተሰኘ ተቋም በምርምር ሥራ ተሰማርተው ቆይተዋል።

ላለፉት ስድስት ዓመታት ከፖለቲካው ዓለም ርቀው የቆዩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ በቅርቡ ወደ አገር ቤት ገብተዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሹመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.