እምቧ በይ ላሚቱ! (በላይነህ አባተ)

ትናንትናም ዛሬም ከብቱ ባይረዳው፣
ካራ ደምን አፍሳሽ ነፍስ አጥፊ እሚሆነው፣
ተቀንድ ወይም ተእንጨት ሲገባ ብቻ ነው፡፡

ታዲያ ጊደር ላሟም ቀንዱን ዛቢያ ትተው፣
ጠላት እሚያደርጉት አራጁን ካራን ነው፣
ልክ እንደ ደን ዱሩ ጨፈቃና ጫካው፣
ጠማማውን ትቶ ምሳር እንደሚያማው፡፡

ያርድ እየመሰላት ተዛቢያው ሳይገባ፣
ላም ደም ታፈሳለች በስለቱ ካራ፡፡

ተበሬ ጭንቅላት የበቀሉ ቀንዶች፣
ሰክተው ሰክተው ተስለት ካራዎች፣
አንገቷን ገዝግዘው ጡቷን ነካሺዎች፣
ደሟን አንደቅድቀው ቀይ ባህር አረጉት፡፡

ተቀንድ የተጋባው አረመኔው ካራ፣
ሆዷን ዝክዝክ አርጎ አንጀት አወጣና፣
ለቅርጫ አቀረባት ዘጠኝ አረገና፡፡

ሐፍረትን የማያውቅ ካራ ዛሬ ደሞ፣
ደንደሱን አስልቶ ሁለት ምላስ ሰርቶ፣
ላምን እንታደግ ይላል ቅዱስ ሆኖ፡፡

ተፈጥሮው ነውና አይገርምም ካራውስ፣
ለሥጋም ለነፍስም የሚከብድ ለመንፈስ፣
ቀንድ ያበረከተው የበሬው መልፈስፈስ፡፡

ልበ ቢሱ በሬ አድሮ እማይማረው፣
የጫፉ ሳር እንጅ ገደሉ አይታየው፣
ሁለት ምላስ ሆኖ ካራው አታለለው፡፡

የቀንዱ እጀታ ካራን ያፈቀረው፣
ስንኖር የላም ልጅ እያለ ቢሰብከው፣
ቢላዋም ላም ሱሴን ሲዘምር ቢሰማው፣
መነዳቱ አይቀርም ዳግም አምኖ በሬው፣
ጊዜውን ጠብቆ ፍሪዳ እስቲያደርገው፡፡

እምቧ በይ ላሚቱ ከታሪክ ተማሪ፣
ዝምሎ እሚነዳውን በሬን አትመኝ!

እምቧ በይ ላሚቱ እፈሪ በበሬው፣
ቀንዶቹን ገብሮ ያስበላሽ እሱ ነው፡፡

እምቧ በይ ላሚቱ ለጥጃሽ ንገሪ፣
የቀንድን ባንዳነት በደንብ አስተምሪ፡፡
እምቧ በይ ላቱ ወይፈንን ምክሪ፣
እንደ በሬ አባቱ ላምን አስደፋሪ፣
ሙጃውን እያዬ እንዳያወልቅ ሱሪ፡፡

እምቧ በይ ላሚቱ ምከሪ ኮርማውን፣
ሻኛውን ቦጅሮ እንዲቋቋም ካራን፣
ተቀንድ ተሰክቶ የቦጫጨቀሽን!

እምቧ በይ ላሚቱ ይባርክሽ እግዜሩ፣
ወይፈን ጥጃዎችሽ ቀንድ የማይገብሩ፣
በሻኛ እሚጥሉ ኮርማዎች ይሁኑ፡፡

እምቧ በይ ላሚቱ!
ሚያዚያ ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.