አሳፋሪ ድርጊት ተፈጽሞብናል! – የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር (ጌጡ ተመስገን)

“ለሰው ልጆች በየቀኑ የምንሰጠው ክብር ለእኛም ይሰጠን” ~ ሠልፈኞች

በአሪሲ ዩኒቨርስቲ ኢንተርን ሀኪሞች መብታችን እንደ ሰው ይከበር ብለው ለጠየቁት ጥያቄ ይሄ በዱላ የተሰጠ መልስ ስብዕናቸውን የሚያሳንስና የሙያውን ክብር የሚያኮስስ ነው።
.
ከታች በምስል እንደምናየው ለታካሚዎቹ ደሙን የሚለግስን ሀኪም የመብት ጥያቄ ጠይቀሀል ብሎ በዱላ ደሙን ማፍሰስ ከግቢው አለቆች ዛሬ የተሰጠ በጣም አሳፋሪ መልስ ነው።
.
ይሄን ያዘዙ እና የፈፀሙ ግለሰቦች ምን እንደሚያስቡ አላውቅም። ለሰው ልጆች በየቀኑ የምንሰጠው ክብር ለእኛም ይሰጠን ላሉ ሀኪሞች የዚህ አይነቱ መልስ ማንነታቸውን አይመጥንም። ይህ ድርጊት መቼም እንደማይደገም ማረጋገጫ እንዲሰጠን እንጠይቃለን። የዛሬ ኢንተርኖች የጠየቃችሁት ጥያቄ እስኪመለስ ከጎናችሁ እስከ መጨረሻ እንቆማለን።
.
ዶ/ር ያሬድ አግደው ፤ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት
[ጉዳት የደረሰባቸው ሐኪሞች ምስል ፍቃድ በመጠየቅ የተገኙ ናቸው]

***

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር መግለጫ

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የህክምና ባለሙያዎች እንደማንኛውም ግለሰብና ባለሙያ ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የማቅረብ መብት እንዳላቸው በጽኑ ያምናል፡፡
.
ይሁንና በዛሬው እለት በአርሲ ዩኒቨርስቲ ያላቸውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለዩኒቨርስቲው አመራሮች ለማቅረብ የህክምና ጋወናቸውን አድርገው በመጓዝ ላይ በነበሩ ወንድና ሴት ኢንተርን ሀኪሞች ላይ የተፈጸመው ጥቃት በእጅጉ እንዳስደነገጠውና እንዳሳዘነው ማህበሩ መግለጽ ይወዳል፡፡ ይህ ጥቃት የተፈፀመው ደግሞ ህግና ስርዓትን እንዲያስከብሩ እምነትና ኃላፊነት በተሰጣቸው የህግ አስከባሪዎች መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን እጅግ አስደንጋጭና አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲውና በኦሮሚያ የፀጥታ አካላት እጅ በንፁሐን ሀኪሞች ላይ የተፈጸመውን ይህንን አሳፋሪ ድርጊት ለማጣራት ማህበራችን ለዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎች በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
.
የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በሀኪሞች ላይ የሚፈጸም ማንኛውንም ጥቃት በጥብቅ ያወግዛል፤ በህክምና ባለሙዎች ላይ በጸጥታ አካላትም ይሁን በማንኛውም አካል በኩል የሚፈጸም ጥቃትንም በጽኑ ያወግዛል!!! በአፋጣኝ እንዲቆምም ይጠይቃል፡፡ ይህ በህክምና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው የሠብዓዊ መብት ጥሰት በአስቸኳይ እንዲቆም ይጠይቃል!!!
.
በዚህ አጋጣሚም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ቢሮ፣ የዩኒቨርሲቲው፣ የጤና ጥበቃና የትምህርት ሚኒስቴር አካላትም ጉዳዩን አጣርተው አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠውም ጥያቄውን ያቀርባል፡፡

1 COMMENT

  1. እጅግ በጣም ያሳፍራል:: የተማረ ዜጋ እንኳን መብቱን የተነፈገባት አገር:: ቤት በዜጋ ላይ የሚፈርስባት አገር:: ምን አይነት ጨካኝ መንግስት ነው ያለን? የምንሰማው ሁሉ ይሰቀጥጣል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.