‹‹የሁለቱን ሕዝቦች ሰላም እያወኩ ያሉት ጡረታ መውጣት ያለበት ሐሳብ የያዙ ፖለቲከኞችና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡›› ደራሲና ከያኒ ደበበ እሸቱ

‹‹ሁለቱ ሕዝቦች ፖለቲከኞችና ልሂቃን የሚያራምዱትን ትርክት የሚያፈርስ አንድነት ያላቸው ናቸው፡፡›› አቶ አዲሱ አረጋ የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ከጥንት እስከ ዛሬ ልዩነት የሌላቸው አንድ ሕዝቦች እንደሆኑና ልዩነቱ ያለው በፖለቲከኞችና ኃላፊነት በጎደላቸው የዘመኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መሆኑን ደራሲና ከያኒ ደበበ እሸቱ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ደራሲና ከያኒ ደበበ እሸቱ ‹‹አማራና ኦሮሞ ትናንትም ሆነ ዛሬ ጠብ የላቸውም፤ የተጣሉት ፖለቲከኞችና ፌስቡከኞች ናቸው፤ሁለቱ ሕዝቦች ኢትዮጵያን ለመጠበቅ አብረው የሞቱ፣ አብረው የደከሙ፣ ተጋብተውና ተዋልደው የሚኖሩ ናቸው›› ብለዋል፡፡

ደራሲና ከያኒ ደበበ እንዳሉት የሁለቱን ሕዝቦች ሰላም እያወኩ ያሉት ጡረታ መውጣት ያለበት ሐሳብ የያዙ ፖለቲከኞችና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ‹‹የእያንዳንዳችን የዘር ሐረግ ቢቆጠር ከተወሰነ ትውልድ በኋላ ከኦሮሞነት ወደ አማራነት፣ ከአማራነትም ወደ ኦሮሞነት ይቀየራል፡፡ ምሁሮቻችን ፈረንጅ ለመለያዬት የጻፈላቸውን ታሪክ አንጠልጥለው ስለሚሄዱም ጭምር ነው ችግሩ የከፋው እንጅ አማራና ኦሮሞ የዚህች ሀገር ምሶሶ የሆኑና በጋራ ዋጋ የከፈሉ፤ በመካከላቸውም ቅራኔ የሌላቸው ናቸው›› ብለዋል፡፡ የቆዬ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ፖለቲከኞች ከመድረኩ ገሸሽ ቢሉና ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው ወጣቶች ወደፊት ቢመጡ ሁለቱ ሕዝቦች በቀደመ አንድነታቸው እንደሚቀጥሉም ነው ያብራሩት፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል›› በሚል በተረጎሙት መጽሐፍ ላይ እንዳስቀመጡት አንድ አደገኛ ቡድን የዘራው መጥፎ ተረክ ሕዝቦቹን የሚያቃቅር ሆኖ መቅረቡን ያስታወሱት ደራሲና ከያኒው ሁለቱ ሕዝቦች ሁለትም ለመባል የማይበቁ በብዙ መልኩ የተሳሰሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡ ‹‹ለተፈጠረው ችግር መጠየቅ ያለባቸው በየጥጉ የመሸጉ ፖለቲከኞች እንጅ ሕዝብ አይደለም፤ በሕዝቡ ዘንድም ጥል የለም፡፡ በግለሰቦች መካከል ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ እንጅ በሕዝቦቹ መካከል ልዩነት ስለመኖሩ እኔ አላምንም›› ነው ያሉት፡፡

ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ደግሞ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች የግንኙነት መድረክ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ጤናማና በመተሳሰብ የተሞላ መሆኑን ያመለከቱት ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ የጎንደር ወጣቶች ‹የኦሮሞ ደም የኛም ደም ነው!›፤ የኦሮሞ ወጣቶችም ‹ጣና ኬኛ!› ያሉት ግንኙነቱ ጥሩ ውጤት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ ፖለቲከኞችና ‹አክቲቪስቶች› ግን ግንኙነቱ ችግር እንዲገጥመው እያደረጉ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

የልዩነት ሐሳቡ በፖለቲከኞችና በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቢሆንም የልዩነቱ ፈጻሚ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ስለሆነ መድረኩ እንደሚያስፈልግ ነው ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ የተናገሩት፡፡ ‹‹ችግሩ የፖለቲከኞችም ሆነ የ‹አክቲቪስቶች› መንገድ እየዘጋና ድንጋይ እየወረወረ ያለው ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱን ምክንያታዊ ለማድረግና የተዛቡ ተረኮችን በማስገንዘብ ለማረም ደግሞ እንዲህ ያሉ መድረኮች አስፈላጊ ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና በሕዝብ ለሕዝብ መድረኮች የተጀመሩ የግንኙነት ዝግጅቶች ተቋማዊ ሆነው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል፡፡

የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ በባሕል፣ በአስተዳደር ወሰን፣ በቋንቋ፣ በሥነ-ልቦና፣ በታሪክና በማኅበራዊ መስተጋብር የቆዬ ትስስር ያላቸው ከመሆኑም በላይ የደም ትስስር ያላቸው ሕዝቦች እንደሆኑ ደግሞ ትናንት በአምቦ በተካሄደው የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ላይ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ተናግረዋል፡፡ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲና ለአንድነት በጋራ መታገላቸውን የገለጹት አቶ አዲሱ ‹‹ሁለቱ ሕዝቦች ፖለቲከኞችና ልሂቃን የሚያራምዱትን ትርክት የሚያፈርስ አንድነት ያላቸው ናቸው፡፡ ዓፄ ሠርፀ ድንግል ከቱርኮች ጋር ሲዋጉ የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች በጋራ ታግለዋል፡፡ በፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሎችም በጋራ ታግለው በጋራ ተቀብረዋል›› ብለዋል፡፡

ሕዝብ ለሕዝብ ተጣልቶ እንደማያውቅና የግጭት መሠረቶች ልሂቃን እንደሆኑ ያስረዱት አቶ አዲሱ ‹አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ ናቸው› የሚል የተሳሳተ ትርክት ቢነዛም በቆዬ ልማዳቸውና አብሮነታቸው ልዩነታቸውን ሲፈቱ የቆዩ ሕዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡ መሠል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ደግሞ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር ጠቃሚ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር አበባው አያሌውም በአምቦው መድረክ ላይ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ሚና በዘመናዊ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ምን እንደሚመስል አንስተዋል፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር አበባው እንዳሉትም የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች በሰጥቶ መቀበል መርህ ተዋሕደው ባሕልና ወግ እየተቀባበሉ ከ550 ዓመታት በላይ በአብሮነት አሳልፈዋል፡፡ ሁለቱም ሕዝቦች የደምና የጋብቻ ትስስር እንዳላቸው የተናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ‹‹ደም አንድን ሰው እንደ ወንዝ የትም ያደርሰዋል›› በማለት የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦችን አንድነት ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ የባሕል መወራረስና አንዱ በአንዱ ውስጥ የመገኘት መገለጫዎች ያሏቸው እንደሆኑም ነው ያብራሩት፡፡

ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና ለዘመናዊ ሀገር ግንባታም የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ የውጭ ኃይሎችንም በጋራ ተዋግተዋል ነው ያሉት፡፡ ‹‹የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ሲባል የሌሎችን አስተዋጽኦ ዝቅ ለማድረግ ሳይሆን በሕዝብ ብዛታቸው፣ በአሰፋፈራቸው፣ በመንግሥት ውስጥ በገዥነትና መንግሥቱን በማስተዳደር ትልቅ ሚና ስለነበራቸው ነው፡፡ ሁለቱ ሕዝቦች ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ የስበት ማዕከል ሆነው ያገለግላሉ፤ አንድነታቸው ሀገርን ያጠነክራል፤ ልዩነታቸው ደግሞ ሀገርን ያፈርሳል›› ነው ያሉት ምሁሩ በሙያዊ ትንታኔያቸው፡፡

በ1900 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሚኒስትሮችን በመሠየም ዘመናዊ ሥርዓት ስትገነባ የሁለቱ ሕዝቦች የተቀናጀ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሱት ተባባሪ ፕሮፌሰር አበባው ከድህረ ጣልያን ወረራ በኋላም ዓፄ ኃይለሥላሴ በዘመናዊ መልኩ ሀገሪቱን ሲመሩ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች ከፍተኛ ተዋናይ እንደነበሩ ነው ያስታወሱት፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰር አበባው የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ይበጃሉ ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦችም ሰንዝረዋል፡፡ የሁለቱ ልሂቃን ታሪክን በትክክለኛው መንገድና መስመር ለሕዝቡ እንዲያደርሱ፤ ወጣቱ በታሪክ ከመጋጨት የሚወሰደውን ወስዶ ራሱ አዲስ ታሪክ መጻፍ እንዳለበት፤ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ ፍጆታ በሚል ብቻ እውነታውን በማዛባት ሕዝብ ላይ ጫና ሊፈጥሩ እንደማይገባና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ከአዳራሽ ፍጆታ እንዲወጣ ሁሉም አካላት ማለትም ወጣቶች ከወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች ከፖለቲከኞች ዓመቱን ሙሉ የጋራ የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ግንኙነቱን የሚመራ ባለቤት ተቋም መኖር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በአምቦው መድረክ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮነን እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺመልስ አብዲሳም የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦችን አንድነት የሚጠናክረው መድረክ ተቋማዊ መሠረት ኖሮት እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመው የ‹ኦሮማራ› መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ጥቅምት 2010ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ነበር፡፡

በአብርሃም በዕውቀት
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 14/2011ዓ.ም (አብመድ)

2 COMMENTS

  1. ጥሩ አስተያት ነው ። ችግሩ ስንተች እራሳችንንም ወደ ውስጥ ለማየት ቢያንስ የሞራል ወኔው ከማጣታችን ላይ ነው ። ከገዥዎች ባሻገር ያለውን የአገር መከራና ውርደት ምክንያት ካነሳን እጅግ ከጥቂቶቹ በስተቀር ከደሙ ነፃ ነኝ የሚል ውሸታም ነው ። ስንቱ የኪነ ጥበብ ሰው ነኝ ባይነው ለመጣው ገዥ ሁሉ እያዠረገደ መከራናና ውርደቱን እንዲራዘም ያደረገ? ሁንስ ገና የዴሞክራሲው አቅጣጫ ባለየበት አርቲስት ደበበን ጨምሮ ስንቱ የአርት ሰው ነኝ ባይ ነው ፖለቲከኞችን ማምለክ የሚቃጣው ? ስንተች እራሳችንም አንርሳ !

  2. ጋሼ ደበበ እባክህ እንዳማረብህ ብትኖር ይሻልሃል:: ድሮ በትቪ ዜናህ በሃገር ፍቅርና ብሄራዊ ቲያትር ቤቲች አስተዋዋቂነት ጥሩ ገጽታህን ይዘህ እንዳልነበር የደርጉ አጫፋሪ ሆነህ በመጽሄት ዝግጅት ስታወድሰው ከልቤ ወጣህ:: አሜሪካ መጥተህ በቪኦኤ ለህዝባችን መልክት ስትባል “እዚያው አጠገቡ ነኝ” ብለህ የነበረውን ግፍ በጥበብ እንኳ እንደመሰሎችህ ለመናገር ተሸበብህ::ያ ድንቅ ዘምዴ ነው የምትለው ወጋየሁ ንጋቱ ስለአንተ ያለውን ባለቤቱ አምሳለን ዋቢ በማድረግ ብዙ ማለት ይቻላል ስለማያንጽ ይቅር:: በቅንጅቱ ብዙ ለመሳተፍ ሞክረህ ወያኔ እየደበደበ ሲያሰቃይህ ” መንግስት አሸባሪ ካለው ጋር ለምን ቆምኩኝ” ብለህ ኢንተርቪው ሰጠህ:: ቅንጅቱን ከበታተኑትም መካከል ሆንክ:: ያ ሁሉ አልፎ በጎ ለውጥ በፈጣሪ ፈቃድ በወጣቶቹ መስዋእትነት ሲጀመር በታላቅነት ማስታረቅ ሲገባህ “በልተናቸው እንቀደስ” በክፉ ቅስቀሳህን አዘንኩኝ:: ከሁሉ የባሰው ደግሞ ያ ቀልማዳ ሃይሌ ገብርስላሴና ወዳጄነህ መሃረነ የሚሉት ዶክተር “የአስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ይቀጥል ኢንተርኔት ይታገድ” ሲሉ የነበረውን ዛሬ በሌላ መልኩ ስታውገረግር ዝም ማለት አልችልም:: በድሮ በጎ ምልከታ የምናውቃችሁ ከያኒያን “መንኛለሁ” ብሎ ዘፈኔ ለምን ተነካ ያለውን ሙሉ ቀንን ይጨምራል ከመነናችሁ ከልብ ይሁን ያለበለዚያ ወደክፋቱ ፍልሚያ ከገባችሁ ይለይላችሁና በደንብ እንፋለም::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.