ብሪታኒያ ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታካሂደው ምርጫ የ15 ነጥብ 5 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ እንደምታደረግ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብሪታኒያ ኢትዮጵያ በቀጣይ የምታካሂደው ምርጫ ግልፅ፣ ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚያግዝብ የ15 ነጥብ 5 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ እንደምታደረግ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀረሚ ሃንት አስታወቁ።

ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀረሚ ሃንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ባለው 26ኛው ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ወቅት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቴ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ ገፆች፣ ብሎጎች እና ጋዜጣዎች እንዲከፈቱ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን እያሰፋ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጀረሚ ሃንት ተናግረዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት በዓለም ላይ ከነበራት ደረጃ በ40 ደረጃዎች ማሻሻል ችላለች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ይህም ትልቅ ስኬት መሆኑን እንስተዋል።

አሁንም ቢሆን በፕሬስ ነፃነት ላይ የሚሰሩ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው እና የብሪታኒያ መንግስትም በዓለም ዙሩያ የፕሬስ ነፃነትን ለማረጋገጥ ለሚከናወነው ስራ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ኤምባሲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ለ100 ጋዜጠኞች የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ በዛሬው እለትም አዲስ የድጋፍ ማእቀፍ ይፋ አድርገዋል።

በድጋፉም ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታካሂደው ምርጫ የሚውል የ15 ነጥብ 5 ሚሊየን ፓውንድ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

የድጋፍ ማእቀፉ ውስጥም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣይ ነፃ እና ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ ማካሄድ እንዲችል ማገዝን ያካተተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

EBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.