እስቲ ትንሽ እሳት ልጫር – ግርማ ካሳ

በዳያስፖራ በርካታ ድርጅቶች አሉ። የብዙ ድርጅቶች ስብስብ የሆነው ሸንጎ፣ ግንቦት ሰባት፣ በነ ሌንጮ ለታ የሚመሩት ኦዴፍ፣የኢትዮጵያ ወጣቶች ንቅናቄ፣ ግሎባል አላያንስ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያዊነት ሲቪክ ማህበር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ኮንግረስ፣ ማርች ፎር ፍሪደም፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪት ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር፣ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች፣ የሰማያዊ ድጋፍ ድርጅቶች፣ የአረና ድጋፍ ድርጅቶች፣ ጋሻ ለኢትዮጵያ፣ ኢሕአፓ … እረ ስንቱን እንዘርዝ። ሁሉም በኢትዮጵያ ለዉጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ። ሁሉም በፊናቸው የድርሻቸውን ለመወጣት እየሞከሩ ነው። እያታገልን ነውም ይላሉ።

ታዲያ እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች እያሉ እንዴት የዉጭ ምእራባዉያን መንግስታትን ለማስመን አልተቻለም ? እንዴት ዌንዲ ሸርማን በአዲስ አበባ የሰጠችውን «ኢሕአዴግ ዴሞክራቲክ ነው» የሚለውን አስተያየት ልትሰጥ ቻለች ?

ዌንዲ ሸርማንን ተቃውመን ሰልፍ ወጣን። ግን ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ሴትየዋ ይቅርታ እንድትጠይቅና የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ማስተካከያ እንዲይደርግ፣ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ አንዳንድ ድርጅቶች ደብዳቤ አስገቡ። ጭራሽ እንደዉም ዌንዲ ሸርማን የተናገረቸው የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን አቋም የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ተነገረን። ሰልፍ መዉጣታችንን፣ ደብዳቤዎቻችን ከቁም ነገር የቆጠረው የለም።

እንግዲህ መሰረታዊ ጥያቄ መጠየቅ አለበት። እርሱም «እንዴት ከላይ የጠቀስኳቸው እነዚያ ሁሉ ድርጅቶች እያሉ ፣ ኢሕአዴግ በዲፕሎማሲ ረገድ አሸንፎ፣ በዉጭ ያሉ ኃይላትን ከጎኑ ሊያሰለፍ ቻለ ? » የሚለው ነው።

ሶስት ምክንያቶች አሉ ብዬ ነው የማስበው፡

1. «ጥያቄዎቻቸው ተመሳሳይ ሆኖ እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች ካሉ፣ ኢሕአዴግ ቢቀየርም ፣ ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ እርስ በርሳቸው ሊጋጩና አገሪቷን ወደ ከፋ ደረጃ ሊወስዷት ይችላሉ ። ስለዚህ የተሻለ አማራጭ እስኪመጣ ከኢሕአዴግ ጋር መቀጠል ይሻላል» ከሚል፣ ምእራባዉያን፣ ተቃዋሚዎች ነን የሚሉትን ብዙም ለመስማት ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል። ሊፈረደባቸው አይገባም። ማንን ሰምተው፣ ማንን ሊተዉ ነው ? ድርጅቶቹን ሁሉ ያቀፈ፣ ሁሉን በሚያስማማ መልኩ አንድ አማራጭ ኃይል ቢኖርና በአንድ ድምጽ ሁላችንም ብንናገር ኖሮ፣ ተሰሚነት እናገኝ ነበር። ዛሬ ኦባንግ ሜቶ፣ ነገ አል ማርያም፣ ከዚያ ሸንጎ፣ ከዚያ ግንቦት ሰባት ….ይጽፋሉ። እመኑኝ የማናችንንም ደብዳቤ በዉጭ ጉዳይ መስሪያ የሚያነበው የለም። ግን አንድ ሆነ፣ በአንድ ድምጽ ብንቀርብ፣ ያኔ እንከበራለን። አንድ ሆነን ሰልፍ ብንጠራ፣ ያኔ ከአንድ ሺህ ያነሰ ሳይሆን 20፣ 30፣ 40 ሺዎች ዲሲ በሚደረግ ሰልፍ ሊወጣ ይችላል።

ስለዚህ ቢያንስ በሚያስማሙ ጉዳዮች ዙሪያ ፣ ድርጅታዊ ነጻነታችንን ጠብቀን አንድ የጋራ ግብረ ኃይል፣ ወይም አማራጭ ኃይል መፍጠር እንችላለን። እንደዉም ሌሎች ትናንሽ ድርጅቶችን እንኳ ትተን፣ ሸንጎ፣ ኢሕአፓ፣ የሽግግር ምክር ቤቱ፣ ግንቦት ሰባት-አርበኞች፣ ኦዴፍ እና የአንድነት/ሰማያዊ ድጋፍ ድርጅቶች በጋራ የማይሰሩበትም፣ የጋራ የዲፕሎማሲ ኮሚቴ የማይኖራቸው ምንም ምክንያት የለም። እስከ አሁን ብዙ እንደተሞከረ አወቃለሁ። ግን ለምን የነዚህ ድርጅት መሪዎች አብረው ሊሰሩ ፍቃደኛ እንዳልሆኑ አይገባኝም። በየቦታው ግን አንድ እንሁን ብለው ሲሰብኩ ይሰማሉ።

2. የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ሴንስ የሚሰጡ አይደለም። አሜሪካ ፣ ወይንም አዉሮፓ የልማት እርዳታ አይስጡ የሚል ጥያቄ ብዙ የሚያስኬድ አይደለም። እርዳታው በከፊልም ቢሆን ሕዝብ ጋር የሚደርስ እንደመሆኑ ለ«ልማት» የሚሰጥ እርዳታን መቃወም በነጮቹ ዘንድ ተሰሚነትን ያሳጣናል። ተገቢም ነው ብዬ አላምንም። ይልቅ፣ የሚሰጠው እርዳታ በቀጥታ ወደ መንግስት ካዝና የሚገባ ሳይሆን፣ ወደ ልማቱ እንዲሄድ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲዉል ግፊት በማድረግ፣ ከኢትዮጵያ ገንዘቦቹ መመዝበራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በማሳየት በማጋለጥ፣ የድርሻችንን መወጣት እንችላለን። ባለስልጣናት ላይ ትራቨል ባን ማድረጉ የመሳሰሉት ላይ ማተኮር እንችላለን። አብዛኛው የአገዛዙ ባለስልጣናት አንዳንዶቹ በዘመዶቻቸው ስም፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠር ገንዘብ ከፍለው ቤት ፣ ቢዝነስ የገዙ አሉ። ያንን በመከታተል ዘራፊዎች ተጠያቂ እንዲሁኑ ማድረግ እንችላለን። ለእርዳታ የሚሰጠው ዶላር ተመልሶ እንደሚወጣ ካሳየን፣ ብዙ ልንሰራ እንችላለን።

ስለዚህ የምእራባዉያን መንግስታት ከምናስበው በላይ ትልቅ ሌቨሬጅ አላቸው። ግን የምናቀርባቸው ጥያቄዎች በተቻለ መጠን ሊቀበሉን የሚችሉ ጥያቄዎች መሆን አለባቸው።

3. አሜሪካኖች በዋናነት ኢሕአዴግን የሚደገፉት ፣ ኢሕአዴግ ራሱን በ «ጸረ-ሽብርተኝነት» ትግሉ ዋና አጋር አደርጎ በማቅረቡ ነው። የአርባ ምንጭ አይሮፕላን ማረፊያን አሜሪካኖች ለድሮን እንዲጠቀሙበት ተደርጓል። አልሻባብን ለመምታት አሜሪካኖች ከኢትዮጵያዉያኖች ጋር አብረው እየሰሩ ነው።

ስለዚህ ተቃዋሚዎች እነርሱም ከኢሕአዴግ የበለጠ ጠንካራ የጸረ-ሽብርተኝነታ አቋም እንዳላቸው ማሳየት መቻል አለባቸው። ከኢሕአዴግ የበለጠ ድህረ -ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ በጸረሽብርተኝነቱ ትግል ላይ አጋር ብቻ ሳይሆን የአካባቢ መሪ እንደምትሆን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይሄም ነጮችን ብቻ ለማስደሰት ሳይሆን፣ መሆንም ስላለበት ነው። እንደዉም ኢሕአዴግ የሚያራምደው ፖለቲካ፣ በአካባቢው አለመረጋጋትን ከመፍጠሩም የተነሳ ለሽብርተኘንት አመች ሁኔታ ሊፈጠረም እንደሚችል ማሳይት ይቻላል።

ለምሳሌ ከዘጠኝ አመታት በፊት የተደረገው የመጀመሪያ የሶማሊያ ጦርነት ነው አልሻባብን የፈጠረው። አልሻባብ የተፈጠረው፣ የጠነከረውና ያደገው በኢሕአዴግ ነው ማለት ይቻላል። ያኔ ለአልሻባብ መጠናከር ኢሕአዴግ እገዛ እንዳደረገው፣ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው በዘር ላይ የተመሰረተ አፈና፣ አገሪቷን ወደ ትልቅ ቀዉስ ሊከታት እንደሚችል በማሳየት፣ በኢትዮጵያ ዉስጥ መረጋጋት ከጠፋ ደግሞ ፣ አንጻራዊ መረጋጋት ያገኘችዋ ሶማሊያ ተመለስ እንደምትበጠበት፣ ሱዳንም ዉስጥም ችግር እንደሚፈጠር በማስረዳት፣ የኢሕአዴግ ፖሊሶዎች በሽብርተኘንት ረገድ፣ አደገኛ ናቸው ብለን ማሳመን እንችላለን።

አሜሪካኖችና አዉሮፓዉያን ምስራቅ አፍሪካ ከሽብርተኝነት ነጻ እንድትሆን ከፈለጉ፣ በዋናናት በአዲስ አበባ የስርዓት ለዉጥ መምጣት እንዳላበት እንዲያምኑ ማድረግ ይቻላል።

ለማጠቃለል ይሄን እላለሁ። አሳማኝ መከራከሪያዎችን በመያዝ፣ በአንድ ድምጽ በመናገር፣ ከስሜት በጸዳ መልኩ የዲፕሎማሲ ትግል ካደረግን ያለ ምንም ጥርጥር የምራባዉያንን ድጋፍ ማግኘት እንችላለን። ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ሕዝብ ጨምሮ የተጠላ ነው። እየኖረ ያለው በዉጭ ድጋፍ ብቻ ነው። በዉጭ ያለነው በዚህ ረገድ ተባብረን፣ ሳንታክት ከሰራን ጥሩ ዉጤት ሊገኝ ይችላል።

እንግዲህ በየጊዜው በመግለጫ፣ በደብዳቤ፣ በስብሰባዎች ወዘተረፈ ያሰለቹን ድርጅቶች፣ መግለጫዎቻቸውን እና ደብዳቤዎቻቸዉን ለጊዜ ሳጥናቸው ዉስጥ አስገብተው፣ በአጭር ጊዜ ዉስጥ እርስ በርስ በመነጋገር አንድ ጠንካራ አማራጭ ኃይል እንዲያቋቋሙ እመክራለሁ። ያንን ማድረግ ካልቻሉ ግ ይቅርታ ይደረግልኝና ዉጭ አገር ያሉ ስብስቦችና ድርጅቶች በሙሉ በቀይ ማርከር እሰርዛቸዋለሁ። ጊዜ ወርቅ ነው። ለማይረባ ወሬና ጩኸት ጊዜ የምናጠፋበት ምንም ምክንያት የለም። 24 አመታት አወራን። ከአሁን በኋላስ በቃ !!

Comments are closed.