ከጠ/ሚ/ሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ጋር! (ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ )

ትናንት ምሽት ከጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ከመላው ዓለም ለአንድ ጉዳይ ከተሰባሰቡ ወገኖች ጋር አብረን አምሽተናል።

ይህ የሆነው ጠ/ሚ/ሩ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ጉሌርሞ ካኖ የዓለም የፕሬስ ነፃነት የሽልማት ስነ ሥርዓት ላይ ለሚያደርጉት የእራት ግብዣ ለመታደምና ሃሳብን በመግለጽ ነፃነት ዙርያ ለመነጋገር ነበር። መርሐ ግብሩም በመልካም ሁኔታ ተጠናቋል።

በአጋጣሚው ከጠ/ሚ/ር ዐብይ እና ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር አቶ ገዱ ጋር ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሃሳብ ለመለዋወጥ ችያለሁ። የዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሁልጊዜ አይገኙምና በተቻለኝ መጠን ማንሳት አለብኝ ብዬ የምላቸውን ከሙያ ጋር የተያያዙና አገራዊ ጉዳዮች ለሁለቱም ከፍተኛ የአገር መሪዎች አንስቻለሁ።

ሁለቱም ትኩረትና ጊዜ ሰጥተው አድምጠውኛል። ነገሮችን በተቻላቸው አቅም ለመፍታት እየጣሩ እንዳለ ገልጸውልኛል። አያይዘውም በእስር ስላሳለፍነው ጊዜ የሚሰማቸውን ጥልቅ ስሜት አጋርተውኛል።

ጠ/ሚ/ሩ ፈገግ ካሰኙኝ ቀልዶች ጋር ስለብዙዎቻችን ገፋ አድርገው እንደሚያውቁ የተገነዘብኩባቸው ሃሳቦችን አንስተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚ/ር አቶ ገዱ፤ ልቤን በነካኝን አባታዊ ትህትና የተወሰኑ ሃሳቦች ተለዋውጠናል። በእርግጥ ጊዜው አጭር እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ቢሆንም በቂ፣ መሰረታዊና ገንቢ ነበር ብዬ አምናለሁ።

ለማጠቃለል ያህል በግሌ ዛሬን ሳይሆን ትናንትን ማስታወስ እፈልጋለሁ። በእነዚያ ቀናት ጭቆና ተደርምሶ ነፃነት እውን የሚሆንበትን ቀን እንናፍቅ ነበር። በእነዚያ ቀናት በመላው ዓለም ያላችሁ ኢትዮጵያውያንና ለሰብዓዊ መብት የሚታገሉ የሰው ዘሮች አጋርነታቸውን ያሳዩን ነበር። ያኔ የእናንተ ቁርጠኛ ሆኖ ከጎናችን መቆም ነው ይህችን ቀን የፈጠራት። በጋራ እስከቆምን ድረስ ነገ የተሻለ የማይሆንበት ምንም ምስጢር የለም!

ዛሬን ሳይሆን ትናንትን አስታውሳለሁ፤ ይልቁንም ለነገ ማሰብን እመርጣለሁ። ለዚያ ነው ነገ የተሻለ ቀን ይሆናል የምለው። ይህን ስልም እንደአገር የተጋረጡብን ተግዳሮቶች ከባድ መሆናቸውን በመገንዘብ ነው። እርግጠኛው ነገር ይህች ምንም ቢሆን ኢትዮጵያ ናትና በጋራ ከቆምን በቀላሉ እንወጣዋለን።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.