የአንድነት ፓለቲካ “አማራ ገዳይ” ይሆን?

ይህን ፁህፍ እንድሞነጫጭር ያነሳሳኝ የፌስቡክ ውዳጄ የሃይለ ገብርኤል ‹የጎሳ ፖለቲካ በሕግ እንዴት ይታገድ?› የሚለው ምፀታዊ መጣጥፍ ነው:: የሃይለን ሃሣብ በሃሣብ ለመሞገት ብመርጥም ለሰጠው የግል አስተያየቱ ግምት እየሰጠሁ ሃሣቡን በሃሣብ በመሞገት በክብር አለመስማማቴን አቀርባለሁ::

ውዳጄ ሃይለ ገብርኤል ባቀረበው ግራፊክ ምስል ላይ የአንድነት ፓለቲካ አማራ ገዳይ መሆኑን አመላክቷል:: ይህ ስህተት ነው:: ምክንያቱም የአንድነት ፓለቲካ ‘’የአማራገዳይ” ከሆነ የአማራ ‘’መዳኛ’’ የጎሣ ፓለቲካ ርዕዮትና “የጎሣ ፌደራሊዝም” ነው ሊሉን ነው። ግን ለምን?

1. የአንድነት ፓለቲካ “አማራገዳይ” ከሆነ አማራው የሞተው ኢትዮጵያ ህልውናዋ ገቢር ከሆነበት ብዙ ዘመን በፊት መሆኑ ነው:: ስለዚህም በነባሮቹ የአሃዳዊ ንጉሣዊ ሥርዐቶችና ከወታደራዊው የደርግ ፋሽስታዊ ሥርዐት በፊት መሆኑ ነው:: አፄ ቴዎድሮስ: አፄ ዩሐንስም ይሁኑ አፄ ሚኒሊክ የአንድነት ወይም የዜግነት ፓለቲካ አራማጆች እንጂ “አማራ ገዳይ” እና የጎሣ ፓለቲካ ምርኮኞች አልነበሩም::

2. የአንድነት ፓለቲካ ኢትዮጵያዊነት ወይም የሲቪክ ወይም የዜግነት ብሔረተኝነት ፓለቲካ ማለት ነው:: የዜግነት ፓለቲካ “አማራ ገዳይ” ነው ካልከን አማራ የሞተውና የአማራ ገዳዩ” እራሱ አማራው ነው ልንል ነው:: አማራ የሞተው እራሱ ባቆሰለው የራሱ ቁስል ሊሆን ነው (self-inflicted action as a product of poor judgement & choices):: ይህ ደግሞ እራስን መግደል እራድን ማዋረድ (self-abasement) መሆኑ ነው::

3. አማራ በራሱ ሕብረ-ብሔራዊ ቅምር (multi-national Identity arrangement)ነው::

4. የአማራ ሕዝብን እንደ ሕዝብ በጠላትነት የፈረጀው የጎሣ ፓለቲካ ርዕዮትና “የጎሣ ፌደራሊዝም” መንግስታዊ ቅርፅ “አማራ” የሚል ምናባዊ ምስልን አስቀምጦ ሊበትን የተከሰተው ኢትዮጵያዊነትን፤ ኢትዮጵያዊነትንም ለማጥፋት የዚህን የዜግነትና የማንነት ፓለቲካ ዋነኛ ማህበራዊ መሠረቱ አማራ መሆኑን በመገንዘቡ ነው:: እንደሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የአማራ ስቃይና መከራ ምንጩ ይህ የጎሣ ፓለቲካ ርዕዮትና “የጎሣ ፌደራሊዝም” እንጂ የእንድነት ፓለቲካ አይደለም:: የአንድነት ፓለቲካ “የአማራ ገዳይ” አድርገን ከሣልነውና “የጎሣ ፓለቲካ አዳኝና መትረፊያችን ነው” ካልን ከአማራ ገዳይ ከሆነው የጎሣ ፓለቲካ ጋር ፍቅር ይዞናል ማለት ነው (Stockholm Syndromes):: የጅብ ጥቃትን ጅብ በመሆን እታደጋለሁ ብላ እንደምትሸልለው የዋህ አህያን ልንሆን ነው::

5. የአንድነት ፓለቲካን የፓለቲካ ድርጅት ፓለቲካዊ ርዕዮተዓለም መሠረት እንጂ የድርጅቶቹ የፓለቲካ ፕሮግራም ወይም የግል ንብረት አይደለም:: ችግሩ እዚህ ላይ ነው:: ወታደራዊው ድርግ በዜግነት ፓለቲካ ወይም ብሔረተኝነት ያምን ነበር:: ይህን የዜግነት ፓለቲካ መምረጥ ፋሽስታዊ ደርግን ማሞገስ አልነበረም:: በመላው ዓለም ለተፈፀሙ ናዚያዊና ፋሺስታዊ ጭፍጨፋዎች የተተገበሩት በዜግነት ፓለቲካ ሣቢያ ሣይሆን በነዚህ ፓለቲካዊ ሥርዐቶች ምክንያት ነው::

6. አማራ እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የግፍ ፅዋ የተጎነጨው በአፓርታይዳዊ ወያኔያዊ ሥርዐት ወይም በጎሣ ፓለቲካ መንግስታዊ ርዕዮት ሳቢያ ነው::
7. ርዕዮተዓለማዊ ፅንሠ ሃሣቦቻችን ድርጅታዊ መሠረተ ሃሣቦችን ይወልዳሉ:: አማራው የእንድነት ወይም የዜግነት ፓለቲካን ተጠይፎ በወያኔያዊው የጎሣ ፓለቲካ ርዕዮተዓለማዊ ፅንሠ ሃሳብ ይደራጅ ከተባለ በገዳዩ ርዕዮት ይገነዝ ማለት ነው:: ችግሩ የአማራ መደራጀቱና ጥቃቱን መመከት ጉዳይ ሣይሆን አማራው ተፈጥሮው ከሆነው ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ወይም የአንድነት ፓለቲካ ውጭ መደራጀት አደጋ ነው ማለታችን ነው:: አማራ ደሴት አለመሆኑንና በኢትዮጵያዊ ማንነቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚኖረው በአንድነት ፓለቲካ መከታነት መሆኑን ማስተዋሉ ይበጃል:: የአንድነት ወይም የዜግነት ፓልቲካን አማራ ይቃወማል ካላችሁን አማራ ነባራዊ ፓለቲካውንና የፓለቲካ ሲስተሙን ሣይሆን እራሱን ይቃወማል እያላችሁን ነው:: በጎሣ ፓለቲካ የተቃኘ አማራዊ ማንንት ኢትዮጵያዊ ማንንትን ይተካል ካላችሁን አማራነትም የአንድነት ፓለቲካ ማንነት ስለሚሆን አማራነትም እያደር የአማራ “ጠላትና ገዳይ” ሊሆን ነው::

መፍትሄው!

1. እማራ መብትና ነፃነቱን እንደሌሎቹ ኢትዮጵያውያን በትግሉ ለመጎናፀፍ በአማራነት ተሰባስቦ በዜግነት ፓለቲካ ተቃኝቶ ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ተቀናጅቶና የሕብረት የአንድነት ግንባርን ፈጥሮ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን ማነፅና የሕግ የበላይነትን ማስፈን ብቻ ነው::

2. በአማራነት ለኢትዮጲያዊነት ግቡ ሲደራጅም ይህን ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትና የሕግ የበላይነትን ለማንገስ ከዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ጋር ልዩነትን አቻችሎ በጋራ በመቆም ነው:: ለአደረጃጀቱም የዜግነት ፓለቲካን በማስረፅ ለሞክራሲያዊ ሥርዐት መፋለም ነው::

3. ሕብረ-ብሔራዊ ስነልቦና ያለውን አማራ በጎሣ ፓለቲካ ነክሮ “መዳኛህ” ነው ማለት ገዳዩ ፊት አቅርቦ “አዳኝህ ነው” ብሎ መስበክም ነው::

4. አማራ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ አይገለፅም (synonymous):: አማራና እትዮጵያዊነት ሥልቻና ቀልቀሎ ናቸው:: “አማራን የበደለችው ኢትዮጵያ: የተበደለውም ኢትዮጵያ ነኝ በማለቱ ነው” የምትሉን “አማራውን የበደለው ነባር ሥርዐት ሳይሆን እራሱ ነው” እያላችሁን መሆኑን ብታስተውሉ መልካም ነው::

5. ከነቆራና ጭቅጭቅ ውይይትን በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን ከሚናፍቁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር እንደ ድር ማበር ነው:: በፓለቲካና የሃሳብ ልዩነትን በመቀበል ነው::

የጎሣ ፓለቲካ መታደግ!

ሃይለ ገብርኤል በፁህፉ ላይ ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሆኑ ግዴታዎች መድለውኛል:: ይህ ድግሞ የፓለቲካ ድርድርን ሣይሆን ቀኖናዊ ግትርነትን እምልካች ናቸው:: ለምሳሌ የጎሣ ፓለቲካ ከመታገዱ በፊት “ሕገ-መንግስቱ ይሻሻል” ይለናል:: ሕገ መንግስቱ ሳይሻሻል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቀልድ እንደሆነ ይገባናል:: የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ከታገደ በዚህ ፓለቲካ ላይ ጥገኛ የሆነው ሕገ መንግስት ተሻሻለ ማለት ነው:: ሌሎች ያቀረባቸው ግዴታዎች እንደ የጥላቻ ሃይሎች ትርክትና ፕሮፓጋንዳ ይቁም: የዜጎች መፈናቀልና መንግስት ሥርዐትን ሲያስከብር ይሚለን ሊገቱ የሚችሉት በሕግ መንግስታዊ ማሻሻያ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን በመገንባት ነው:: የችግሮቹ ምንጭ የጎሣ ፓለቲካ መፍትሄውም የሕግ የበላይነት የሥፈነበት እንዲሁም የሐግረ-ኢትዮጵያ ገዢና የበላይ ሕግ ሲሆን ነው::

ማጠቃለያ:

የጎሣን ፓለቲካ በሕግ መታገድ መንግስታዊ ሣይሆን ሕዝባዊ ጥያቄ ነው:: ጠያቂው የሕዝብ ልጆችና ሕዝብ ምላሽ ሥጪውም መንግስት ነው:: ሃይለ ገብርኤልም ይሁን ከዚህ የይታገድ ጥያቄ በተቃራኒ የተቃውሞ ጎራ የቆሙ ያቀረቡት ግዴታዎች ለመንግስት ሣይሆን ለችግሮቻችን ምክንያት የጎሣ ፓለቲካ መሆኑን ከተገነዘቡ ዜጎች ጋር ነው::
‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ የሚለውን ዘመቻ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ መቀላቀሉ ይበልጥ የሚጠቅመው በጎሣ ፓለቲካ ሠለባ የሆነውን አማራና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን እንጂ መንግስትን እይደለም:: ለዚህ ነው ይህን ዘመቻ መቃወም ገዳይን ማፍቀርና የድመትን እፍንጫ ማሽተት ነው ያልነው::

‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ የአንድነት የፓለቲካ ድርጅቶች ጥያቄ ብች ሣይሆን ይጎሣ ፓለቲካ ተጠቂው ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥያቄ ነው:: የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ ጥያቄን ‘የናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ’ በሚልና “የአንድነት የፓለቲካ ድርጅቶች ዘመቻ ነው” በሚል ሰበብ ማጥላላቱና ማራከሱ ‘ባሏን የጎዳች መስሏት ብልቷ ውስጥ እንጨት እንደደነቀረችው’ ሞኝ ሴት መሆን ነው::

‘የጎሣ ፓለቲካ በሕግ ይታገድ’ ዘመቻን መቃወም እትዮጵያዊ ወይም የዜግነት ፓለቲካን መቃወም ነው:: የዜግነት ፓለቲካን መቃወምም የአማራን ህልውና አደጋ ላይ መጣልና የአማራን ኢትዮጵያዊነት ወይም አማራን መቃወም ነው::

ማሳሰቢያ:-

አማራን ብተመለከተ ምላሽ መስጠት የፈለኩት ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ በመሆኗ ሣይሆን ፀሃፊው ሃይለ ገብርኤል በአማራ ሥም በመፃፋቸው መሆኑ ይታወቅልኝ!!

ለረጅሙ ፁህፍ ይቅርታ ጠይቃለሁ!!
ምላሽ የሰጠሁት የፀሃፊው ሃይለ ገብርኤል ሊንክ በኮሜንት ክፍል ተቀምጧል።

#HaileGebreal

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.