አደገኛው የአማራ ፖለቲካና የአብይ የሰሞኑ ንግግር (ሰርፀ ደስታ)

 

 • የዘረኝነትና ጥላቻ ፖለቲካ አማራንም እንደ ኦሮሞ ከማንነቱ እያመከነው ይመስላል!
 • አምባቸው በአምቦ የአዲስ አበባን አስመልከቶ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን ማስከበር የእኛም ድርሻ ነው ያለው ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? የኦሮሚያን አለ እንጂ የኦሮሞን አልወጣውም፡፡ አምባቸው ይሄን ወጥቶ ሲያብራራ አላየሁም፡፡
 • “አምቦ ላይ ስኳር የጫነ መኪና አስቆምክ ብለን በመሳሪያ አንገድልም ” ዜጎች እየተገደሉ ስርዓት እየጠፋ ነው ሲባል ከአብይ የተሰጠ አስገራሚ ማብራሪያ ነበር፡፡ አብይ ሆይ አምቦዎች ሕገወጦች የከለከሏቸውን መብት እንጂ ሕግ ጥሰው ይሄን አላደረጉም፡፡ የአረመኔውን ኦነግ ለመሸፈን ያልተጠየከውን ቦታ ሕዝብ ሥም ተጠቀመህ ኦሮሞ ውስጥ አትወሸቅ፡፡ ከዚህ በፊት ከሱሉልታ መንግስታችን ተነካ ብሎ ሕዝቡ ተነቅሎ እየመጣ ነበር ያልከውንም አስታውስ፡፡
 • የኢዜማ በብርሀኑ መመራት ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል? በኢትዮጵያዊነት ደረጃ ብርሀኑ የአስተሳሰብ እጥረት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ብርሀኑ ጥሩ አዲስ አበቤ ሊሆን ይችላል ግን ለመሪነት የሚያበቃ ኢትዮጵያዊነት ቁጭትና እልህ ያለው አይመስለኝም፡፡
 • ሙስጠፌ ኡመር አሁን ከምናየው ለዜጎች መብት መከበር ጥሩ መሪ ነው፡፡ የሙስጠፌ መሠረታዊ ፍልስፍና እንጂ ለማስመሰል አይደለም፡፡ ታላቅ ቁጭትም የሚነበብበት ይመስላል፡፡ በአፋርና ሱማሌ አዋሳኝ ያለውን ጉዳይ በስሜታዊነትና በጉልበት ሳይሆን በአወዛጋቢ ቦታዎች ላይ የሚኖረው ሕዝብን መብት በጠበቀ መልኩ እንዲፈታ እንዲዘራ ሙስጠፌንና ቡድኑን በዚህ አጋጣሚ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ከአፋርም ወግን እንዲሁ፡፡ሰሞኑን ከሚራገቡ ነገሮች ነውና፡፡

ከዚህ በፊት ስጋቴን ግልጫለሁ፡፡ አሁን የምናየው የአማራ ፖለቲካ በብዙ መልኩ ኦሮሞን ከማንነት አውጥቶ የደሃ አስተሳሰቦች ባሪያ ያደረገውን የኦሮሞ የ50 ዓመት ፖለቲካ ይመስላል፡፡ አማራን እንደ አማራ አደራጅቶና ራሱን መከላከል በሚል ስልት የሕዝቡ እሴቶችና ልዕልናውን ጠብቀው የኖሩ በራስ የመተማመን ስሜቱን እየሸረሸሩ ያሉ የአልቃሻነትና የተበደልኩ ኡኡታ በእጅጉ አሳሳቢ ናቸው፡፡ በአንድ መልኩ የአማራን ልዕልና እናስጠብቃለን እያሉ በሌላ መልኩ ግን የኖረ ማንነቱን አስጥሎ የመከነ ማንነት የሌለው የባዘነ እየተደረገ እንደሆነ ይታያል፡፡ አማራ በአለፉት 28 ዓመታት ምን እንደደረሰበት ግልጽ ነው፡፡ ያም ቢሆን ከምንም በላይ ግን በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ስለሚኖር አንድ ቀን ራሱንም ኢትዮጵያንም ሊያነሳ እንደሚችል ግልጽ ነበር፡፡ የብሔር ቡድኖች የአማራን መደራጅት እንደጦር የሚፈሩት አካሄዱ ኢትዮጵየን መልሶ ኢትዮጵያ ያደርጋታል በሚል ስጋት እንጂ አማራ እንደ አማራ የሆሉ ቀበሌዎች ውስጥ የአማራ በአማራነት መደራጀት እጅግ ደስታቸው ነበር፡፡ አሁን ላይ አማራን በአማራነት ለማደራጀት በሚደረገው ሂደት ውስጥ በዋናነት የማራውን የኢትዮጵያዊነት ልዕልና እያጣጣሉ ከሌሎች ጋር በጠላትነት እንዲያስብ እያደረጉ ከማንነቱ አውርደው የመከነ እያደረጉት ያሉትን የፖለቲካ አዝማሚያ እያየን ነው፡፡ ኦሮሞ ዛሬ የደረሰበት ውድቀት የደረሰው በዚህ መልኩ እንደሆነ ብዙዎች አይረዱም፡፡ ዛሬ የኦሮሞን ፖለቲካ ማንም ለፈለገው ሴራ ይጠቀምበታል፡፡ ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀዳሚው አድርጎ የሚያስብ የኦሮሞ ምሁር ከኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚለው በብዙ እጥፍ ድምጹ ይሰማል፡፡ እንግዲህ ኦሮሞን ዛሬ ለደረሰበት የፖለቲካዊ ውድቀትና የማንነት ማጣት የዳረገው የጥላቻና ዘረኝነት ፖለቲካ ራሱ አሁን ላይ አማራውን እየሸረሸረው እንደሆነ እየተሰማኝ ነው፡፡ እኔ በአብን ላይ አሁን እንደውም ከበፊቱ በተሻለ ተስፋ እያደረኩ ነው፡፡ ሆኖም ግን በአማራ ሥም በአላዋቂዎች ይሁን በሴረኞች በከፍተኛ ደረጃ እየተነዛ ያለው ፖለቲካ አደገኛ እንደሆነ እያየሁት ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን ታማኝ በየነ አማራ አደለም ቅማንት ነው የሚል ትልቅ ዘመቻ አይነት የሚመስል ነገር ሰምቻሁ፡፡ ይሄን ፖለቲካ ተመልከቱት፡፡

ማንነትህን እወቅ፡፡ ከጅምሩ አማራና ቅማት በሚል የመጣችው ሴራ ምን ለማሴር እንደሆነ መረዳት አለመቻል ትልቁ ስህተት ነው፡፡ ታማኝ ቅማንት ሆነ አማራ እሱ ጎንደሬነቱን እንጂ አማራነቱንም ቅማንትነቱንም አልተናገረም፡፡ ለመሆኑ ቅማንት ማን ነው? አማራስ ማን ነው? ጎንደረው አማራ አያቶቹ እነማን ናቸው? የጎጃሙስ የወሎውስ?በአማርኛ መናገር ነው እንዴ አማራነት? አሜሪካን አድጎ ኢንግሊዘኛ ብቻ የሚናገር የጎንደሬው ልጅ ከአማራነት የሚያግደው አለ? እንግዲህ አማራ የተባለው ማህበረሰብ ዛሬ አማርኛ የሚያወራውን ብቻም እንዳልሆነ በድንብ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለመሆኑ ግን አማራ በሚል በየቦታው በሚደርስበት ጥቃት ከመሠረቱ ቅማንት የሆነ የለበትም? አገው የሆነ የለበትም? እስኪ በየክልሉ እየሄዳችሁ ተመልከቱ በአማራነት እየተጠቃ ያለው ዛሬ አማራ ክልል ውስጥ እርስ በእርሱ ቅማነት፣ አማራ፣ አገው እያለ እራሱን የሚሸረርፍ ሁሉ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ በእምነትም ስንመጣ ይሄው ነው፡፡ ሙስሊም ሆንክ ክርስቲያን በአጠቃለይ ከወሎ ከጎጃም፣ ከጎንደርም በአጠቃላይ ዛሬ አማራ ከተባለው ክልል ሄደው በሌላ ቦታ በሚኖሩ ላይ ሁሉ በአማራነት አደለም እንዴ እየተጠቁ ያሉት? ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ እንደተባለው ነው፡፡ ቅማነት አማራ አገው በሚል ጠላት ምን እየሰራ እንደሆነ አለማስተዋል አደጋ ነው፡፡

የአማራ የጥላቻና ዘረኝነትን ፖለቲካን በተለየዩ ቦታዎች መስፈማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከአምክነዮ የወጣ ሁሌም በሮሮና በጥላቻ የአማራ ፖለቲካ እንዲቀጥል የሚያደርጉ እየበዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ከውስጥ ችግራቸው የተነሳ ሰዎች የሚሉትን ራሱ በራሳቸው አስተሳሰብ እንጂ በትክክል የተባለውን አያደምጡም፡፡ ለምሳሌ አምባቸው በአምቦ አዲስ አበባን አስመልክቶ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ማስከበሩ የእኛም ፍላጎት ነው ያለውን ንግግር በጣም አሳፋሪ በሆነ መልኩ የኦሮሞን ልዩ ጥቀም ለማስበር እኛም እንሰራለን ብሏል ብለው ያስነበቡንና ይሄንኑው አማራ የተባለ ሁሉ ሲያራግብ ታዝቤያለሁ፡፡ አሁንም አስተውሉ፡፡ ጉዳዩ ምን ያለበት ምን እንደሚባለው ነው እንጂ  አምባቸው የተናገረው እንዳች ሥህተት የለበትም፡፡ የኦሮሚያን ጥቅም ማለትና የኦሮሞን ጥቅም ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ኦሮሚያ የአስታደደር ክልል እንጂ ኦሮሞ ብቻ ማለት አደለም፡፡ በኦሮሚያ ኦሮሞ ያልሆኑ በርካቶች አሉ፡፡ የአዲስ አበባውን ከኦሮሚያ ጋር ያውን ነገር ከጅምሩ ልዩ ጥቅም በሚል በቃላት ከማሳከር የጋራ ጥቅም መባል ነበረበት፡፡ የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ደግሞ ከእዚህ ክልል የተለያዩ አገልግሎቶች ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ቆሻሻ መጣያ፡፡ አዲስ አበባ ቆሻሻዋን ለመጣል በአዋሳኝ የኦሮሚያ ቀበሌዎች እየተጠቀመች ያንን ቆሻሻ በሕዝብ ላይ ጎዳት እንዳያመጣና ሕዝብ እንዳይጎዳ ግን ኃላፊነቱ የኦሮሚያ መንግስት ነው ማለት ምን አይነት አምክንዮ ሊሆን ይችላል? ይሄን ጎዳይ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንደሚጠቀሙበት አደለም፡፡ እነዚህ ቀበሌዎች የአዲስ አበባ ክልል ውስጥ እንኳን ቢሆኑ በቀበሌ ደረጃ የቆሻሻ መጣያ ቦታ ከሰጡ የአካባቢው ሕዝብ ይሄን ቆሻሻ ተከትሎ ለሚመጣበት በቂ ዋስትና ሊሆነው የሚችል ማካካሻ ያስፈልገዋል፡፡ ይሄ የልዩ ጥቅምነት ጉዳይ ሳይሆን ለሚያቀርበው አግልግሎት ከዛም በላይ የራስን መብት (ጤናማ አየር) መስዋዕት እስከማደረግ የተከፈለ ነውና፡፡ አምባቸው ኦሮሚያን እንደመንግስት ከአዲስ አበባ እነዚህ ለአዲስ አበባ አገልግሎት እያቀረቡ ያሉ ቦታዎችን ለመካስ ልዩ ጥቅም የተባለውን መክፈል አለባት እንጂ ለኦሮሞ የሚል ቃል ከአፉ አልወጣም፡፡  ይሄ ልዩ ጥቅም ተብሎ የሚነገረው ሲጅምር ዝም ብሎ ለኦሮሚያ በሚል መተውም ያለበት አደለም፡፡ ይሄ ገንዘብም ሆነ ሌላ ማካካሻ በቀጥታ እነዚህ በአዲስ አበባ ምክነያት ለሚጎዱና በቀጥታ አገልግሎት ለሚያቀርቡ ቀበሌዎች የሚውል መሆን አለበት፡፡ ይሄን ቁማር ግን የኦነግ/አዴፓም የአማራ የጥላቻና ዘረኝነት ፖለቲካ አራማጆችም ሌላውም ዝም ብሎ የሚደነብረው ይጫወቱበታል፡፡ እየተስተዋለ፡፡ አምባቸው ከዛ በኋላ ወጥቶ ይሄን ጉዳይ ማብራራት ነበረበት፡፡ ግን አልሰበማሁም፡፡ ይሄ ከላይ ያልኩት የአማራ የጥላቻና ዘረኝነት ፖለቲካ ስጋቴን ከጨመሩት ነው፡፡

የሰሞኑ የአብይ ንግግር፡- “አምቦ ላይ አራት መኪና ስኳር አስቆምክ ብለን በመሳሪያ አንገድልም ” ሌላ ሌላውን ዝባዝንኬ እርሱት፡፡ አብይ ምን ያህል አደገኛ ሰው እንደሆነ በዚህ ንግግሩ አስተውሉ፡፡ ፖለቲካን እንዴት በዘር ማንነት ላይ ቁማር ሲጫወት ተመልከቱ፡፡  “አምቦ ላይ አራት መኪና ስኳር አስቆምክ ብለን ወጣት በመሳሪያ አንገድልም “፡፡ እውን እንዲህ ያለ ነገር የጠየቀ ሰው አለ? የአምቦ ወጣት ስኳር የጫኑ መኪኖርን ያስቆመበትን ክስተት ሕገ ወጥ ነው ያለስ አለ? ይሄን ክስተት አስታውሳለሁ፡፡ በአንድ ወቅት አምቦ ላይ ስኳር ከእነጭርሱ ጠፋ፡፡ አምቦ ስኳር አምራቹ ፊንጫዓ በጣም ቀርብ ነው፡፡ የአምቦ ሕዝብ የፊንጫዓ ስኳር የእኔ ነው ብሎም አደለም፡፡ ግን ሌላ ቦታ የተሻለ አቅርቦት እያለ ከሌላው ቦታ በከፋ አምቦ ላይ የስኳር እጥረት አጋጠመ፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ (ወጣቱ) እነሱን እያለፈ ወደሌላ የሚጓዘውን ስኳር አገቱት፡፡ ይሄ እኮ ግልጽ ሰላማዊም የሆነ የመብት ጥያቄ እንጂ አመጽም አደለም፡፡ ከሌላውም የተለየ ስኳር ፍላጎትም አደለም፡፡ ሌላው የሚያገኘውን ስላጣ እንጂ፡፡ ይሄን ክስተት ዜጎች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ሥርዓተ አልበኝነት እየተስፋፋ ነው መንግስት እንደመንግስት ለምን ቸል ይላል ለሚለው አብይ ለማስተባበያ የተጠቀመበት አሳፋሪ ንግግር ነበር፡፡ ሰው እየገደሉ ባንክ እየዘረፉ ያሉትን አረመኔዎች በአምቦ ፍትሀዊ በሆነው የመብት ጥያቄ በመሸፋፈን አረመኔዎችን ሽፋን እየሰጠ ራሱን የአምቦ ወጣት ተቆርቋሪ ሌሎች ደግሞ ስኳር እንዳናገኝ ያደረገንን የአምቦን ወጣት ግደልልን ያሉት ይመስል ይሄን መልስ ሰጥቶናል፡፡ በዛውም ራሱን አምቦዎች ውስጥ ለመደበቅ፡፡ ጥያቄው ግልጽና ግልጽ ነው፡፡ ኦነግ የተባለ አሸባሪ ቡድን ሰው እየገደለ በየቦታው የሽብር ሥራ እየሰራ ነው፡፡ በየክልሎችም በብሔር ምክነያት ሰዎች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ግልጹና አጭሩ ጥያቄ፡፡ ይቀጥላል አብይ እንታገስ ብለን ነው ይልሀል፡፡ የዜጎች ሕይወት በየቦታው እየረገፈና በሚሊየኖች የሚቆጠሩ እየተፈናቀሉ ትግስት ይልሀል፡፡ ገዳዮችን ሲጠየቅ የአምቦ ወጣቶችን የገዳዮቹ አካል አድርጎ ያምታታሀል፡፡ የሚገርም ነው!

አብይ ከምንጠብቀው በላይ አደገኛ አካሄድ እንደመረጠ እናያለን፡፡ አዝናለሁ! ኢትዮጵያውያንን በቃላት በማታለል ኢትዮጵያን ከሚያፈረሱት ጎን ሆኖ እያሴረ እንደሆነ እናያን፡፡ የቤተመንግስት እድሳት በሚል እየሰራሁት ነው የሚለውን ፕሮጄክት የሆነ ጊዜ ሰውዬው የታሪክ አሻራ ለማጥፋት ነው ብለው ሰዎች ሲተቹ ተራ ነገር መስሎኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ሰውዬው በእንደእነዚህ ርካሽ በሆኑ ሴራዎች ላለመሳተፉ ምንም ማስተማመኛ የለም፡፡ በጣም ይዋሻል፣ ራሱን ለማሳወቅ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ለዚሁ እንዲረዳው ዙሪያውን ከእሱ በታች በአሉ ሰዎች አስከበቦ እያስጨበጨበ እናየዋለን፡፡ መለስም ይሄንኑ ስልት ይጠቀም ነበር፡፡ እንደመንግስት ሳይሆን እንደ ወሮበላ ቡድን አደረጃጀት ባለው መዋቅሩ ይሄው ነገሮች እየፈጠጡ መጥተዋል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ሰሞኑን መልስ ለመስጠት የሚሆን ሌላ ብሔር እንኳን እንደሌለው ታዘብን፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሞኑን ድጋሜ በወለጋ ተዘረፈ የሚል ዘና ተሰምቷል፡፡ እንግዲህ አስቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለወለጋው ኦነግ በዘረፋ ሥም ገንዘብ እያስተላለፈ ላለመሆኑ ምንም ማስተማመኛ የለም፡፡

ኦሮሞ ሆንክ አማራ ወይም ሌላ አሁን ላይ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ምን ያህል እንደሚጫወቱብ አስተውል፡፡ ወሮበሎች አገርህን እንደያዙት አስብ፡፡ ወያኔ የለቀቀ መስሎህ አሁንም ወያኔ ያሳደጋቸው ጸረ-ሕዝብ የሆኑ ወሮበሎች እንዳሉብህ አስብ፡፡ በሁሉም ቦታ ይሄ እየሆነ ነው፡፡ ከማንነትህ እያወጡ የንግድ እቃቸው እያደረጉህ እንደሆነ አስተውል፡፡ እንደ ሚሊየን ሕዝብነትህ አስብ፡፡ የሆነ ከአንተ የወጡ ወሮበሎችን እየደገፍክ ለልጅልጅ የመከራ ሕይወት አታውርስ፡፡ በሱማሌ ክልል ያለው ከዘለቀ ሁኔታ ከሌላው በተለየ አስደሳች ነው፡፡ የሱማሌ ሕዝብ አሁን እንደሕዝብነቱ የሚያስቡለት ስለበደሉ የሚቆጩለት መሪዎች የመጡለት ይመስላል፡፡ ኦብነግን ጨምሮ በክልሉ አወንታዊ ለውጥ እንዲመጣ እየሰሩ እንደሆነ እናያለን፡፡ ጉዳዮን ከፖለቲካ ቡደንኖች ሽኩቻ ይልቅ የሕዝብን መከራና ግፍ መሠረት ያደረገን አካሄድ እየተከተሉ ይመስላል፡፡ ፈላስፋው ሙስጠፌ የወያኔን የዘር ፖለቲካ ከሥር እየገዘገዘ በሱማሌ ልዩ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብን እያሰፈነ ይመስለል፡፡ ሙስጠፌን ከጅምሩ ፍልስፍናውን ከምወደው ነው፡፡ ይሄ ዛሬ ያልኩት አደለም፡፡ ዛሬ ያለበትን ቦታ ከመታሰቡ በፊት በሚያነሳቸው ጉዳዮች አይቼዋለሁ፡፡ ዛሬ ያን አስተሳሰቡን በተግባር እያደረገው ስላገኘሁት ተደስቻለሁ፡፡ በሱማሌ በኩል በኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤትነት ጥያቄን እያጎሉ የመጡም ሌሎች ምሁራን እየበረከቱ ይመስላል፡፡ ይሄ ሌላው የሚበረታታ ጉዳይ ነው፡፡ በተበዳይነትና በበታችነት አስተሳሰብ ሕዝብን ከማንነት አውጥተው በመከራ ያኖሩበትን የጠላቶቹን ሴራ እነ ሙስጠፌና አጋሮቹ እያመከኑት ይመስላል፡፡ በተግባር የሚታዩ እውነታዎች፡፡ ይሄ እውነት ከአብይ የዲስኩር ኢትዮጵያዊነት በተቃራኒ በተግባር የኦነጋዊነት ሴራ የተለየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤትነት ድርሻ ጠያቂዎች ጉልበት እንደሚኖራቸው ጥርጥር የለውም፡፡ የኦሮሞ በቁጥር በዝቶ በተጽኖ የወረደበት ዋናው ምክነያት ከታሪክ ባለቤትነት አውጥተው የእነ ተስፋዬ ገብረአብ የድግምት መጻፍ አምላኪ ያደረጉት እለት ነበር፡፡ አሁን አማራውን በተመሳሳይ ስልት እያመከኑት ይመስላል፡፡

ኢዜማ፡- ጥሩ ነው ግን ጮቤ የሚያስረግጥ ነገር የለውም፡፡ የብርሀኑ ዋና ሆኖ መመረጥ ጥሩ ገጽታን አይፈጥርም፡፡ ሲጀምር ብርሀኑ መሠረታዊ የኢትዮጵያዊነት ልፍስፍስ ፍልስፍና ያለው ሰው ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ብርሀኑ የሚታወቅበት አዲስ አበቤነቱ ነው፡፡ አንዱ አለም ጥሩ ከሚባሉ ነው፡፡ እሱም ቢሆን በኢትዮጵያዊ እልኸኝነትና ቁጭት ደረጃ ለመሆኑ እርግጠኛ አደለሁም፡፡ ኢትዮጵያ ቁጭት የተሰማው መሪ ትፈልጋለች፡፡ ዛሬ ሙስጠፌ በሱማሌ ክልል ስለሆነው ነገር የሚቆጭበት ስሜት ያስደስተኛል፡፡ በኢትዮጵያዊነትም እንዲሁ  ቁጭት የሚሰማው ከሆነ ምን አልባት ሙስጠፌን በመሪነት ቦታው ማሰቡ ከወዲሁ ለመዘጋጀት ይጠቅማል፡፡ አብይ በመጀመሪያ ቀን ንግግሩ ይሄ ስሜት ያለው መስሎን ነበር ቆመን አድምጠን እንደእንቁለል እንዳይሰበር ስንከባከበው የነበረው፡፡ አብይ በአንድ አመት ውስጥ የውስጥ ማንነቱን በተግባር አሳይቶናል፡፡ በአብይ ላይ ጠ/ሚኒስቴር ከመሆኑ በፉት የነበረኝን እይታ ተናግሬ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ሲያደንቁት እኔ ሊመጣልኝ አልቻለም ነበር፡፡ ሆኖም ጠ/ሚኒስቴር ሲሆን በፊት ያሰብኩት የተሳሳትሁ ስለመሰለኝ ራሴን ወቅሼ ነበር፡፡ ለዛም አንድ ሁለት ጊዜ በጣም የፈጠጡ ነገሮቹን ስላየሁ ከመተቸት በቀር በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ ከሰጡት ነኝ፡፡ ከእሱ ይልቅ ለማን ዛሬም ድረስ በተሻለ መልኩ አምነዋለሁ፡፡ ለማን አላስፈላጊ መንገድ እየወሰዱት ያሉት ሌሎች ይመስሉኛል፡፡ ለማ ማንም ሰው ሆኖ በአልተገኘበት ወቅት ብቻውን ለእውነት ቆሞ ተጋፍጧል፡፡ ያም ብቻ አደልም የኦሮሚያ ፕሬዘደንት ሆኖ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ንግግሮቹን አደምጥ ነበር፡፡ ለማ ለማስመሰል መናገር አይችልበትም፡፡ ቁጭትም አለው፡፡ አብይ ጋር ይሄ የለም፡፡ ብልጣብልጥ ነገሩን በይፋ አነብ ነበር፡፡ በአጠቃላይ መሪን በዚህ አይነት እናስብ፡፡ የብርሀኑ ኢዜማን መሪ መሆን ከኢሀፓ ጀምሮ የነበረውም ጥሩ ያልሆነ ታሪክ እክል ነው፡፡ ብርሀኑ ብልጣብልጥ ይሁን ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ በኢትዮጵያዊነት መሪ ለመሆን የሚንቀሳቀስን ፖለቲካ ቡድን ግን ለመምራት ይጎድለዋል፡፡ ከእሱ ይልቅ የሺዋስ ሳይሻል አይቀርም፡፡

አብን፡-ከላይ የአማራን ፖለቲካ ነገር ስጋቴን ገልጫለሁ፡፡ የአማራን ፖለቲካ አብን ሆን ብሎ ላይሆን ይችላል ግን የሚያጠፋቸው ጥፋቶች አሉ፡፡ በተለይ ሊቀመንበሩና ጸሀፊው የመሠረታዊ የመሪነት ባሕሪ ያላቸው አደሉም፡፡ ጸሀፊው ክርስቲያን የአማራ ሊግ ወጣቶች ነበር መባሉ እኔን ካልተመቹኝ ነው፡፡ የወጣቶች ሊግ የነበሩ ሰዎች እነማን እንደሆኑ እናውቅ ነበርና፡፡ ሆኖም በዚህ ብዙ አልከሰውም፡፡ ግን በተግባር የአማራ ተቆርቋሪ በመምሰል ሕዝቡን ከማንነት ልዕልናው ከሚያሰውጡት ንግግሮችን ከሚናገሩ አንዱ ነው፡፡ ከአለመብሰል ይሁን ወይም በወያኔ በማደጉ የተሰጠውን ሚሺን ለመፈጸም አላውቅም፡፡ ሊቀመንበሩ የብስለት ችግር ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምክትሉ ግን እንደማየው ጎበዝ ይመስላል፡፡ አብን አማራን እወክላለሁ ከአለ እንደ በለጠ ንግግር ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ የበለጠ ፍልስፍና (የአብንም ነው ብለን እናስብና) የዜግነት ፖለቲካን እናራምዳለን ከሚሉት በብዙ እጥፍ የዜጎችን መብት ዋስትና የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ ላይ በለጠ የኢትዮጵያዊነት ቁጭቱም ይነበብበታል፡፡ ከአልተሳሳትሁ፡፡ አማራን እንደ አማራ ማደራጀቱን ኢትዮጵያውያንን ለማስተሳሰር ከአልሆነ ትርጉም የለውም፡፡ ያም ሆኖ አብንን ከሰው በላ አሸባሪዎቹ በይፋ ሰው እየገደሉና እያፈናቀሉ፣ ባንክ እያዘረፉ ከአለው የኦነጋውያን ቡድን ጋር እያነጻጸሩ ለመተቸት መሞከር ትልቁ ስህተት ነው፡፡ አብን አስካሁን በምናየው ስለ ዜጎች ጥሩ የሚባሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች በተግባር እየጠየቀ ያለ ቡድን ነው፡፡ የአዲስ አበባን ከተማ ጉዳይ ጨምሮ ተደራጅቼለታለሁ ከሚለው አማራ ውጭ እንደነ ጌዲዮና ሌሎች ሕዝቦች መፈናቀልን በመግለጫ ያወገዘ ብቸኛ ቡድን ነው፡፡  በተግባር እንፈልጋለን፡፡ ከዚህም በላይ ራሱን እያስተካከለ ከሄደ ጥሩ ሚዛንን የሚያስጠብቅ አቅም ያለው ይሆናል፡፡ አሁን የምናየው በአብን ላይ ያለው ዘመቻ የፍራቻ ይመስላል፡፡ አብንን ብዙዎች ፈርተውታል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በአማራ በኩል ያመጣብናል ብለው ነው እንጂ ፍራቻቸው አማራን በማደራጀቱ አደለም፡፡ እንደውም አማራ በአማራ አክራሪነት ቢደራጅላቸው ከማንነቱ ለማውጣት ስለሚመች ብዙዎች ይፈልጉታል፡፡ የብሐየር ፖለቲካ ቡድን ሆነው ዛሬ አብን ላይ ትልቅ ዘመቻ የከፈቱት አደጋ ሊሆንባቸው እንደሚችል ስለገባቸው ነው፡፡ ገና ከአሁኑ ሸዋ አካባቢ ያለውን ፖለቲካ ለመቀየር እየሰራ እንደሆነ እናያለን፡፡ ከኢዜማ ይልቅ በኢትዮጵያዊነት የብሔር ፖለቲከኞች የሚፈሩት አብንን ነው፡፡ በተግባር ያለው እውነት ይሄን ነው የሚመስለው፡፡ አማራ ነኝ በሚል በሌሎች ላይ የጥላቻና ዘረኝነት ፖለቲካ የምታራምዱ አክቲቪስትና ፖለቲከኛ የአብንን ተግባር እንዳያበላሹት ግን ሥጋት አለኝ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

ሰርፀ ደስታ

4 COMMENTS

 1. The amhara need to organise better to give leadership for the people of ethiopia for unity, democracy , justice and peace.
  Over the last 50 years ethno liberation fronts have changed the mentality of the people they claim to represent into slavery and setting them selves as ethnic liberators.
  Only the amhara can restore confidence , unite our country and lead its people to restore its place as a proud country among the nations of the world.
  At the core of amahara organisibg itself is the ethiopian unity.
  The amhara groups should not depart from this principle . Their aim should always be the well being unity of ethiopians as people of one great country.
  Amhars unity for Ethiopia.

 2. “አደገኛው የአማራ ፖለቲካ”
  ሳያጣሩ ወሬ ሳይገሉ ጎፈሬ ይባላል፡፡ ይህን የፈረንጅ ድጎማ እየበላህ ስትጠግብ ያው የፈረደበትን አማራ መሳደብ ያስደስትሃል፡፡ ከርሳም፤ ጽፈህ ሞተሃል፡፡ መጃመሪያ አይምሮህ እንዲሰራ የተሸከመከውን በደን በስፖርት አቃጥለው፡፡ መቸም ይህ የፈረደበት አማራ የማንም ቅራቅንቦና ማህይማን መፈላሰፊያ ከሆነ ሰነበተ፡፡ አሁን አንተን አማራ ምን አደረግህና ነው አደገኛ ፖለቲካ የምትለው፡፡ የሚሞተው፤ በገጀራና በቀስት እንዲሁም ከነሕይወቱ ገደል ውስጥ የሚወረው አማራው ነው፡፡ ስለዚህ ምን ያድርግልሕ፡፡ በአንተ ቤት ብልጥ ሆነህ ሞተሃል.. ኦሮሞ ቅብጥርስይ ምናምን ትላለህ፡፡ አንተ ድንጋይ እራስ ከገባህ በአሁኑ ስአት ተደራጅቶ መብቱን ማስጠበቅ ብቻ አይደለም እንደ ንስሃ አባቱ ወያኔ በተመሳሳይ ቀመር በመጠቀም በዝርፊያ ላይ ያለ ቢኖር የኦሮሞ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ በመደራጀት ትንሷወያኔ እኳን ያን ሁሉ ህዝብ እንደ በግ ነድታ ቂጡን ገልባ ገርፋዋለች፡፡ በመጨረሻ አማራ ከዚህ በኋላ አይሸወድም፤ እንደ አንተ ያሉ ቅል እራሶች ሲቀልዱበት አይኖሩም እርምህን አውጣ፡፡ ከርሳም፡፡

 3. “አደገኛው የአማራ ፖለቲካ” የሚለው የጽሁፍህ ርእስ ባይጥመኝም ከሞላደል ያቀረብካቸው የእርምት ሃሳቦች በወጣቶች ለተሞላው አብን ጥሩ ማሳሰቢያ ነው:: ሆኖም ግን ምንም ቢሆን ለዘማናት ኦሞን ነጻ የማወጣ ነን ብሎ ጭራሽ ከተከፋፈለውና ኣኦሮሞን የሚበጁ ኣአጀንዳዎች ከማቅረብ ይልቅ አማርና የሚያዋርድ የሚጨርስ ዘመቻ ለተያያዝወና በአብይ አህመድ ምንም ቁጥጥር ለማያደርግበት ኦነግና መሰሎቹ ማለትም መለስ ዜናዊ የጠፈጠፈው ሲላጥ ኦነግ ነው ከሚባለው ኦፕዲኦ ለሚደርስ የተለመደ ጥቃት አብን በጽናት መስራቱን ላደንቅ ወዳለሁ:: ስለመሪዎቹ ያለመብሰልክ የቀረበው ትችትም በስለው ካረሩትና ጋብቻና ቤተክርስቲያን ገበያም ሳይቀር በብሄር ይሁን ከሚሉት ከነበቀለ ገርባ የጥላቻ ከፋፋይ ፖለቲካ ይልቅ የአብን ወጣቶች ለትውልድ ሃገራችንም ሆነ ለአማራው ህዝብ በተገቢ ምክር ድንቅ የሃገር መሪ የሚሆኑበት እምቅ ስጦታ እንዳላቸው ይታያልና::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.