ለሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበት የአመራር ለውጥ እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ገለጹ

ዶ/ር አምባቸው መኮንን

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2011ዓ.ም (አብመድ) እስከ 70 በመቶ የሚደርስ የአመራር መተካካት የተደረገባቸው ቦታዎች ቢኖሩም የመተካካት ሥራው በጥናት የተደገፈ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የተፈለገው ውጤት አለመምጣቱንም ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በወረዳ፣ ዞንና ክልል ደረጃ ባሉ የተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ መተካካት እስከ 70 በመቶ የሚደርስ የአመራር መተካካት የተደረገባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ነው ያመለከቱት፡፡

ይሁን እንጂ የመተካካት ሥራው በጥናት ያልተደገፈ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም፡፡ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተደረገ ሕዝባዊ ውይይትም የአመራር መተካካቱ ውጤታማ ያልሆኑባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን መረዳት መቻሉን ዶክተር አምባቸው ለአብመድ ገልጸዋል፡፡ በተለይ በቂ ልምድ የሌላቸው አመራሮች ከመኖራቸው ጋር በተያያዘ ሠራተኞችን በደንብ ወደ ሥራ ያለማሠማራት ውስንነት መኖሩንም ነው የገለጹት፡፡

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውጤታማ አመራር መገንባት አይቻልም፡፡ ያለው አመራር ያለውን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ በመሥራት አዲስ ለሚተካው ሰው በቂ ጊዜ ሰጥቶ በሚገባ ሥነ-ምግባሩን፣ ቁርጠኝነቱን እና የሥራ ብቃቱን ብሎም ለሕዝቡ ያለውን ውግንና በጥናት እና በበቂ መረጃ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ሊዘገይ እንደሚችል ቢገመትም ባልተጠና መረጃ ላይ ተመሥርቶ አመራር ተክቶ መልሶ ከማፍረስ ይልቅ በቂ ጊዜ ወስዶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የማይመጥኑ አመራሮችን በአዳዲስ የመተካት ሥራው ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡ አሁን ያለው አመራር ሀገራዊ ለውጡን በደስታ የተቀበለው እንደሆነ ያስታወቁት ርዕሰ መስተዳድሩ ቀጣይ ግን በተሻለ መልኩ በዕውቀት ላይ የተመሠረተና ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበት የአመራር ለውጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ የመንግሥት የሥራ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ መቀዛቀዝ እየታየበት መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡ ተገልጋዮችም በተለያየ አጋጣሚ ቅሬታ እንደሚያነሱ ነው ያስረዱት፡፡ በተደረጉ የትውውቅና የውይይት መድረኮች የመንግሥት ሠራተኞች ለሥራቸው ግዴለሽ መሆንና የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሕዝቡ በመሠረታዊነት የሚያነሳቸው ናቸው ብለዋል ዶክተር አምባቸው፡፡ የተቋማት የአመራር ድክመት እንዳለ ሆኖ የመንግሥት ሠራተኛው ሰዓቱን በየማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማሳለፉ፣ ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጠ መሆኑ፣ የሥራ ሰዓቱን ከቢሮ ውጭ ሆኖ ማሳለፉና ቢሮም ሆኖ ቀልጣፋ አገልግሎት ያለመስጠት ችግር የቅሬታ ምንጭ መሆናቸውን ያስገነዘቡት፡፡

ችግሮችን መነሻ በማድረግ በክልል ደረጃ ያሉ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አመራሮች በተገኙበት ሁሉም ሠራተኛ በተሠማራበት የሥራ መስክ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዉይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ መሠረት ዝርዝር የሥራ ተግባራት ቆጥሮ ሰጥቶ ቆጥሮ የመቀበል ባሕል እንዲዳብር እና የየተቋማቱ ኃላፊዎችም የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡ ከምንም በላይ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች የመጨረሻ አቅማቸውን ተጠቅመው ሊሠሩ ይገባል ያሉት ዶክተር አምባቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ተጥዶ የአሉባልታ ሐሳብ ሰለባ ከመሆን ወጥቶ እራሱን በተግባር ሊገነባ አና ኅብረተሰቡንም በቅንነት ሊያገለግል ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

1 COMMENT

  1. በማኅበራዊ ሚዲያ ተጥዶ የአሉባልታ ሐሳብ ሰለባ ከመሆን የመንግሥት ሠራተኛው ሰዓቱን በየማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማሳለፉ፣ ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጠ መሆኑ፣ የሥራ ሰዓቱን ከቢሮ ውጭ ሆኖ ማሳለፉ…….አንድ ቢሮ የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት ይወጣ ዘንድ ሰርቶ የሚያሰራ መሪ ያስፈልገዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን አዴፓ ታማኝ አባሎቹ ቅር እንዳይሰኙበት ብቻ በይሉኝታ ከማይመጥናቸው/ከማይመለከታቸው ቦታ ላይ በሃላፊነት ይመድባቸዋል። ከኦዴፓ አንፃር ሲታይ አዴፓ ያደረገው መተካካት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚል ሃሜት በስፋ ይናፈሳል። አንድ አባባል ልብ እንበል “የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ።” የሚለውን። ጭንቅላቱ/መሪው ከተበላሸ ፈፃሚ ሠራተኛው ዕጣ ፈንታው ከላይ የተገለጡት ናቸው። ምስኪኑ ተገልጋይ ህብረተሰብም ፍላጎቱ ሳይሟላለት ይቀርና ነገሮች ሁሉ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ይሆናሉ ማለት ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.