የምንወዳቸውን ሰዎች ማክበር እና ሰላም መስጠት እንልመድ!

አሜሪካ አገር ውስጥ፥ ስለሰው ጤንነት በግምት እና በስማ በለው ተነስቶ መነጋገሪያ ማድረግ፤ ማንኛውም የህመም ዓይነት በሀኪም ከታወቀ በኋላ ከታማሚው ፈቃድ በቀር በምንም ዓይነት ሁኔታ መረጃ ለሌላ አካል ማስተላለፍ፤ በታማሚው ፍቃድ ያገኙትን መረጃ ታማሚው በጽሑፍ ካልፈቀደ በቀር ለሌላ ሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ/ማውራት፣ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ናቸው።

ሰውን ተደብቆ ፎቶ ማንሳት፣ ድምጽ ወይም ምስል መቅረጽ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው። (በተለይ ደግሞ ድብርትን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት የስነልቡና ችግር ላይ ብለው ያሰቡትን ሰው፣ ራሱን ለመከላከል በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ተብሎ ሲባል ጥፋቱም፣ ቅጣቱም ይገናሉ።)

ማንኛውም ሰው፣ ስለራሱ “እንዲህ ሆኗል፣ እንዲህ ታይቷል፣ እርዳታ ያሻዋል” ዓይነት ወሬዎችን ደጋግሞ ሲሰማ፣ ወደ ድብርት እና ሌሎች የስነልቡና/የአእምሮ ጫና ችግሮች ሊፈጠሩበት ይችላሉ።

በማንኛውም ዓይነት የስነልቡና ችግር ላይ ደግሞ፥ “እንዲህ ሆኗል፣ እንዲህ ታይቷል፣ እንድረስለት፣ እንዲህ እናድርግለት” ሲባል ሲሰማ ሕመሙ ጭራሽ ይባባሳል፣ ከሰዎች መሸሽ ይፈልጋል፣ ራሱን በሚችለው መልኩ ማራቅ ያመጣል፣ አንዳንዴም ራሱን የሚጎዳ እርምጃ መውሰድ እስከማሰብ ድረስ ሊደርስ ይችላል።

ህግ ችላ ቢባል እንኳን፣ ኅሊና የሚባል ነገር አለ!

ማህበረሰባችን የሚወዳቸውን ሰዎች የሚይዝበት መንገድ በሙሉም መፈተሽ አለበት። እንደ አንድ ትልቅ አገር ዜጎችም ይሄ አይመጥነንም!! ለሰው ክብር ዝቅ ያለ ነው!

የጂጂን የሙዚቃ ሕይወቷን እና የሰውነት ሕይወቷን ለይተን ማየት አለብን። ቀዳሚው ነገር የግል ሕይወቷ የራሷ የግሏ ብቻ ነውና የምትፈልገውን የግል ጊዜ እና ቦታ (privacy) መስጠት እንኳን ጋዜጠኛ ነኝ ከሚል፣ ከማንም ፊደል ከቆጠረ ሰው የሚጠበቅ ነው። የምትፈልገውን የግል እረፍት ወስዳ መመለስ እንድትችል የሚያደርግ ነገር መስራት አግባብ ነው።

የአየር ሰዓታቸውን የሚሞሉበት ነገር ካጡ፣ የሚጠቅማትን መንፈሷን ደስ የሚያሰኘውን በጎ በጎ ነገር አውርቶ፣ ኮፒ ራይት የሚጠይቃቸውም ስለሌለ የሰራቻቸውን አበርክቶዎች ዘክረው ሙዚቃዎቿን መጋበዝ ነው።

የእሷንም የወዳጆቿንም መንፈስ የሚሰብር ነገር ደጋግሞ ከማስተላለፍ፣ እሷን ከማሸሽ፣ ‘ምን በደልኳቸውን ይህን ያህል? መች ደረስኩባቸው?’ በማስባል ለማሸማቀቅ ከመሞከር፣ እና እሷ የምትወደውን ቤተሰቧን በነገር ሸፋፋኝነት እያነሱ ስም ከማጥፋት ይልቅ፣ አክብሮ መተውና፣ ቤተሰቧን ቀርቦ “የምንረዳችሁ ነገር ካለ” ብሎ ቀድሞ መጠየቅ፣ “የለም! ግን ለበጎ ሀሳባችሁ እናመሰግናችኋለን” ካሉም፣ ወይም ማውራት ካልፈለጉ እንደ ሰው አክብሮ እና በጎውን ተመኝቶ መሄድ፣ ከሰው ልጅ የሚጠበቅ ስልጣኔ ነው።

ጭራሽ በሬዲዮ ያስተላለፉትን ነገር፣ “እሷ ትስማው እና ትሆነውን እንይ” የሚል በሚመስል መልኩ ዩቲዩብ ላይ አድርጎ ገንዘብ ለማግኘት ማሰብ የሚያስነውር ነው። እሷም ዩቲዩብ እንደምትከታተል ይታወቃልና፣ ስትሰማው ምን ይሰማታል ብሎ ማሰብ ለምን ራቀን? (ባለፈው አድማስ ሬድዮ በድብቅ የቀዱትን ድምጽ፣ ዩቲዩብ እንደምትከታተል እያወቁ እንኳን ዩቲዩብ ላይ አድርገውት ነበር። እንዴት ሊጠቅሟት አስበው ነበር ይሆን?)

ስለዚህም እስካሁን የተሳሳታችሁትን ወደኋላ ሄዳችሁ ማረም ባትችሉ እንኳን፣ መለስ ብሎ ቆሻሻን ማጽዳት ይቻላልና፣ ለአድማጮቻሁ እና ለእሷ ክብር ስትሉ ወደኋላ ሄዳችሁ ዩቲዩብ ላይ ያደረጋችኋቸውን ብታነሱ ክብርን ታተርፋላችሁ።

እኛም የምንጽፋቸውን ነገሮች “ባለቤቱ ቢያነባቸው ምን ይሰማዋል?” ብለን ብናስብ የተሻለ እንጠቅማለን።

እባካችሁ፥ ለጂጂ ትንሽ ፍቅር እና ክብር ያለን ብንሆን፣ ይህንን መልዕክት እነሱ ጋር ይደርስ ዘንድ ሼር እናድርገው። ከቻልንም ዩቲዩብ ላይ ያሉትን ቪዲዮዎች አድርገን እናስወርዳቸው።

Ethiopia

1 COMMENT

  1. ያለንበት ዘመን ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም የሚለውን የአበው አባባል አጎልቶ ያሳያል። እውቀት እንደሚበዛ የተተነበዬ እንደሆነ መጽሃፍ ያስረዳል። የሰው ልጅ ከፈጠራቸው ብልሃቶች አንድ የኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ በሶሻል ሚዲያና በሌላ የሚዲያ መስኮች የፈለጉትን ጭቃ ቀብተው የፈለጉትን አዋርደውና ሰድበው፤ የሌለ ነገር ፈጥረውና አለ የተባለን ነገር ለጥጠው ስንቶችን አልባሌ ስም እንደሰጧቸው የእለቱ ዜና ያመላክታል። በዚህ አንጻር በጂጂ ጉዳይ ብዙ እንደተባለም አንበናል። አዳምጠናል። እውነቱ ግን በወሬዎቹ ሁሉ መካከል ወድቋል። አታድርስ ነው። ሰው ከሰው ተገሎ ለመኖር መብት የለውም እንዴ? ይህ ሁሉ የውሸትና የፈጠራ ወሬ ለማን ይጠቅማል?
    በምዕራብ ወለጋ ውስጥ በምትገኝ ጩታ በተባለች ስፍራ የተወለደው እውቁ ገጣሚና ምሁር ሰለሞን ደሬሳ በአንድ ወቅት ያልሆነ ወሬ ማናፈስን በተመለከተ ተጠይቆ እንዲህ ብሎ ነበር። የፈጠራ ወሬ ስትሰማ ምን ይሰማሃል ቢሉት “ምንም” አለ። ለምን ሲሉት ጸሃይ በምስራቅ ትወጣለች ቢሉኝ የሚያከራክር ነጥብ አለኝ። ለፈጠራ ወሬ ግን ከወሬው ፈጣሪ በስተቀር ጉዳዮን የሚያውቅ የለም። ስለሆነም ባዶ (ኦና) ወሬ ነፋስን ለመጨበጥ እንደመሞከር ይቆጠራል ይለናል።
    እጅጋየሁ የህዝብ ሃብት ብትሆንም የራሷን ኑሮ የመኖር መብቷም መጠበቅ አለበት። ሰው ከመድረክ ፈቅዶ ከራቀ በምን አይነት መንገድ ነው ወደዚያ ስፍራ እንደገና እንዲቆም የምናረገው? በራሷ ጊዜ ብቅ ልትል ትችላለች። ጭራሽም በስራዎቿ ላናያትም እንችላለን። እሱ የራሷ ምርጫ ነው። ከእኛ የሚጠበቀው ግን የሌለ ነገርን እንዳለ እንደሆነ አድርጎ በየሚዲያው መለጠፉ መቆም አለበት። በዚህ ምድር ላይ የምንኖርበት ዘመን ውስን ነው። የተሰጠንን እድሜ በብልሃት መጠቀም ከማንም ይጠበቃል። ለጂጂም የምለው … ቁሚ፤ ንቂ፤ የምትወጂው ሃገርና ህዝብ ይናፍቅሻል። ያለውን እውነታ ለህዝብ አሳውቂ። ይህን የፈጠራ ወሬም ለማምከን ይበጃል እላለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.