የፓርቲ መሪ እና የፓርቲ ሊቀመንበር (ታደሰ ብሩ)

በፓርቲ “መሪ” እና በፓርቲ “ሊቀመንበር” መካከል ስላሉ ልዮነቶች ከ Organisation theory አንፃር የማውቀው ካለ እንዳካፍላቸው በግል የሚደርሱኝ ጥያቄዎች በመብዛታቸው ለእያንዳንዱ ሰው በመመለስ የሚጠፋውን ጊዜ ለመቆጠብ ይህን አጭር ማስታወሻ መፃፍ መረጥኩ።

የድርጅቶችን የዕለት ለዕለት ሥራ የሚመራው ሥራ አስኪያጅ (Chief Executive Officer) እና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂያዊ አመራር የሚሰጠው ቦርድ መሪ (Chairman of the Board of Directors) መለያየታቸው በኮርፓሬሽኖችም በጣም የተለመደ አሠራር ነው። ይሁን እንጂ የቢዝነስ “ዓለምን” ትተን የፓለቲካ ድርጅቶች ላይ እንድናተኩር እፈልጋለሁ። “የሰለጠነ” ፓለቲካ አለባቸው በሚባሉ አገሮች የፓርቲ መሪ እና የፓርቲ አስተዳዳሪ (በእኛ ሁኔታ ሊቀመንበር) የተለያዩ ሰዎች ናቸው።

በጣም አጭር በሆነ አገላለጽ የፓርቲው መሪ ሥራ የፓርቲውን ተልዕኮ ማሳካት ነው፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ሥራ ደግሞ የፓርቲውን ተልዕኮ የማሳካት አቅም ያለው ድርጅት መፍጠር ነው። የፓርቲው ተልዕኮ የሚሳካው አገር ላይ ነው፤ በዚህም ምክንያት የፓርቲው መሪና በሥሩ ያሉት መዋቅሮች ትኩረት አገር ላይ ነው። የፓርቲው ሊቀመንበርና እሱ የሚመራው መዋቅር ትኩረት ደግሞ ይህንን ተልዕኮ አሳካለሁ በሚለው ፓርቲ ላይ ነው።

የፓርቲው መሪ ወቅቱ የሚፈቅደውን የትግል ስልት በመጠቀም የፓርቲውን አጀንዳ ያራምዳል። በሰላማዊ ትግል ውስጥ በምርጫ ተሳትፎ አሸንፎ የመንግሥትን ስልጣን በመያዝ፤ ምርጫ ካልተሳካለት ጥላ ካቢኔ (shadow cabinet) በማቋቋምና በመምራት፤ የፓለቲካ እንቅስቃሴዎችን በማደራጀትና በመምራት፤ ሕዝባዊ ስብሰባዎች፣ ኮንፍረንሶች፣ ክርክሮች፣ የተለያዩ የውትወታ (አድቮከሲ) ሥራዎች በማከናወን የድርጅቱ ተልዕኮ እንዲሳካ ይጥራል። ገዢው ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ገድቧል ብሎ ካመነ የትግል ስልቱን ከፍ በማድረግ ሰላማዊ ሰልፎችንና የሥራ ማቆም አድማዎችን ሊጠራ ይችላል፤ በዚህ መፍትሄ ካልተገኘ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሊገባ ይችላል። የፓርላማ ተመራጮች ያለው ፓርቲ ከሆነ የፓርቲው መሪ ሕዝብ አምኖ ከመረጣቸው መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል።

የፓርቲ ሊቀመንበር ዋነኛ ኃላፊነት ፓርቲው አሳካዋለሁ ብሎ ለተነሳበት ተልዕኮ ብቁ ማድረግ ነው። የፓርቲ ብቻ ሳይሆን የማንኛውም ድርጅት ጥንካሬን ከሚወስኑ ነገሮች የሚከተሉት ሶስቱ ዋነኞቹ ናቸው – (1ኛ) ድርጅታዊ መዋቅር፣ (2ኛ) ድርጅታዊ ባህል እና (3ኛ) ግብዓቶች። ፓርቲው የቆመለትን ተልዕኮ ለማሳካት ምን ዓይነት መዋቅር፤ ምን ዓይነት ድርጅታዊ ባህል እና ምን ዓይነት አባላት ሊኖሩት ይገባል የሚለውን መወሰን እና ማቅረብ የፓርቲው ሊቀመንበር ኃላፊነት ነው። ፓርቲ ምርጥ የሆነ የአገር አስተዳደር ፓሊሲ ቢኖረው እንኳን ፓሊሲውን ሊያስፈጽም የሚችል ሰው ከሌሌው የፓሊሲው መኖር ብቻውን ፋይዳ የለውም። ስለሆነውም የሊቀመንበሩ ሥራዎች ከላይ በተዘረዘሩት ሶስት ትላልቅ ምሰሶዎች መግለጽ ይቻላል፤ ድርጅታዊ መዋቅርን ማዘመን (መተዳደሪያ ደንብ፣ የእዝ ሰንሰለት፣ የውስጥ መመሪያዎች፣ ተደራሽነት …)፤ ድርጅታዊ ባህል መገንባት(መተማመን፣ የርስ በርስ መስተጋብር፥ የቅራኔዎች አፈታት ክህሎት፣ ጽናት፣ ቀናነት፣ …) እና ድርጅታዊ ግብዓቶችን ማጎልበት (የአባላት ብዛትና ጥራት፥ የስልጠናዎች ዓይነት፣ በፓርቲው ውስጥ ያለ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣ ገንዘብና ንብረት)።

ለአብነት ያህል

1. የእንግሊዝ
• የሠራተኞች (Labour) ፓርቲ – መሪ ሚ/ር ጀረሚ ኮርቢን፤ ሊቀመንበር ሚ/ር ኢያን ላቨሪ
• የወግአጥባቂ (Conservative) ፓርቲ – መሪ ሚስ ተሬዛ ሜይ፤ ሊቀመንበር ሚ/ር ብራንዶን ሌዊስ

[እንግሊዝ ውስጥ ፓርቲው ስልጣን ሲይዝ የፓርቲው መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን የፓርቲው ሊቀመንበር ደግሞ የሚያዘው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሳይኖረው በሚኒስትር ማዕረግ (minister without portfolio) የካቢኔ አባል ይሆናል]

2. የዩ ኤስ አሜሪካ
• የሪፑብሊካን ፓርቲ መሪ ዶናልድ ትራምፕ (በፓርላማው ”የአነስተኞቹ” መሪ ኬቪን ማክካርቴ፤ ሊቀመንበር ሚስ ሮና ሮምኒ ማክዳንኤል
• የዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ (“የአብላጫዎቹ መሪ“ ) ሚ/ር ስቴኒ ሆየር ፤ ሊቀመንበር ሚ/ር ቶም ፔሬዝ

ስለ ጥላ ካቢኔ

በዘመናዊ ፓለቲካ አንድ ፓርቲ ተወዳድሮ የመንግሥትን ሥልጣን የመያዝ ዓላማ ያለው ከሆነ፤ የሕዝብና የመንግሥት አስተዳደርን መለማመድ ያለበት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ሳይሆን ሥልጣን ከመያዙ በፊት ነው። አሠራሩ ከአገር አገር የሚለያይ ቢሆንም በአውሮፓ በብዙ አገሮች የተለመደው አሠራር ስልጣን የመያዝ ተስፋ ያለው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን የመሰለ ካቢኔ ያቋቁማል። ለምሳሌ፤ በአገሪቱ ውስጥ “የትምህርት ሚኒስትር” ካለ በፓርቲው ውስጥ የትምህርት ሚኒስትርን ጉዳይ የሚከታተል ሰው ይሾማል፤ መዋቅር ይዘረጋል። በትምህርት ጉዳይ ላይ ፓርቲው ስላለው አቋም የሚገለፀው በዚህ ሰው አማካይነት ነው። ይህ ሰው የገዥው ፓርቲ የትምህርት ሚኒስትርን እንደ ጥላ ይከታተላል፤ ይህን የሚያደርገው ግን ለመቃወም ወይም ለመተች ብቻ አይደለም። ገዢው ፓርቲ በትምህርት ጉዳይ ላይ መልካም ሲሠራ፤ ያግዛል፤ ያበረታታል። ስህተት ሲሠራ ደግሞ እየተከታተለ ያጋልጣል። መንግሥት በትምህርት ጉዳይ ላይ ፓሊሲዎችና መመሪያዎች ከማውጣቱ በፊት ከሚያማክራቸው ባለድርሻ አካላት ቀዳሚው የተቃዋሚው ፓርቲ የጥላ የትምህርት ሚኒስትር ነው። በትምህርት ሚኒስትር ምሳሌነት የቀረበው በሌሎች ሚኒስትሮችም ሁሉ መደረግ አለበት፤ ገዢው ፓርቲ 20 ሚኒስትሮች ካሉት ተቃዋሚውም 20 ጥላ ሚኒስትሮች ሊኖሩት ይገባል። በዚህ መንገድ አንድ ጠንካራ ፓርቲ የመንግሥትን ስልጣን ከመያዙ በፊት በወቅቱ በሥራ ላይ እየዋሉ ካሉ መመሪያዎችና ባለሙያዎች ጋር የተዋወቁ፤ ሕዝብም ያወቃቸው ሰዎች አሉት ማለት ነው። መራጩ ሕዝብ ድምፁን በሚሰጥበት ወቅት በሥራ ላይ ያለው ካቢኔ ከጥላ ካቢኔ ጋር በማወዳደር የትኛው ቡድን ይሻላል ብሎ ለመምረጥ ያመቸዋል። መንግሥትና ፓርቲ መደባለቅ እንደሌለበት ሁሉ የፓርቲው አስተዳደርና የጥላ ካቢኔው መደባለቅ የለባቸውም። ፓርቲና መንግሥትን የመለየት ሥራ ስልጣን ሳይያዝ ጀምሮ ማሳየት ይገባል።

አንድነት ፓርቲ በተቋቋመበት የመጀመሪያ ዓመት ይህ ሀሳብ ሲንሸራሸር እንደነበር አውቃለሁ፤ ጊዜው ግን ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አልበረም። በብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች አንድነት ፓርቲ ተዳከመ። ከዚያ ወዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጎበት ይሁን አይሁን አላውቅም።

አሁን ግን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ይህንን የኢትዮጵያ ፓለቲካ ድርጅቶቻችንን የማዘመን የዓመታት ህልም ተግባራዊ ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

D’r Tadesse Biru Kersmo

1 COMMENT

  1. ዶክተር፤
    እባክዎን ይቅርታ መረጃ ስላልነበረኝ ምዝገባ አልፎብኝ ነው፡፡ ይህን ኮርስ ለመውስድ ምን ምን ነገሮችን ማሟላት ይጠበቅብኛል፡፡ ከይቅርታ ጋር ስላልገባኝ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.