ድራዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምን ተፈጠረ

ከዛሬ 3 ቀን በፊት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተፈጠረው ችግርን በተመለከተ

መንስኤው፦

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፌደራል ፖሊስ በቋሚነት የፀጥታ ማስከበር ስራ ይሰራል። ባሳለፍነው ዓርብ ዕለት ግን ከዚህ ቀደም የነበሩት ፖሊሶች በአዳዲስ የፌደራል ፖሊስ አባላት ይተካሉ። የፌደራል ፖሊስ አባላቱ ወደ ግቢው ሲገቡ ምንም ከተማሪ ተወካዮች ጋር ትውውቅ አልተደረገም፤ ከአመራሩም ጋር ምንም ትውውቅ አልተደረገም። እነዚህ ፀጥታ አስከባሪዎች ሲገቡ የላይኛው አመራርም ሆነ የተማሪ ተወካዮች የሚያውቁት ነገር አልነበረም።

እሁድ፦

እሁድ ዕለት በቶኒ በር በኩል ከእምነት ተቋማት ወደ ግቢው የሚገቡ ተማሪዎች ነበሩ። ከተማሪዎቹ መካከልም ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው ፅሁፍ ያለበት ቲሸርት ያደረገ ተማሪ ወደግቢው ለመግባት ይሞክራል። የፀጥታ አካላቱ እንዲህ አይነት ይዘት ያለው ልብስ ለብሶ መግባት እንደማይቻል ይገልፃሉ። ተማሪዎቹም ከዚህ ቀደም ያለምንም እገዳ እንደሚገቡ ይናገራሉ። በዚህ መሀል አለመግባባት ይፈጠራል። ከፌደራል ፖሊስ አንዱ ተማሪው የለበሰውን ልብስ የቦጫጭቀዎል፤ ተማሪውንም እራቆቱን እንዲቀር ያደርጉታል። በዚህ ድርጊት የተበሳጩ ሌሎች ተማሪዎች በፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ድንጋይ መወራወር ይጀምራሉ። ነገሩን ለማብረድ ፖሊስ ወደ ላይ ይተኩሳል። በዚህ መሃል አንድ የፖሊስ አባል በድንጋይ ይፈነከታል። ከዚህ በኃላ ነው እንግዴ ፖሊሶች ያገኙትን ተማሪ በየብሎኩ እየገቡ መደብደብ የጀመሩት። ብሄር፣ ማንነት ሳይመርጡ በግቢው ያሉት ተማሪዎች ላይ ድብደባ ይፈፅማሉ። የተማሪዎችን ድብደባ የሰሙት የተማሪ ተወካዮች ለከፍተኛ አመራሮች ደውለው በአፋጣኝ ይህ ድርጊት እንዲቆም ይጠይቃሉ። የግቢው አመራር ምንም የማድረግ አቅም አልነበረውም። መረጃውን ያደረሰኝ ወዳጄ እንደነገረኝ የአስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዘዳንት ጭምር በፌደራል ተመቷል።

ከብዙ ጥረት እና ድካም በኃላ ፌደራል ፖሊሶቹ እያደረጉ ያሉትን ነገር እንዲያቆሙ ይደረጋል። በድብደባው የተጎዱ ተማሪዎች በርካቶች ነበሩ፤ የደሙ የቆሰሉ ብዙ ናቸው። ጉዳት የደረሰባቸውም ከፍተኛ ፤ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ተብሎ ተከፍለዋል። ዛሬም ድረስ ራሱን ስቶ ሆስፒታል የሚገኝ ተማሪ አለ። ይህ የሆነው እስከ ቀኑ 6:00 ብቻ ነው።

√በግቢው ሀይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ማራመድ አይቻልም። አንዳንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሰራ ነው። ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ የተማሪዎች ህብረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በተሰላሰለ መንገድ ሲሰራ ቆይቷል።

በበር አካባቢና ሌሎች ቦታዎች ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የስራ ተዋረዱን ሲያስረዱኝ፦ ችግር ሲኖር በቅድሚያ ተማሪዎችን ጥበቃዎች ያናግሯቸዋል፤ ከመቀጠል የተማሪ ህብረት ጉዳዩን ያየዋል፤ ከአቅም በላይ ከሆነ ብቻ ወደ ፌደራል ፖሊስ ይጠቆማል። ባለፈው እሁድ ግን ይህን ተዋረድ የተከተለ ስራ አልተሰራም ምናልባትም ፌደራል ፖሊሶቹ አዳዳሲ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል።

ከሰዓት ምን ተፈጠረ…

ነገሩ በትንሹም ቢሆን በርዶ ነበር። ተማሪውም በግቢው ውስጥ ለነበረ የእግር ኳስ ጨዋት ወደ ስታዲየም ይሄዳል። የኳስ ጨዋታው ጥዋት በግቢው ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ነገር ተረስቶ በርካቶች የታደሙበት ነበር። በውድድሩ መሃል ችግር ይገጠራል። ችግሩ የተፈጠረው ከዚህ ቀደም በነበረ ቁርሾ እንደሆን ጉዳዩን ያስረዱኝ ተማሪዎች ገልፀውልኛል። በሜዳ ዙሪያ በተሰማው ወሬ በተማሪዎች መካከል አለመግባባት እና ግጭት ይፈጠራል።

√ከወር በፊት በሁለት ተማሪዎች መካከል የተፈጠረ የግል ፀብ ወደ ብሄር መልክ ተቀይሮ ችግሮች ተፈጥረው ነበር። በወቅቱ ችግሩን ለመፍታት ብዙ ጥረት ተደርጎ ነበር።

የዩኒቨርሲቲው ድክመት…

ከወር በፊት በነበረው አለመግባባት የማስታረቅ እና የማስማማት ስራ ሲሰራ ዋና ችግሩ የሚመለከታቸውን አካላት ላይ የማግባባት ስራ አልተሰራም። ተደብድበናል፤ ተበድለናን የሚሉትን አካላት ላይ የማስማማት ስራ አልሰራም። ይህ ድክመት ችግሩ ሙሉ በሙሉ እንዳይፈታ እና ዛራም ድረስ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ከጨዋታ በኃላ…

በኳስ ጨዋታ ሜዳው የተፈጠረው ችግር መልኩን ቀይሮ አድማሱን አስፍቶ ተማሪዎች እርስ በእርስ እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል። ችግሩ ሰፍቶ ሰኞ ትምርት እዲቋረጥ ተደርጓል። ሰኞ 4:00 አካባቢ ዳግም በተማሪዎች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፤ ተማሪዎችም ይጋጫሉ። በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ችግሩን ለመፍታት ውይይት ሲያደርጉ ነበር።

ማክሰኞ፦

በተመሳሳይ ማክሰኞ ዕለት ሰፊ ውይይት ሲደረግ ይውላል። 10:00 ገደማ የደህንነት ስጋት አድሮብናል፤ የምንጠይቀው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፤ ከፍተኛ ችግር አለ፤ ስርዓት አልበኝነት በግቢው ነግሷል ያሉ ተማሪዎች ሻንጣቸውን ይዘው ግቢውን ለመልቀቅ ይሞክራሉ። የሚመለከታቸው አካላትም ተማሪዎችን ለማግባባት ይሞክራሉ ግን አልተሳካም። ዩኒቨርሲው ተማሪዎቹ ውጭ ቢወጡ ሌላ ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል በግቢው ውስጥ ሬጅስትራር አካባቢ ፍራሽ አውጥቶ አሳድሯቸዎል።

ዛሬም ችግሩ እንዳልተፈታ ሰምቻለሁ!
ተጨማሪ መረጃ ሳገኝ ወደእናተ የማደርስ ይሆናል።

ከTIKVAH-ETH

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.