ገበታ ለሸገር፡ “እራት ለመመገብ አይደለም የምንሄደው” በላይነህ ክንዴ

የዐፄ ምኒሊክ የግብር አዳራሽ
የዐፄ ምኒሊክ የግብር አዳራሽ

የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸውን የማልማት ሥራን ለመተግበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ታቅዶ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ተቋማት በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ብር በማበርከት የሚታደሙበት የእራት ድግስ ዛሬ ይካሄዳል።

‘ገበታ ለሸገር’ በሚል ስያሜ የተዘጋጀው የገንዘብ ማሰባሰቢያ የእራት ዝግጅት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የሚታደሙበት ሲሆን በዝግጅቱ ላይ ለመገኘት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተሳታፊዎች የተለያየ መታሰቢያ መዘጋጀቱ ተነግሯል።

• የ5 ሚሊዮን ብር እራት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር

ዛሬ የሚከናወነው ‘ገበታ ለሸገር’ የእራት ዝግጅት ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚጀመር ሲሆን ከዋናው የእራት ግብዣ ቀደም ብሎ የተለያዩ ግንባታዎችና ጥገና እየተካሄደበት የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበር የሚገኝበት ታሪካዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚደረግ ጉብኝት እንደሚኖር ታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የ’ገበታ ለሸገር’ የ5 ሚሊዮን ብር እራት ላይ ለመገኘት ከተመዘገቡ እንግዶች መካከል በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማራው የቢኬ ግሩፕ (በላይነህ ክንዴ ግሩፕ) ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ እንዱ ናቸው።

“ገበታ ለሸገር የልማት ሥራ ነው፤ እንደ አንድ ባለሃብት የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም መሰብሰቢያ የሆነችው ሸገር እንድትዋብ እንዲትለወጥ ፍላጎታችን ነው” የሚሉት አቶ በላይነህ ዓላማውን በመደገፍ ያለምንም ማመንታት ገንዘቡን እንደከፈሉ ይናገራሉ። እራቱ ላይም ይህንን ዓላማ ለማስተዋወቅ እንደሚገኙ ገልፀው “በአጋጣሚውም እራታችንን እንጋበዛለን” ብለዋል።

• የማትተነፍሰው ከተማ: አዲስ አበባ

“ምግብ ለመመገብ አይደለም የምንሄደው” የሚሉት አቶ በላይነህ “ሃብት ያለው ሰው በሕብረት ሌሎች ከተሞችንም ካለማ አገር ያድጋል” የሚል ሃሳብ አላቸው። የዚህ እራት ዓላማውም የልማት ነው ሲሉ አክለዋል።

የፕሮግራሙ ዝርዝር ባይደርሳቸውም ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት እንዲገኙ የግብዣ ወረቀት ደርሷቸዋል። በፕሮግራሙም ላይ ተገኝተው በሚኖረው መርሃግብር ላይ እንደሚሳተፉ ነግረውናል።

Image copyright@PMETHIOPIA
አጭር የምስል መግለጫየወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የሚኖረው ገጽታ

ሌሎች የአፍሪካ ከተሞችን እንዳዩና በጽዳት የተሻሉ እንደሆኑ በቁጭት የሚናገሩት አቶ በላይነህ “አገር በግለሰብ ለማልማት ሊሞከር ይችላል፤ እንደዚህ በጋራ ሆኖ ማልማት ጠቃሚ ነው” በማለት ይህንን ዓላማ እንደደገፉ ገልጸዋል።

የእራት መስተንግዶውም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሚገኘው በታሪካዊው የአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ውስጥ እንደሚካሄድ የተነገረ ሲሆን እስካሁን ከሁለት መቶ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት በእራት ድግሱ ላይ በመታደም አስተዋጽኦ ለማበርከት መመዝገባቸው ተነግሯል።

• ”አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ናት” ከንቲባ ታከለ ኡማ

ሸገርን የማስዋብ ዕቅድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረ የሦስት ዓመታት ፕሮጀክት ሲሆን በዚህም ከእንጦጦ እስከ አቃቂ የሚዘልቅ የ56 ኪሎ ሜትር ርዝመትን የሚሸፍን በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ የሚገኙ ስፍራዎችን ለማልማት የታቀደ መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የታቀደው የአዲስ አበባ የወንዞችና የወንዞች ዳርቻን የማልማት ዕቅድ ተግባራዊ ሲሆን በተለያዩ የፕሮጀክቱ ሥፍራዎች ላይ በእራት ዝግጅቱ የታደሙ ሰዎች ስም በተናጠል ተጽፎ የሚቀመጥ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋርም የአንድ ለአንድ ፎቶ የመነሳት እድልን ያገኛሉ ተብሏል።

ይህም ፎቶግራፍ የአዲስ አበባን ገጽታ የቀየሩ ግለሰቦች በሚል ተሰባስቦ በአንድ ጥራዝ ላይ እንዲቀርብ ይደረጋል ተብሏል።

በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ‘ገበታ ለሸገር’ ላይ ከሚሳተፉት ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ በላይነህ ክንዴ “እንደ ግለሰብ፤ 5 ሚሊዮን ብር ስለከፈልኩ በእኔ ስም ቦታ ይሰየምልኝ ብዬ አላስብምም፤ መሆንም የለበትም፤ ስሜን ለማስተዋወቅ አይደለም የከፈልኩት” ይላሉ።

• አዲስ አበባ፡ የፈጠራ ማዕከል ለመሆን እየጣረች ያለች ከተማ

የዐፄ ምኒሊክ የግብር አዳራሽ
የዐፄ ምኒሊክ የግብር አዳራሽ

የእርሳቸው ፍላጎት በከፈሉት 5 ሚሊዮን ብር ልማቱ እውን ሆኖ ከተማው ሲለወጥና እድገት ሲመጣ ማየት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ ባቀረበው የግብዣ ጥሪም የንግድ ተቋማት ባለቤቶችና አመራሮች እንዲሁም የዓለም አቀፍና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በዚሁ የእራት ዝግጅት ላይ እንዲታደሙ ጋብዟል።

በቫርኔሮ ኩባንያ የሚከናወነው የአዲስ አበባን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ይለውጣል ተብሎ የታሰበው ፕሮጀክት በ29 ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወን ሲሆን በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለታል።

ሥራው የአዲስ አበባ ከተማን ለሁለት ከፍለው የሚያልፉ ወንዞችን መሰረት ያደረገ ሲሆን ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ ያለውን 56 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ነው።

የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎች ልማት ሥራ ሲጠናቀቅ 4 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የተነገረ ሲሆን፤ በውስጡም አስፈላጊው ነገር የተሟላላቸው የመዝናኛ፣ የመጓጓዣ፣ የንግድ ማዕከላትና አረንጓዴ ሥፍራዎች ይኖሩታል ተብሏል።

BBC Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.