“ ወቅቱ በቆሎ የምንዘራበት ቢሆንም የተከሰተው የሠላም መደፍረስ ግን ለሕይወታችንም አስጊ ሆኗል፡፡” ቻግኒ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮች

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የፀጥታ ችግር ብዙ ዜጎች ከቀያቸው በመፈናቀላችው የእርሻ ወቅታቸውን ያለ ሥራ በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከማንዱራ ወረዳ ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮችም ከአምስት ሺህ በላይ ከብቶችን ይዘው ከመኖሪያቸው እንደራቁ ተናግረዋል፡፡

“ሕዝቡ እያሳየን ላለው ድጋፍ ምሥጋና ይገባዋል፤ ነገር ግን ለሰውም ለእንስሳቱም መዋያ ቦታ አጥተናል” ነው ያሉት ተፈናቃዮቹ፡፡ በማንዱራ ወረዳ ከ33 ዓመት በላይ ኑሪያለሁ ያሉት አንድ ተፈናቃይ ደግሞ “ለዘመናት አብረን የኖርነውን የአመራሮች ሥነ-ምግባር የጎደለው ሥራ ነው ለዚህ የዳረገን፤ አሁንም መንግሥት እረፉ ሊላቸው ይገባል” ብለዋል፡፡

የጓንጓ ወረዳ ቢዝራካኒ ቀበሌን ጨምሮ ብዙ ቦታዎችም የፀጥታ ችግር ያለባቸው መሆናቸውን አስተያዬት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

የጓንጓ ወረዳ አስተዳደር እና ፀጥታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሃምሳ አለቃ አብዮት መለሰ ደግሞ “ሁለቱ ሕዝቦች ለዘመናት አብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ጉዳዩም የሕዝቦች ሳይሆን ዓላማቸው እንዲሳካ ፍላጎት ያላቸው አካላት ያቀጣጠሉት ግጭት ነው፤ ግጭቱን ለማርገብ በሁለቱም መንግሥታት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው” ብለዋል፡፡ “ሕዝቡም በወሬ እና በአሉቧልታ መታወክ የለበትም፤ አካበቢውን ለማረጋጋት እየሠራን ነው” ብለዋል ኃላፊዉ፡፡

የአካባቢ የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን እና ችግሮች በውይይት እንደሚፈቱ ተገልጿል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የአዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ ደግሞ ‹‹የሁለቱንም ሕዝቦች ወደ ሠላም ለማምጣት በተፈጠረው መድረክ ልክ ሠላም ማምጣት አልተቻለም፡፡ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት ሠላም እንዲረጋገጥ መሥራት አለበት›› ነው ያሉት፡፡

ከሕዝቡ ባገኘነው መረጃ መሠረት ‹‹ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ ሕዝቡ ወደ ግጭት እንዲገባ የሚገፋፉ አካላት እንዳሉ ጥቆማ ደርሶናል›› ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ተንቀሳቅሶ ሀብት የማፍራት መብቱን መነፈጉን ያስገነዘቡት ኃላፊው አካባቢው ወደ ተሻለ መረጋጋት እንዲመለስ እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

#አብመድ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.