የ ‘ምን ልታዘዝ’ ድራማ ሰምና ወርቅ

ኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ድራማዎች በተለያየ ዘመን ታይተዋል፤ ‘ባለጉዳይ’፣ ‘ማን ገደላት’፣ ‘ገመና’፣ ‘ቤቶች’ እና ሌሎችም ትችት አዘል የቴሌቪዥን ድራማዎች ይጠቀሳሉ።

የቅርብ ጊዜው ‘ምን ልታዘዝ’ የነዚህን ድራማዎች ዝርዝር የተቀላቀለ ይመስላል። ከላይ የተጠቀሱት ድራማዎች ማኅበራዊ ህጸጽን አጉልተው ሲያሳዩ ‘ምን ልታዘዝ’ በአንጻሩ ፖለቲካዊ ሽሙጥን በሚገባ ይጠቀማል።

ድራማው በቴሌቪዥን መተላለፍ የጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ በገነነበት፣ የፖለቲካው አካሄድ ሚናው ባልለየበት ወቅት ነበር። ድራማው በዚህ ወቅት በድፍረት ፖለቲካውን መሸንቆጡ ተወዳጅ አድርጎታል።

የ ‘ምን ልታዘዝ’ መቼት አንድ ካፌ ነው። የካፌው ባለቤት እትዬ ለምለም ቢሆኑም በበላይነት የሚመሩት አቶ አያልቅበት ናቸው።

አቶ አያልቅበት፤ የካፌው አስተናጋጆች፤ ዕድል፣ የንጉሥና ደግሰውን ክልል ከፋፍለው እንዲሠሩ መድበዋቸዋል። በየወቅቱም ስብሰባ ይወዳሉ። ይህንን ‘የካፌ ዓለም’ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚያነፃፅሩ ተመልካቾች አሉ።

ነፃነት ተስፋዬና ታመነ በአመቻቸው ጊዜ ሁሉ ድራማውን ይከታተላሉ። ድራማው የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እየተከታተለ የሰላ ትችት እንደሚያቀርብ ይስማማሉ።

ረጋ ያለው፣ ጢማሙ ባሬስታ ዳኜ፣ ጋዜጣ አዟሪው ሱዳን፣ የልጥ ፓርቲ ሊቀ መንበር፣ ጨርቦሌ፣ ደራሲው ዶኒስና ሦስቱ የባንክ ሠራተኞች የድራማው ገፀ ባህሪያት ናቸው። ሌሎች ቋሚና አልፎ ሂያጅ የካፌው ደንበኛ ገፀ ባህሪያትም አሉት።

ታዲያ ታመነ በገፀ ባህሪያቱ ብሽቅ ይላል። ለምን? ስንለው “ይልፈሰፈሱብኛል” ነው መልሱ።

ካፌው ውስጥ በየሳምንቱ የሚነሱ ጉዳዮች ፖለቲካዊ ናቸው። በየወቅቱ አገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ነገሮች በአቃቂር ተለብጠው፣ በሳቅ ተከሽነው ወደተመልካች ይደርሳሉ።

ድራማው በፋና ቴሌቪዥን መቅረቡ ለአንዳንዶች ግርምት አጭሯል። ታመነ እንደሚለው፤ ማኅበረቡ ውስጥ ያለውን፣ የሚብላላውን ነገር ከማቅረብ ባለፈ ጠንካራ መልእክት የለውም። ነፃነትም በሀሳቡ ይስማማል። ሆኖም ገፀ ባህሪያቱ የገሀዱ ዓለም ወካይ መሆናቸውን ያምናል።

ድራማው የብዙሀን መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ታመነና ነፃነትን የሚስማማ ሌላው ጉዳይ ነው።

የምን ልታዘዝ ድራማ ተዋንያን (ደግሰው፣ እድልና የንጉስ)Image copyrightDIRE TUBE

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊና ለዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴአትር ያስተማሩት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፤ የ ‘ምን ልታዘዝ’ ፖለቲካዊ አቃቂር ለኢትዮጵያ የድራማና ቴአትር ዘርፍ አዲስ አይደለም ይላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው ቴአትር ፖለቲካዊ ይዘት እንደነበረውም ያጣቅሳሉ።

በጅሮንድ ተክለኃዋርያት ተክለማርያም የጻፉት ግንባር ቀደሙ ኢትዮጵያዊ ቴአትር የ ‘አውሬዎች ኮመዲያ መሳለቂያ’ ከአንዴ በላይ ለመታየት እድል አለማግኘቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት አቶ ዘሪሁን ብርሃኑ ይናገራሉ። ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ ባለስልጣናት በጭብጡ በመቆጣታቸው ነው ይላሉ።

ትችትን በቴአትር ማቅረብ ለኢትዮጵያውያን አዲስ እንዳልሆነ ሁለቱም ይስማማሉ። “ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ ትችትን በቅኔ ማቅረብ አዲስ አይደለም” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፤ ሸፈንፈን አድርጎ ማቅረብ ሥነ ጽሁፋዊ ባህላችን ነው ሲሉ ያክላሉ።

አቶ ዘሪሁንም ‘ምን ልታዘዝ’ እውነት አለው፤ ውበትም እንዲሁ በማለት ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ባለጥርሱምን ልታዘዝ

በየሳምንቱ እሁድ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የቴሌቪዥን ድራማ፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን እግር በእግር ተከታትሎ ለመተቸት እድሉን አግኝቷል።

በፋና ብሮድካስቲንግ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ዋና አዘጋጅና የተባባሪ ፕሮግራሞች ክፍል ኃላፊ ዘካሪያስ ብርሃኑ፤ የ ‘ምን ልታዘዝ’ ፕሮፖዛል ወደቢሯቸው ሲሄድ አላማው ፖለቲካዊ ጉዳዮችን መተቸት እንደነበር ያስታውሳሉ። የፋና ብሮድካስቲንግ ባለሙያዎች ከደራሲዎቹ ጋር በመወያየት አሁን ያለውን ቅርፅ እንዲይዝ ማድረጋቸውንም ያስታውሳሉ።

አውዳዊነትንና አሁናዊነትን አጣምሮ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትችቱን ለማቅረብ እድል ያገኘው ‘ምን ልታዘዝ’፤ ተወዳጅነት ካተረፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ብዙሀኑ በሚመለከቱት ቴሌቪዥን መተላለፉ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ይናገራሉ።

አቶ ዘሪሁን በበኩላቸው፤ ‘አይነኬ ናቸው’ የምንላቸውን ጉዳዮች የደፈረ ነው ይላሉ። ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ፖለቲካውን ደፍረው በጥበብ ሥራቸው የነኩ ባለሙያዎች እየተሳደዱ፣ ጫና ውስጥ የመውደቅ እድላቸው ሰፊ ነበር በማለት የበጅሮንድን ተውኔት ይጠቅሳሉ።

በአሁን ሰዓት ቴሌቪዥን ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ስለሚታይ ‘ምን ልታዘዝ’ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመታየት እድል አግኝቷል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፤ ለመወደዱ እንደምክንያት ያቀረቡት ሌላ አስረጅ የደራሲያኑን ችሎታ ነው።

የምን ልታዘዝ ድራማ መግቢያ ጽሑፍImage copyrightDIRE TUBE

የሰላ ትችት የሚቀርብበትን መንገድ በደንብ አውቀውታል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ይህንን ገፀ ባህሪቱን በማንሳት ያስረዳሉ።

ገፀ ባህሪያቱ ቋሚ ሆነው፣ ባህሪያቸውም ታውቆ ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን ያቀርባሉ። አቶ አያልቅበት፣ ጨርቦሌ፣ ባሬስታው ዳኜ፣ ጋዜጣ አዟሪው ሱዳን በባህሪያቸው ይታወቃሉ። በባህሪያቸውና በድርጊታቸውም ያስቁናል።

አቶ ዘሪሁን እንደሚናገሩት፤ ተመልካች በገፀ ባህሪያቱ ድርጊትና ንግግር ከመሳቅ ባሻገር፤ ንግግራቸውን ሳይዘነጋ ለቀናትና ለሳምንታትም ፈገግ ይላል።

የ ‘ምን ልታዘዝ’ ጉልበት የሚመነጨው በማሳቁ ወይንም በመተቸቱ ብቻ ሳይሆን፤ በየሳምንቱ የሚታወሱ ቃለ ተውኔቶች እንዲሁም ክስተቶች በማቀበሉ መሆኑን ሁለቱ ባለሙያዎች ይስማማሉ።

በገፀ ባህሪያቱ ስም አወጣጥ፤ ልጥ (ልማታዊ ጥምረት) እና ጨርቦሌ (ከጨርቆስ እስከ ቦሌ) ውስጥም እንዲህ አይነት ነገር ይስተዋላል ሲሉም ያክላሉ።

“ጉልበቱ ሳቅ መፍጠር ሳይሆን ትችት መሰንዘር ነው” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፤ ሰዎች ሲስቁ ነገ ያንን ድርጊት ላለመደገም፣ መሳቂያ መሳለቂያ ላለመሆንም ትምህርት እየወሰዱ መሆኑን ይገልጻሉ።

‘ምን ልታዘዝ’ መጀመሪያ አካባቢ ፖለቲካውን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ጉዳዮችንም ይዳስስ እንደነበር አቶ ዘሪሁን ያስታውሳሉ። የፖለቲካው ሁኔታ ሲለወጥ ግን የድራማው ሂስም ጠንከር ማለቱን ይጠቅሳሉ። ጸሀፊዎቹ ካለው የፖለቲካ እውነታ መውጣት አይችሉም ሲሉም ያስረዳሉ።

አስቂኝ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ (ሲትኮም) ማኅበራዊ ጉዳይ የመሄስና ወቅታዊ ጉዳይ እያዋዛ የመተቸት ባህሪ አለው። ‘ምን ልታዘዝ’ ይህን ማሳካት መቻሉን ይገልጻሉ።

የደራሲያኑ አቋም መታየትና መከበር እንዳለበት “መሥራት የምንፈልገው ፖለቲካዊ ሳታየር ነው ካሉ አቋማቸው ሊከበር ይገባል” ሲሉም ያስረዳሉ። የፋና ብሮድካስቲንግ ባልደረባ አቶ ዘካሪያስም፤ የአገሪቱ ፖለቲካ ሲከር ፖለቲካውን አምርረው መተቸታቸው ተጠባቂ ነገር ነው ይላሉ።

የምን ልታዘዝ ድራማ ተዋንያን (ልጥ፣ ጨርቦሌ፣ ሱዳን)Image copyrightDIRE TUBE

ጥበብ እንደፈቺው ነው

ለአቶ ዘሪሁን፤ በድራማው ውስጥ በአልፎ ሂያጅም ሆነ በዋናነት የተሳሉ ገፀ ባህሪያት፤ እኛን መስለው እኛን አክለው የተሳሉ ሰዎች ናቸው።

ለረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ግን ‘ምን ልታዘዝ’ ኢትዮጵያዊ ብቻ አይደለም። ለኢትዮጵያውያን የቀረበ ዓለም ቢፈጥሩም፤ የሚቃኙት ግን በአፍሪካና በተቀረው ዓለም ላይ የሚካሄዱ አበይት ክስተቶችን ነው ይላሉ።

ገፀ ባህሪያቱ ሁሌም ከገሀዱ ዓለም ጋር በአቻነት የቆሙ ናቸው በሚለው ረዳት ፕሮፌሰሩም ሆነ መምህሩ አይስማሙም።

ጋዜጣ አዟሪው ዛሬ እከሌ የሚባለውን ጋዜጠኛ ቢመስል፣ ነገ ደግሞ ሌላ ጋዜጠኛ ይመስላል፣ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ሌላ ሰው ይወክላል። ተቃዋሚ ፓርቲውንም ሆነ አክቲቪስቱን የሚመስሉ ገፀ ባህሪያት ውክልናም ይለዋወጣል።

“የተፎካካሪ ፓርቲዎችንና የአክቲቪስቶችን ፅንሰ ሀሳብ ወክለው የተሳሉ እንጂ የአንድ ሰው ቅጂ ናቸው ብዬ አላስብም” ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ።

አቶ ዘሪሁን በበኩላቸው፤ ተመልካች የራሱን ትርጉም የመስጠት እድል እንዳለው መዘንጋት እንደሌለበት ያስታውሳሉ። በጎ ምላሽ እንደሚሰጠው ሁሉ ያልተገባ ትርጉም ተሰጥቶት ልንሰማ እንደምንችልም ያነሳሉ።

በድራማው ላይ የሚስተናገዱ አካላት የአንድ ክልል ወይም ክፍለ ከተማ ወካይ ናቸው ብሎ አስተያየት መስጠት አይቻልም ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ።

የተለያዩ ተመልካቾች ቅሬታቸውንም ሆነ ሙገሳቸውን ወደቢሯቸው መውሰዳቸውን የሚያስታውሱት አቶ ዘካሪያስ፤ “እንደተመልካች እከሌ እከሌን ይመስላል ማለት ከባድ ነው” ይላሉ።

ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ ድራማው ከፋና ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ጋር ይጣረሳል? የሚለው ሲሆን፤ አቶ ዘካርያስ ከፖሊሲያቸው ጋር እንደማይጋጭ ይናገራሉ።

በ ‘ምን ልታዘዝ’ ውስጥ ያሉ ገፀ ባህሪያት አንዳቸው ከሌላቸው የተለዩ ተደርገው ስለተቀረጹ የሚያፈልቋቸው ሀሳቦች የተለያዩ ናቸው። አቶ አያልቅበት ከጨርቦሌ፣ ደግሰው ከዕድል የተለየ ሀሳብ ያላቸው ገፀ ባህሪያት መሆናቸው ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ።

ይህ ልዩነት ገፀ ባህሪያቱ በቀላሉ በተመልካች አንዲለዩ ብቻ ሳይሆን፤ ግጭት ለመፍጠርና የድራማውን ታሪክ ለማንቀሳቀስ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

የገፀ ባህሪያቱ ሥነ ልቦና፣ ሞራልና ማኅበራዊ ሁኔታ ቁልጭ ብሎ የሚታይ በመሆኑ በተመልካች ዘንድ ገፀ ባህሪያቱን ከእውኑ ዓለም ሰዎች ጋር በማመሳከር ጨርቦሌ እንትና ነው፣ ልጥ ደግሞ እንትና ነው ይባላል። “ይህ የሆነው ገፀ ባህሪያቱ በደንብ ተደርገው ስለተሳሉ ነው” ይላሉ።

የምን ልታዘዝ ድራማ ተዋናይ ሚካኤል ታምራት (አያልቅበት) እና ሱዳንImage copyrightDIRE TUBE

 ‘ምን ልታዘዝ ድራማ የሚስቅ ተመልካች ምን ያተርፋል?

ድራማው ለማስተማር የተዘጋጀ አይደለም የሚሉት አቶ ዘካርያስ፤ ከማዝናናት ባሻገር የአገሪቱ ፓለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ የመተው ግብ አለው ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ በበኩላቸው፤ “ሥነ ጥበብ ሕሊናን በመሸንቆጥ፤ ሰልፍ ላይ ወጥቶ ድንጋይ ከመወርወር፣ መስታወት ከመስበርና ሕይወት ከሚጠፋ፣ ነገሮች እንዲስተካከሉ እድል ይሰጣል” ይላሉ።

ሥነ ጥበብ የመማር እድል ይሰጣል የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ ገፀ ባህሪያቱ ባደረጉት ነገር ስንስቅ እግረ መንገዳችንን እየተማርን መሄድ አለብን ይላሉ።

 ‘ምን ልታዘዝ የመተቸት ነፃነት ከየት መጣ?

‘ምን ልታዘዝ’ በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ዜና በሆኑ ማግስት ለሳቅና ለስላቅ ያበቃቸዋል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ የሆኑትን እንከኖች በጥበብ አሽቶና አዋዝቶ ያቀርባቸዋል። ይህ ነፃነቱን ከሌሎች ድራማዎች በተለየ ከወዴት አገኘው?

የሥነ ጥበብ ነፃነት ከመናገር ነፃነት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፤ ሕገ መንግሥቱ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ቢፈቀድም “በተለያየ ጊዜ በተለያየ ምክንያት አንዳንዴ ስንጠቀምበት ሌላ ጊዜ ስንተወው ነበር” ይላሉ። “በአሁን ወቅት በነጻነቱ ተናዶ ጡንቻውን የሚያሳይ ስለሌለ በጥሩ ሁኔታ እየኮመኮምን” ይላሉ።

አቶ ዘካሪያስ በበኩላቸው፤ ከድራማው ነፃነት የተነሳ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “ድራማው ሊቋረጥ ነው” እና “ደጋፊ አካላት ውላቸውን አቋረጡ” ተብሎ ሲወራ መስማታቸውን በመግለጽ፤ “ፋና ውስጥ ሁሌም የምንቆምለት ነገር የመናገር ነፃነት ነው። ድራማዎቻችንም የዚህ ማሳያ ናቸው” ይላሉ።

በጣቢያቸው ስለሚተላለፉ ድራማዎች ሁልጊዜ እንደሚወያዩ ገልጸው፤ ከሕዝብ የሚላኩ አስተያየቶች ላይ ከ ‘ምን ልታዘዝ’ ደራሲዎችና ፕሮዲውሰሮች ጋር እንደሚወያዩ ያስረዳሉ። የድራማው ቡድን አባላትም እርስ በእርስ እንደሚወያዩ ያክላሉ።

የምን ልታዘዝ ድራማ ተዋንያን (የንጉስ፣ እድል፣ ዳኜ)Image copyrightDIRE TUBE

ምን ሻሻል?

ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፤ ‘ምን ልታዘዝ’ ማኅበራዊ ሂሱንም፣ ፖለቲካውንም ኢኮኖሚውንም የሚሄስ ነው ይላሉ። “ወደአንድ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ጎን ያደላ ባለመሆኑ ደራሲያኑም ሆነ አዘጋጆቹም በእውቀት እንደሚሠሩት ያሳያል” በማለት የፈጠራ ችሎታቸውን ያደንቃሉ።

የደራሲዎቹን እና የፕሮዲውሰሮቹ ልምድ ለዚህ ድራማ ተወዳጅነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን አቶ ዘካሪያስም ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፤ የሀሳብ መደጋገም መመልከታቸውን በማንሳት፤ በአገሪቱ የሚታዩ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕፀፆችን እንደሚተቹ ሁሉ በግለሰቦች ዙሪያም ቢያተኩሩ መልካም ነው ይላሉ።

ገፀ ባህሪያቱ በፍቅር፣ በገንዘብ፣ በሥነ ልቦና፣ በአስተዳደግ ምክንያት ችግር ሊገጥማቸው እንዲሁም እርስ በእርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ምክንያት እንቅፋት ሊገጥማቸው ይችላል። እንደዚህ ያሉ በግለሰብ ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በማምጣት ለማሳየት ቢሞክሩ ሲሉም አስተያየት ይሰነዝራሉ።

አቶ ዘሪሁንም ፖለቲካዊ ጉዳዮች መብዛታቸውን ይጠቅሳሉ። ያላየናቸውን ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማሳየት እና ሀሳብ ማፈራረቅም መልካም ነው ሲሉ ይመክራሉ።

ለአቶ ዘካሪያስ ግን ፖለቲካዊ ሂስ የ ‘ምን ልታዘዝ’ ካስማ ነው። እናም ፖለቲካው እስካለ፣ የደራሲያኑ ብዕር እስካልነጠፈ ድረስ ይቀጥላል ይላሉ።

BBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.