ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም! በጣሊያን ወራሪዎች ያልተረታ ሕዝብ በባንዳዎችና በሹምባሾች የተወረረበት ክፉ ቀን ነው

ነብሰ ገዳዮች በከፉ አረመኔ ገዳዮች የተተኩበት የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ ደሙ የፈሠሰበትና አጥንቱ የተከሠከሰበት ጥቁር ቀንና የታሪክ ጉድፍ ነው::

“የፓለቲካ ጭቆና፣ የኢኮኖሚ ብዝበዛና ማህበራዊ ጉስቁልናን ለማስወገድ ጫካ ገባን” ብለው ወንድም በወንድሙ፣ እህት በእህቱ ላይ እንዲዘምት ያደረጉት የወያኔ መሪዎች ይፈልጉ የነበረው ፓለቲካዊ የሥርዓት ለውጥ ሣይሆን የፓለቲካ ሥልጣን ነበር:: በቂም በቀል የተቋጨ የግል ፓለቲካዊ እሣቤያቸውን ደብቀውና በወገን ደምና አጥንት ላይ ተረማምደው ለሥልጣንም በቁ:: ሥርዐቱን ሣይሆን ሠዎቹን ቀየሩ:: የፈራነው ደረሠ:: የጠላነው ነገሠ:: ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ማለትም ፍቅር፣ አብሮነትና መተሣሰብ በልዩነትና ጥላቻ ተተኩ:: በጥቁሩ ግንቦት 20 ጥቁር የደም ዕምባ አነባን::
“ለሕዝብ ነፃነት ነው የምንታገለው” ያሉን ወያኔዎች ጫካ ገብተው ለካ ሠውነታቸውን ትተው አውሬ ሆነው ነበርና እንደ አውሬ የሚያባላንን “የጎሣ ፌደራሊዝም” ሥርዐትና መርዘኛውን የጎሣ ፓለቲካ አፍንጫችንን ይዘው ይግቱን ጀመር:: ያንገራገረውን የሕዝብ ልጅ ሁሉ እየፈረጁ፣ እያሰሩና እየገደሉ ሥልጣናቸውን አጠናከሩ:: የሐገሪቱን ክብርና ታሪክ እያራከሱ ሃብትን እየዘረፉ ተንደላቀቁ:: ይህም ነበር አላማቸው:: የወያኔ መሪዎች በባንዳነት ለጣሊያን አድረው ኢትዮጵያዊ አርበኞችን ሲያስገድሉ የነበሩትንና የተቀጡትን ዘመዶቻቸውን ለመበቀልም ነበር::

እንዲህም ተባለ (ቴዲ አፍሮ):-

‘ለለውጥ ያጎፈረው ሥልጣን ላይ ሲወጣ፣
እንዳምናው ባለቀን ያምናውን ከቀጣ፣
አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ::’

ቴዲ አፍሮ ልክ ነው::

ባንዳና ሹምባሽ ወያኔዎቹ አሁን በሥልጣን ኮርቻ ላይ የሉም:: የደገሱልንና ያበረከቱልን “የጎሣ ፌደራሊዝም” ሥርዐትና መርዘኛውን የጎሣ ፓለቲካ አሁንም አለ:: ወያኔ ሞተ የምንለው ይህ የጎሣ ፓለቲካ እንደ ናዚዝምና ፋሺዝም በሕግ ሲታገድን የድንጋይ ዘመን ሥርዐት በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ሲተካ ብቻ ነው::

ግንቦት 20ን ልናከብር የምንችለው ሐገረ ኢትዮጵያ በባንዳዎችና ሹምባሽ ወያኔዎች መወረሯን በፀጋ ስንቀበል ብቻ ነው:: ግንቦት 20ን ልናከብር የምንችለው የጣሊያንንም ወረራ “ትክክለኛ” ነው ብለን መቀበል ስንችል ነው:: ግንቦት 20ን ልናከብር የምንችለው የተወረረ ሕዝብ የወራሪዎቹን ወረራ “ሕጋዊነት” ሲቀበል ብቻ ነው::
በድምሩ ግንቦት 20 ኢትዮጵያ ሐገራችን በቂም በቀልና በሥልጣን ጥም የሠከሩ ወያኔ ሽፍታዎች እንደ አንበጣ የወረሯትና ሐገራዊ ሰብሏን የጎዱበት ቀን ነው::

ግንቦት 20 ትቶልን የሄደው ትምህርትና ተመክሮ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ካልመጣ በስተቀረ በሥልጣን መንበሩ ላይ መሪ ግለሰቦች ቢቀያየሩ የሕዝብ መብትና ነፃነት መከበር እንደማይችልና ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትና የሕግ የበላይነት ‘ላም አለኝ በሠማይ’ መሆኑን ነው!

መብትና ነፃነት የሚረጋገጠው በመሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ብቻ ነው!

ግንቦት 20 የወያኔ ወራሪዎች “የድል ቀን”)፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ የመከራ ምዕራፍ የተጀመረበት ክፉ ቀን ነው!

3 COMMENTS

 1. በአስመራ የሃገሪቱ ብቸኛ መሪ ሲናገሩ ከስደትና ከሞት የተረፈው ህዝብ ይበልጡ ሴትና ሽማግሌ እልል ሲሉ መስማት እንዴት ልብን ያደማል። እልል የሚባለው ግን ለምኑ ነው? በአዲስ ባበባ ጠ/ሚሩ በመቀሌ ሌላው መንግሥት ለአስመራ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፉ ተብለናል። ደስታው የቱ ላይ ነው? በሩ የተዘጋበትን ህዝብ እንዴት ነው እንኳን ደስ ያለህ የሚሉት? የኤርትራው ፕሬዚደንት ዲስኩር ምንም አዲስ ነገር የለበትም። ያው ልክ እንደ ወያኔ ጀግኖች ሆነን ይህን አረገን ያን ሰርተን እዚህ ደርሰን ይልና ትላንት ስልጣን ላይ እንደወጣ ስለ ኢኮኖሚ፤ መንገድ ሥራ ያነሳና ሁልጊዜም ስለሚወረፉት የውጭ ሃይሎች ወዘተ ተርኮ በፉከራ ያልቃል። በየቤቱ ያለው ጉድ ግን ሌላ ነው። ደግሞም የውጭ ሃሎች ካፈረሱት ይልቅ እኛው በውጭ ሃይሎች እየተረዳን ያፈረስነው ይበልጣል። አተኩሬ የኤርትራውን መሪ ስመለከት ሳዳም ሁሴንን ያስታውሱኛል። እሱም አለም የምትሽከረከረው በእኔ ዙሪያ ነው ብሎ እያለ ሳያስበው የገመድ ራት ሆነ። አምባገነኖች ጊዜን ማንበብ አይችሉም። ሞታቸውም በስደት ወይም በሃገር ውስጥ በግፍ ተሰቃይቶ ነው። የአቶ ኢሳያስ እድል ፈንታም ከዚህ እንደማይዘል ቆይተን እናያለን። ጊዜ ለኩሉ ይል የለ ግዕዙ!
  የትግራዪ ወያኔ ሃርነት በትግራይ ህዝብ መነገድ የጀመረው ገና ጫካ እያለ ቢሆንም ዛሬም በህዝቡ ስር ከወንጀል ተጠልለው የአዲስ አበባውን መንግስት በመናቅ ልክ እንደ አንድ ሃገር እኔን ስሙኝ ማለታቸው የውጭ ዲፕሎማቶችን ሁሉ እያሳሰበ መጥቷል። ወያኔ ከጣሊያን ፋሽስት የከፋ ድርጅት ስለመሆኑ የራሳቸው ሰዎች ከበረሃ እስከ ከተማ ታሪክ የሚሉትን ማዳመጥ በቂ ነው። ይህ አልበቃ ካለ በየስርቻው ተጥለው በወያኔ ግፍ የደረሰባቸውን ወገኖች ገመና ማዳመጥ ይቀላል። አሁን በአንድ አውሮጳ ሃገር የምትገኝ አንዲት ኢትዮጵያዊት ትጥቅና ስንቅ ከሱዳን ሆነሽ ለተቃዋሚ ታቀብያለሽ ተብላ በሱዳንና በወያኔ የስለላ መረብ ውስጥ ተጠልፋ የተፈጸመባትን አረመኔያዊ ድርጊት ስትተርክ መስማት መፈጠርን ያስጠላል። የወያኔው ሰላይ ቁጭ ብሎ እያየ እርሷ እየተማጠነች ነበር ለሱዳን ወንዶች መቀለጃ ያደረጋት። ያው ከደረሰባት ሰቆቃ የተነሳ ዛሬ ያቺ ሴት ጤነኛ አይደለችም። ከደርግ የመከራ ግፍ አወጣናችሁ እያለ … የሞተ እያስቆፈረ ደረት የሚያስደቃው የወያኔ ፓለቲክ ከደርግ በእጅጉ የከፋ በሃገራችን ውስጥ ተደርጎ የማይታወቅ በደል የፈጸመ ድርጅት ነው። ለዚህ ድርጅት ነው በየአመቱ ከበሮ እየተመታ የነጻነት ቀን የሚከበርለት? የነጻነት መስፈርቱ ምን ይሆን? ጥፍር መንቀሉ፤ የሰው ብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠሉ፤ በእስር ላይ ያሉ ሴትችን በጋርዮሽ መድፈሩ፤ በወንዶች ሶዶማዊ ተግባር መፈጸሙና በዘርና በጎሳ እንዲሁም በቋንቋ ህዝብን ከፋፍሎ ማፋጀቱ ያ ነው ከበሮ የሚመታለት? የእብዶች የነጻነት ቀን! በቅርቡ ኦሮሚያ ከሌለች ኢትዮጵያ አትኖርም ሲባል ሰማሁ። ቀደም ሲል ደግሞ ትግራይ ከሌሌች ይህች ሃገር ሃገር አትሆንም ይሉናል። እስቲ ይገንጠሉ እና ይሞክሩት። እንደመሳፍንት ዘመን አይደል እንዴ አሁንስ የሆነው? የክልል ፓለቲካ በየጎራው ባንዲራ እያውለበለበ እንተ ውጣ አንቺ ውጪ እየተባለ ሰው ለመከራ የተዳረገው? የሚያሳዝነው የትምህርት ተቋማት እንኳን ሳይቀሩ የዘረኞች መጠቀሚያ መሆናቸው ነው። የወያኔ ግንቦት 20/1983 በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ጥቁር ነጥብ እንጂ ነጻነትን አላስመጣም። ወያኔ ሃገርን የሸጠ፤ ገንጣይ ሆኖ ያስገነጠለ፤ ለራሱ ብቻ የሚኖር ህብር የሆነ ሃገራዊ ስሜት በውስጣቸው የሌለ የደም አፍሳሾች ጥርቅም ናቸው። በመሆኑም አንገት አልባዋ ሃገር በሻቢያና በወያኔ ሴራ ትርምሷ የወጣ አፍራሽን አፍራሽ የተካበት የጨለማ ዘመን ነው። የአስመራው የጠ/ሚ አብይ ጉብኝት፤ የኤርትራው የተደጋጋገመ የማህል ሃገር ጉብኝት ከሰላም ጋር ምንም አያገናኘውም። ኢሳይያስ ወያኔን ለማሳፈር የተጠቀመበት የፓለቲካ ታክቲክ ነው። ኢሳይያስ ለኢትዮጵያ መልካም ነገርን አስቦ አያውቅም። ሊያስብም አይችልም። በዘመኑ ሙሉ ጥላቻ የተሞላ ሰው በአንድ ሌሊት የመልአክት ክንፍ አያወጣም። ሞኙ የሃገሬ ህዝብ ግን እውነት መስሎት ጨፈረ፤ ዘመረ፤ አመሰገነ። እባብ እባብነቱን አይለውጥም። ዛሬ ድንበሮች ተዘግተዋል፤ የሻቢያ ሰራዊት ወደ ድንበር ተጠግቷል እንባላለን። ሻቢያ በስልጣን ለመኖር ጦርነት አስፈላጊ ነው። አሁን ደግሞ ጓደኛውና አጋሩ የሱዳኑ አልበሽር ሲሽቀነጠሩ ማየት የራሱም ቀን እንደ ተቃረበ ስለሚያመላክተው ያው እንደ ደርግ አጥፍቼ ልፈርጥጥ ይል ይሆናል። አይ ሃገር አይ አፍሪቃ… አይ ነጻ መሆን.. ድንቄም ነጻ ትውጣ! አስመራም ሆነ መቀሌ የሚኩራሩበት አንዲትም ነገር ለህዝባቸው አልተገበሩም። ያው ሰውን ማፈናቀል፤ መግደል፤ ማፈን፤ ለስደት መዳረግ ግን በረሃ እያሉም ሙሉ ስራቸው ነበር አሁንም ከሙሉ ስራ በላይ እየተሰራበት እንደሆነ ህዝባችን ያውቃል። የድሃ ልጅ ወታደር ሆኖ ለጦርነት ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሲኖር ሌሎች በገንዘብና በጉቦ በየአቅጣጫው እግሬ አውጪኝ በማለት ላይ ይገኛሉ። እውነታው ይህ ነው። ከበሮውና ዘፈኑ ስልችቶናል። ባርነቱ ይቁም! ስልጣንም ለአዲሱ ትውልድ አስረክቡ። ይብቃ.. የዘረፋችሁትን ይዛችሁ አርፋቹሁ ተቀመጡ። ወይም ከሃገር ውጡልን! በየአመቱ የምታረጉት የነጻነት ሰርከስ ይብቃ።

 2. where were you then? what did you do to reverse the anti Ethiopian process? The dog barks after the hyena left. I am not sure if you are not the current “TEDEMARI” which is the same woyane.

 3. My brother suggested I might like this web site.
  He used to be totally right. This submit truly made my day.
  You cann’t consider simply how so much time I had spent for this info!
  Thanks!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.