በሬውን ሊያልቡት ነው! – በላይነህ አባተ

ዋሽንት እየነፉ የእስስት ገሳ ለብሰው፣

ከብት እሚጠብቁ በግ እረኛ መስለው፣
ልክ እንደ ትናንቱ እንደልማዳቸው፣
ሳርን እያሳዩ በሬውን ሊያልቡት ነው፡፡

 

ሰማእታት ብሎ አዳም ሲጠራቸው፣
እርኩሳን የሆኑት ተጅብ ተወዳጅተው፣
ስብከት ቀጥለዋል ዛሬም ፃድቅ መስለው፡፡

 

በዜጋ ሰንሰለት እግሮቹን ጠፍረው፣
በአንድነት መዶሻ ፍሬውን ቀጥቅጠው፣
ብልቱን ቆራርጠው አራት ቦታ ተክለው፣
ጎልማሳውን በሬ ጾታውን ቀይረው፣
እንደ ጥገት እላም አሁንም ሊያልቡት ነው፡፡

 

ይጦቢ እምትባል ሳርን አሳይተው፣
በሬን እያሞኙ ወደ አፋፉ ወስደው፣
ተገደል አጣብቀው ዛሬም ሊልጉት ነው!

 

ጭንብልን አጥልቀው እንደ አንበሳ አግስተው፣
ለሰላሳ ዓመታት ፍጥረትን አታለው፣
እየዘረጠጡ በሬን ሊነክሱስት ነው፣
ጅቦች ተጥንብ አንሳ በጓሮ ተሻርከው፡፡

 

መከራን የዘሩት እኒያ ስልሳዎቹ፣
ወገሎች ሆነዋል ለሰላሳዎቹ!

 

ወይፈኖች በእምቢታ ቀንበሩን ሲሰብሩ፣
በሮች ተማነቂያ ኑ ግቡ ይላሉ፡፡

 

በሬውን በጋዲ በአንድነት ሸብበው፣
ደሞ እንደ ትናንቱ አንጠፍጥፈው አልበው፣
እምቦሳ ጥጃውን በርሃብ ሊፈጁት ነው፡፡

 

ሰባና ሰማንያ ቢሞላውም በሬው፣
መታለሉ አይቀርም ጮሌ ሳር ሲያሳየው፡፡

 

ተማነቂያ ገብቶ ሲመለጥ የኖረው፣
ሞፈር ተነድግሩ ሲጎትት የባጀው፣
ታፍኖ ሲያበራይ እድሜውን የገፋው፣
ለእምቢተኛ ወይፈን የጪንጫ እርሻ ሆነው፡፡

 

ኮርማ ሆይ በሬውን ፍጡም አትከተል፣
ማፈኛን ቦጫጭቀህ ማነቂያውን ስበር፡፡

 

ጅቡ ገነጣጥሎ በተራ እንዳይበላህ፣
ጆፌ እየጎተተ እንዳይዘነጥልህ፣
እስስት በምራቁ አግሮ እንዳይውጥህ፣
አካኬ ዘራፍ በል ልክ እንደ አያቶችህ፡፡

 

ወይፈን ትምህርት ውሰድ በሬን አትከተል፣
እንደ ስድሳዎቹ ገደል ይዶልሃል!

 

ሲመክሩት አይሰማ መከራው አይመክረው፣
ፍሬውን አፍርጠው በአንድነት ቀጥቅጠው፣
ጾታውን ቀይረው የጥገት ላም አርገው፣
ደሞ እንደ ትናንቱ በዜጋ ጋዲ አስረው፣
ሳርን እያሳዩ በሬውን ሊያልቡት ነው፣
ወይፈን መክትና አባትህን አድነው፡፡

 

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ግንቦት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.