በቅርስነት በሚታወቀው በደጃዝማች አምዴ አበራ ካሳ ቤት መፍረስ የተቆጬ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ጉዳይ አይዘናጋም!

አሥራት ሚዲያ በትናንትናው ዘገባው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ አራት ኪሎ የሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሊፈርስ እንደነበር/እንደሆነ የት/ቤቱ አስተዳደር፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆችን አነጋግሮ መረጃውን አድርሷል። ይህን ተከትሎ ማስተባበያ የሚሰጡ የታከለ ኡማ አስተዳደር “ጠባቂዎች” ዘገባውን ውሸት ነው ሊሉን ሲፍጨረጨሩ እያየን ነው።

በመሰረቱ ከማንም በላይ የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ናቸው። የትምህርት ቤቱን ሁኔታ በተመለከተ ከእነሱ በላይ ቅርብ የለም። እነዚህ አካላት ትምህርት ቤታቸው (ቅርስም ነው) ሊፈርስ መሆኑን በተመለከተ ስጋታቸውንና በተግባር ያዩትን ለመናገር ከእነሱ የተሻለ አለ ለማለት ያዳግታል። ትናንት ያደረጉትም ይህንኑ ነው። የት/ቤታቸው ሁኔታ ያሳሰባቸው መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆች ያለውን እውነታ ለህዝብ አሳውቀዋል። በዚህም መደመጥ ችለዋል። ይህን ተከትሎ አንዳንዶች “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” የሚለውን ረስተውና በእኔ አውቅላችኋለሁ ስሜት የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ ውሸት ተናጋሪ አድርገው ሲወቅሷቸው ይታያል።

በእርግጥ መምህራንና ተማሪዎች ከጊዜ ጋር ተሻምተው ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ት/ቤቱ አደጋ ሳይደርስበት ቀድመው መረጃውን ለህዝብ አሳውቀዋል። አሁን ምናልባት “ከተነቃ ይቀራል” በሚል ትተውትም ይሁን፣ ሌላ ምክንያት ኖሯቸው ትምህርት ቤቱ አይፈርስም እያሉ ነው። የሚፈለገውም ይህ ነው። ት/ቤቱ አይፍረስ!

ነገር ግን አስተዳደሩን ለቅርስ ተቆርቋሪ ለማስመሰል መሞከር ከንቱ ነው። ይኸው የታከለ ኡማ አስተዳደር የእቴጌ ጣይቱ መታሰቢያ ሐውልት ግንባታን የከለከለ መሆኑን አንረሳውም። የደጃዝማች አምዴ አበራ ካሳ ቤትን ያፈረሰ መሆኑንም እናውቃለን። ስለሆነም የሌለውን ስብዕና ልንሰጠው ብንሞክር ትዝብቱ ነው ትርፉ።
ይልቅ በቅርስነት በሚታወቀው በደጃዝማች አምዴ አበራ ካሳ ቤት መፍረስ የተቆጬ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ጉዳይ አይዘናጋም!

በላይ ማናየ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.