ኮሎኔል መንግስቱ ሀ/ማርያም ለአምባ ልጆች ደብዳቤ ጻፉ (ጌጡ ተመስገን)

የህፃናት አምባ ልጆች ማህበር የኮሎኔል መንግሥቱን ልደት ሊያከብር ነው።

የህፃናት አምባ ልጆች ማህበር የደርግ ሊቀመንበር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ልደትና የምስጋና ፕሮግራም በመጪው ሰኞ ሊያሰናዱ መሆናቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ጆኒ መርጊያ ለቢቢሲ ገለፀዋል።

ከዚህ በፊት ልደታቸውን በይፋ አክብረን አናውቅም የሚሉት አቶ ጆኒ ዘንድሮ ለማክበር የማህበሩን አባላት ያነሳሳውን ጉዳይ ይገልፃሉ።

ነገሩ ወዲህ ነው፤ ከወር በፊት በህፃናት አምባ ያደገና የማህበሩ አባል የሆነ ሰው ኮሎኔሉን ለማግኘት እርሳቸው በስደት ወደ ሚኖሩበት ዚምባብዌ ለማቅናት ይነሳል። ግለሰቡ ስሙ እንዲጠቀስ ባይፈልግም አካሄዱ ግን እርሳቸውን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ነበር።

እርሳቸውን ለማግኘት ቁጥጥሩና ጥበቃው ጥብቅ ቢሆንም በወንድማቸውና እዚያው ዚምባብዌ በሚኖር አንድ የህፃናት አምባ ልጅ አማካኝነት ፈቃድ ማግኘት እንደቻሉም ገልፀውልናል።

ታዲያ ማህበሩ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለእርሳቸው የሰላምታ ደብዳቤ ለመላክ አሰበ። በደብዳቤያቸው ላይም እንዲሁ በትክክል የተወለዱበትን ቀን እንዲነግሯቸው ጠይቀዋቸዋል።

አቶ ጆኒ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም የኮሎኔሉ የልደት ቀንና ከአገር የወጡበት (ግንቦት 13) ተመሣሣይ ነው የሚሉ መረጃዎች ይወጡ ስለነበር ትክክለኛ የልደት ቀናቸውን ለማወቅ ነው ብለዋል።

የማህበሩ ኮሚቴ የፃፉላቸው ደብዳቤ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ይዘት የለውም የሚሉት አቶ ጆኒ ደብዳቤው ልጅ ለአባቱ የሚፅፈው ዓይነት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ደብዳቤው ስለ ደህንነታቸው፣ ስለ ልጆቻቸው ሁኔታ የጠየቁበት፣ ቤተሰባዊ ሰላምታ ያቀረቡበትና የልደት ቀናቸውን የጠየቁበት እንደሆነ ይናገራሉ።

“ልደታቸውን ስናከብር እናስታውሳቸዋለን ብለን እንጂ ለምርምር ፈልገነው አይደለም” ሲሉም የልደት ቀናቸውን የጠየቁበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

አቶ ጆኒ እንደገለፁልን ከደብዳቤው ጋር ባህላዊ የአልጋ ልብስ፣ ግድግዳ ላይ የሚሰቀል የመስቀል ቅርፅ ያለበት ጌጥ እና ለባለቤታቸው ውብ አንችና ለእርሳቸው የሚሆን ባህላዊ ፎጣ ስጦታም ልከውላቸዋል።

እርሳቸውም እንደ አባት ምላሻቸውን እንደላኩላቸው አቶ ጆኒ ገልፀዋል።

በምላሹ በላኩላቸው ደብዳቤ ላይም በጥሩ ጤንነት ላይ እንዳሉ፣ የተጋነነ የጤንነት ችግር እንደሌለባቸው፣ በልጆቻቸው እንደተባረኩ፣ አምስት የልጅ ልጆች እንዳዩ፣ ሁል ጊዜ ስለ ሃገራቸው እንደሚያስቡና ሃገራቸውን እንደሚናፍቁ በመግለፅ መጨረሻ ላይ የተወለዱበትን ቀንና ዓመተ ምህረት የሰፈረበት አጭር ደብዳቤ ፅፈውላቸዋል።

“የተወለድኩት፡ በአዲስ አበባ ፡ እንደኢትዮጵያ፡ አቆጣጠር፡ በ1933.ዓ.ም፡ ግንቦት አስራዘጠኝ ቀን፡ነው።” ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ እንዳሰፈሩ አቶ ጆኒ ገልፀዋል።

ማህበሩም ቢሮ እንዳለውና እንደሌለው በመጠየቅም ቢሯቸው ላይ የሚያስቀምጡት የአፍሪካ ካርታ ያለበት ሰዓት ልከዋል።

ይህ ብቻም ሳይሆን የእርሳቸው ፊርማ ያረፈበት፣ ‘ለህፃናት አምባ ልጆች’፤ መልካም ንባብ’ የሚል ፅሁፍ ያለበት የመጀመሪያ መፅሃፋቸውን ልከውላቸዋል።

“በዋነኛነት እንደ ልጆች የሚሰሙን ነገሮች አሉ፤ በእርሳቸው ጊዜ በነበረው ሥርዓት ያልተገቡ ነገሮች ተከናውነዋል፤ ነገር ግን በዘመኑ በጣም ጥሩ ሥራዎችንም ሰርተዋል” የሚሉት አቶ ጆኒ ባለፈው ሥርዓት በአጠቃላይ ደርግ በሚል መንፈስ የእርሳቸው ሥራ መጥፎነት ነው የተሳለው ይላሉ።

በመሆኑም የህፃናት አምባ ልጆች ማህበር እርሳቸው በዘመኑ ከሰሯቸው በጎ ሥራዎች መካካል አንዱ የህፃናት አምባን ማቋቋም መሆኑን በመጥቀስንና መሰል ሥራዎችን በማንሳት የልደትና የምስጋና ፕሮግራም ለማዘጋጀት አስቧል።

ግንቦት 18/2011 ዓ.ም የተወሰኑ የህፃናት አምባ ልጆች በግል በነበራቸው የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ የኮሎኔሉን ልደት እንዳከበሩ ገልፀውልናል። ይሁን እንጂ ዋናው ማህበር በመጭው ሰኞ ሰኔ 2 ቀን/2011 ዓ.ም ፕሮግራሙን ለማካሄድ እንዳቀደ አቶ ጆኒ መርጊያ ነግረውናል።

“በፕሮግራሙ ላይ እንደማንኛውም ልደት ኬክም ዳቦም ይኖራል፤ በዘመኑ የነበሩ ሰዎችንና ሌሎች እንግዶችን ጋብዘን ሞቅ አድርገን ለማክበር ነው ያሰብነው” ብለዋል።

ፕሮግራሙ የሚካሄድበትን ሰዓትና ቦታ ጊዜው ሲቃረብ እንደሚገልፁ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በህፃናት አምባ ያደጉ ልጆች ቁጥራቸው ከ7 ሺህ በላይ ሲሆኑ አዲስ አበባ የሚገኙና የማህበሩ አባል የሆኑ ልጆች ቁጥር ስድስት መቶ እንደሚሆን የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ጆኒ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የህፃናት አምባ በቀድሞ አጠራር በሸዋ ክፍለ ሃገር ሀይቆችና ቡታጂራ አውራጃ፤ አላጌ በሚባል አካባቢ የተቋቋመ ሲሆን ወላጆቻቸውን በጦርነትና በሌሎች ምክንያቶች ያጡ ህጻናትን ተቀብሎ የማሳደግ ዓላማ ነበረው።

ህፃናት አምባው ‘ሰብለ አብዮት’፣ መስከረም ሁለት ኦጋዴን፣ ዘርዓይ ደረስ እና መንግሥቱ ኃይለማሪያም የተባሉ 5 መንደሮችም ነበሩት።

ምንጭ ቢቢሲ አማርኛ

2 COMMENTS

  1. Interesting story.

    But source, like other ferenji sources, should better be avoided.

    This “ነገሩ ወዲህ ነው፤” sounds not correct, better is
    “ነገሩ እንዲህ ነው፤”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.