የሶማሌው ም/ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ የፌደሬሽኑ የክብር እንግዳ እንዲሆኑ ጥሪያችን ነው! (አስግድ አረጋ)

ጸሐፊ ዳዊት ከበደ ወየሳ “ጥብቅ መረጃ -­ ጠቅላይ ሚንስትራችን… ስለምን አትላንታ አይመጡም?” በሚል ርዕስ 05/29/19 በዘ-­ሐበሻ ዩቱዩብ የለቀቁትን ለማዳመጥ እኔና ወዳጆቼ እድል ገጥሞን ነበር። ዶ/ር አብይ በዘንድሮው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት በዓል እንዲገኙ በስፖርት ፌደሬሽኑ በኩል የክብር ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር። በምላሻቸው በበዓሉ ለመገኘት እንዳልቻሉና በምትካቸው በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍጹም አረጋን እንደወከሉ አስደምጠውናል። የስፖርት ማህበርሰቡ የህንኑ ውክልና በአክብሮት እንደሚቀበለው ተስፋችን ነው። በዚህ አጋጣሚ በስፖርት ፌደሬሽኑ “ዘገያቸሁ ካልተባልን” በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ህይወት ውስጥ በጎ ተጸዕኖ እያሳደሩ እንዳሉ የሚታመንባቸው ዜጎችን በተጨማሪ የክብር እንግድነት በመድረኩ እንዲጋብዝ ጥያቄ እናቀርባለን። ይህ የክብር ግብዣ በዓሉን ለማድመቅም ሆነ ፤ ትርጉም ያለው መልዕክት ለታዳሚው ለማስተላለፍ ድርሻው ከፍ ያለ እንደሚሆን ነው። በዚህ መንፈስ መስፈርቱን የሟላሉ ብለን ከምናስባቸው አንዱና ተቀዳሚው የሶማሊ ክልል ም/ፕሬዘዳንት ሙስጠፉ መሐመድ ዑመር ናቸው።

 

በጠ/ሚንስትሩ የተወከሉት አምባሳደር ፍጹም በአሜሪካ የሀገሪቱ ምስለኔ እንደመሆናቸው፤ ውክልናቸውም ሆነ መልዕክታቸው የመሪውን መንፈስ ፤ ኢትዮጵያዊነትን ፤ አበክሮ በመዘከሩ ላይ እንደሚያተኩር ግምታችን ነው። የተቀበሉት አደራ በስራ ቆይታቸው ዘመን በዲያስፖራው መሀከል በመገኘት የሚወጡት የዕለት ተዕለት ሀላፊነት ነው። እንዲህ በመሰሉ የበዓል አጋጣሚዎች፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለሆኑ የሀገሪቱ ልጆች እድሉን በመስጠት መድረኩን በጋራ መጋራቱ እሚያስከብራቸው ብቻ ሳይሆን፤ ለመድረኩ ህብረቀለም የሚያጎናጽፍ ፤ ለመልዕክታቸው ተጨማሪ እሴት የሚያክል ነው። ጠ/ሚንስትሩም ሆኑ አምባሳደሩ ይህንኑ ስሜት እንደሚጋሩ ተስፋችን ነው።

 

ሙስጠፋ መሐመድን ለክበር እንግድነት ስናቀርብ ምክንያታችን ዘርፈ -­ብዙ ነው። ስለ ዜጎች ሰብዓዊ መብት፤ የሀገር አንድነትና ሰላም ያላቸው ግንዛቤ እውቀት የዘለቀው ነው። እያራመዱት ባለው በዚህ ጽኑ አቋማቸው ዛሬ በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ ጥቂት የህዝብ መሪዎች ተርታ ይሰለፋሉ። በለውጡ ሂደት እንዲያስተዳድሩ የተረከቡት የሶማሊ ክልል ፤ የመላ ሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት በእጅጉ ሊያናጉ በሚችሉ አደጋዎች እየዋዠቀ የሚገኝበት ወቅት ነበረ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሳይቀር እንዲበተን በጠየቀው የክልላቸው የሚሊሺያ ሀይል፤ የዜጋው መብት አለቅጥ ሲረገጥ፤ የተፈጥሮ ሀብቱና ንብረቱ ሲዘረፍ የተስተዋለበት ነው። ነዋሪው በሀገሩ ስደተኛ የሆነበትና ክልላቸው መንግስት አልባ የመሰለበት ነበር። ፍትህ ሲጓደል እጁን አጣጥፎ፤ ፊቱን አዙሮ የተቀመጠ የጦር ሀይልንና፤ የጦር አለቆችን የታዘብንበት ከፉም አጋጣሚ ነበር። የተከበሩ ሙስጠፋና የትግል አጋሮቻቸው በጋራ ይህንን ቀውስ ባልተጋነነ የፕሮፖጋንዳ ድጋፍ ፤ በዕውቀት፤ በሙያና በክልሉ ባህላዊ ልምድ የመሩበት ብቃት ዕውቅናን እና ክብርን የሚመጥ ነው። ክልሉ ዛሬ በሀገሪቱ ካሉት ክልሎች በተሻለ የሰላምና ፍቅር አየር በእጅጉ እንዲነፍስ እየተሰራበት ያለ ነው።

 

ም/ፕ ሙስጠፋ ከቆሙበት ምድር ላይ ሆነው ኢትዮጵያን የሚያዩበት መነጽርም የፀዳ ነው ። ራእያቸው ግልፅና ትውልድ አሻጋሪ እንደሆነ ይሰማናል። “ማንነት ተፈጥሯዊ እንጂ ፤ ማንም መርጦ የማይወለድበት ፤ በህይወት ጉዟችን በበጎ የምንኮተኩተው ፤

 

ግን ወደ አፍራሽነት እንዳይሸጋገር የምንቆጣጠርው እንደሆነ ያስገነዘቡ ቀዳሚ የህዝብ መሪ ናቸው ። የምንመራበት የአስተዳደር ስርዓት በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ያለውን ማህበረሰብ በእኩልነት ካላስተናገደ ፤ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ካላረጋገጠ ፤ ስርዓቱ “አፓርታይድ” እንጂ ሌላ ስም እንደሌለው በድፍረት የነገሩን ናቸው። በገዥዎቸ እንጂ በህዝቦች መሀል ግጭት “እርሳቸው በሚያውቋት ኢትዮጵያ” እንዳላዩ ምስክርነታቸውን የሰጡን ናቸው። ተግባሩን በጽኑ እንድንዋጋው ምክራቸውን ለግሰውናል ፤ ጥሪም አቅርበውልናል። የክልላቸው ፓርቲ በክልሉ ነዋሪ ለሆነና ለክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ራእይ ፤ ሙያና ፍላጎቱ ላለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ከፍት መሆኑን በፓርቲያቸው ጉባዔ ያሳወቁን አስተዳዳሪም ናቸው።

 

ባጭሩ፤ ም/ፕሬዚዳንት ሙስጠፋና የትግል ጓዶቻቸው በክልላቸውና ከክልላቸውም ተሻግረው የፌደራል መንግስቱና የለውጡ አራማጅ ሀይሎች ጠንካራ ክንድ በመሆን ላሳዩት ተግባር ክብር ልንሰጣቸው የሚገቡ ናቸው። በመጪው ጉዟቸውም ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ እንዲታይ ፤ ዜጋው እንደ ዜጋ የሀገሩን መሪ መምረጥና ማውረድ የሚችልበት ስርዓት ስር ሰዶ እንድናይ ይበርቱ የምንላቸው፤ የትግሉን ችቦ በአደራ የምንሰጣቸውና ከጎናቸውም ለመቆም ቃል የምንገባበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ፤ ከእየአቅጣጫው የአክብሮት ጥሪያቸን ይድረሳቸው። የስፖርት ፌደሬሽኑ፤ ህብረ ብሄራዊው የአትላንታና አካባቢው ነዋሪ የጥሪውን ዓላማ ከግንዝቤ በማስገባት ለግብዣው መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በአክብሮት እንጠይቃለን። ዕለቱም እንደተለመደው ኢትዮጵያዊነትን በሚያስተጋባ የአንድነት ድምፅ ደምቆና በባንዲራዋ አሸብርቆ እሚውልበት እንደሚሆን ተስፋችን ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.