አስመሳዮች በበዙበት  ለቴዎድሮስ ካሳሁን /ግርማ ቢረጋ

ቀባጣሪው በበዛበት
አለም ሁሉ ባቦካበት
የንዋይ ፍቅር በአየለበት ።

የስሜት እሩጫ ግርግሩ
በተስፋ ስሜት መወጠሩ ።

ባሳበደው በዚህ ዘመን
አስተውለህ ግራ ቀኙን
ያንተ መስከን እንዴት ይሆን ።

ጭራውንም የሚቆላ
ያገኘውን የሚበላ
በበዛበት አሜኬላ ።

በአስራ ሰባቱ መርፌ ጠቅጥቀህ
ሲያሻህ እንደ ቢራቢሮ በረህ ።
እዩኝ እዩኝ ያላበዛህ
ሰከን ብለህ አስተውለህ።

ካበዱት ጋር ያልደባለቅክ
ከፍታህን ያላካፈልክ ።

በሙያህ ላይ ከፍ ብለህ
ማስመሰሉን ተጠይፈህ
ቃለ የገባህ ለህሊናህ ።

ሰውም አለው ብዙ አውደልዳይ
የሚመቸው ልታይ ልታይ
ግራ ቀኙን ዞሮ እማያይ ።

አንተ ብቻ በማስተዋል
የሆነውን ልብ ብለሃል ።

ያዩህ ሁሉ ሲደነቁ
ህፃናቱም ምን ሳያውቁ ።

ሲጮሁልህ ሲዘምሩ
ለአንተ ልባም ለአንተ ኩሩ ።

ገንዘብ ላለው  የሚሰግዱ
ማሸርገድን የሚወዱ
ሙያቸውን ያዋረዱ  ።

በዚህ ግዜ በፈሉበት
የንተ ነገር ብቻ እውነት ።

ፍቅርን በበዓሉ ፊዮሪና
የዲማን ጊዮርጊስ ምስጋና
ፍቅርን የተረክ ብላቴና ።

ፍቅርን ለፍቅረኞች በማወደስ
ያገር ክብሩን በሚኒሊክ ፣ በቴዎድሮስ ።

ሃገር ሕዝብን መውደድህን
ስትሰብክበት ችሎታህን ።

ጭራቸውን የሚቆሉ
በሁለት ቢላ የሚበሉ ።

አስመሳዮች በበዙበት
የአንተ ኩራት ባይኖርበት
ሆነን  ነበር የለየለት ።

ብለው ወጥተው ልታይ ልታይ
ጊዜው ሲያልፍ ደብቁኝ ባይ ።

በዚህ ጊዜ በበዛበት
መሸማቀቅ አንገት መድፋት ።

ቀና ብለህ የተራመድክ
ያልተደመርክ ያልተቀነስክ ።

ጁን 2019

ስቶክሆልም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.