“ምክንያታዊ ትውልድ – አለኝታ ለትውልድ! (Rationality Campaign)” – ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ
የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ
(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና
የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

የተለያዩ እውቅ ዓለም አቀፍ ምሁራን፣ ፈላሰፋዎችና የታሪክ ባለሙያዎች ስለምክንያታዊነትና ከምክንያታዊነት ጋር ተያያዥነት ስላላቸው ኹለንተናዊ ጉዳዮች ከፍትህ፣ ከነጻነት፣ ከዲሞክራሲ፣ ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ከማህበራዊ – ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች፣ ከሰላም፣ ከዕርቅ፣ ከግጭት አፈታት – – – ወዘተ አንጻር ብዙ ብዙ ብለዋል፡፡
ጠቅላል ባለ መንገድ ከሶስት አውዶች አንጻር ምክንያታዊነት የተሰጠውን ትርጓሜ ቃል በቃል የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ይኸውም፡-
I. ጥቅል ትርጓሜ (General Definition)
– (Definition of “rationality” from the Cambridge Advanced Learner’s Dictionary & Thesaurus © Cambridge University Press)
Rationality –
 the quality of being based on clear thought and reason, or of making decisions based on clear thought and reason
– (Definition of “rationality” from the Cambridge Academic Content Dictionary © Cambridge University Press)
 the existence of reasons or intentions for a particular set of thoughts or actions; reason
II. ከሜዲካል ትንታኔ አንጻር (Medical Definition of rationality)
– (Merriam-Webster on rationality)
1: the quality or state of being rational
2: the quality or state of being agreeable to reason
III. ከቢዝነስ አንጻር (Business Dictionary)

– Read more: http://www.businessdictionary.com/definition/rationality.html
– Mental state of a rational person characterized by
(1) Beliefs that are coherent (not contradictory) and compatible with the person’s experience within a given context,
(2) Purposeful (intended to produce certain results) behavior guided by means versus ends analysis,
(3) Decision making based on cost-versus-benefit (pain versus gain) evaluation and
(4) An overall optimization approach (utility maximization) expressed in attempts to maximize advantages or gains and to minimize disadvantages or losses.
እነዚህ ከላይ የተቀመጡ ጥቅል ትርጓሜዎች ከተለያዩ ኹለንተናዊ ነጠላና የስብስብ መገለጫዎች ጋር ካላቸው ትስስርና ፋይዳ አንጻር ብዙ የተባለላቸው፣ ብዙ የተጻፈባቸውና ብዙ ሊባልለት የሚችል ትልቅ ጽንሰ ሀሳብ መኾኑ ሊሰመርበት የሚገባ ነው፡፡
ምክንያታዊነት፡ የስሜታዊነትና የኢ-ምክንያታዊነት ተቃራኒ ነው፡፡ በዓለም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥም ኾነ በኛ የታሪክና ነባራዊ አኗኗር ውስጥ ያልታረሙ አንደበቶች፣ ያልታረሙ ጽሑፎች፣ ያልታረሙና ኢ- ምክንያታዊ ስሜት ቀስቃሽ ኹለንተናዊ እንቅስቀሴዎች ሕዝብን እንደሕዝብ ኹለንተናዊ የአካል፣ የሕይወት፣ የጊዜ፣ የጉልበት፣ የዕውቀት – – – ወዘተ ኹለንተናዊ መስዋዕትነት ማስከፈሉና በማስከፈልም ላይ መኾኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
ኢ-ምክንያታዊና ስሜታዊ ነገሮች ከግለሰቦች (ከመሪዎች፣ ከመሪነን ባዮች፣ ከገዥዎች፣ ከተወካዮች – – -)፣ ከቡድኖች (ለኾነ ዓላማ ከተሰባሰቡ ስብስቦችና ከተደራጁ አካላቶች) አልያም ከተቋማት (ከድርጅቶች፣ ከማሕበራት፣ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልኾኑ አካላት) በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ፣ በንቃትም ኾነ ያለ ንቃት፣ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ ሊመነጭ የሚችልና የቻለ ነው፡፡
በሀገራችን በተግባር በቀኝም ኾነ በግራ፤ በውስጥም ኾነ በውጭ የሚታዩ ጽንፍ የረገጡ ኢ-ምክንያታዊ ድርጊቶች መበራከትና በእጅጉ መንሰራፋት፤ ስሜታዊነት በእጅጉ መሠልጠንና አመክንዪ አልባ የሕይወት እንቅስቃሴ በዕለት ተዕለት ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ውስጥ በሰፊው በአኗኗር መንጸባረቅ ብሎም አሉታዊ ገጽታዎቹ የሚታዩ መኾናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
በጽንሰ ሀሳብም ኾነ በተግባር ደረጃ ኢ-ምክንያታዊነት የብዙ ግለሰቦችን ሕይወት ቀጥፏል፣ የብዙ ግለሰቦችን ጤናማና ሰላማዊ ሕይወት በጥብጧል፣ በተግባር የብዙ ግለሰብን ሕይወት ይጎዳል፣ ቤተሰብን ይበትናል፣ ትዳርን ያፈርሳል፣ ልጆችን ወላጅ አልባ ያደርጋል፣ ግጭቶች እንዲበራከቱ ያደርጋል፣ የማሕበረሰብን ኹለንተናዊ ትስስር ይጎዳል፣ ሀገርን እንደሀገር ሰላሟን ያናጋል፤ ከዕድገት ይልቅ በዝቅጠት ውስጥ እንድትኖር፤ በነጻነት የሚኖርባት ከመኾን ይልቅ የባሪያዎችና የገረዶች መጫወቻ እንድትኾን በር ይከፍታል፡፡
ኢ-ምክንያታዊነት ሕዝብን እንደሕዝብ ይጎዳል ብቻ ሳይኾን ተጎድተን በተግባር አይተነዋል፡፡ የጉዳቱም ኹለንተናዊ ዕዳ ከፋዮች ኾነናል፡፡ በሰላማዊ የምክንያታዊነት ዐውድ ሊፈቱ የሚችሉ ኹለንተናዊ ጥያቄዎች፣ ቁጣዎች፣ አስተያየቶችና ስሜቶች በኢ-ምክንያታዊ የስሜት ሂደት በመዋጣቸው ከውይይት ይልቅ ብጥብጥ፤ ከሀሳብ ይልቅ ዱላ፤ ከመደማመጥ ይልቅ ጩኸት፤ ከአርቆ ማሰብ ይልቅ ወደ ኃላ ማሰብ፤ ከመሠልጠን ይልቅ መሰይጠን ተበራክቶ ሀገር እንደሀገር መተኪያ የሌላቸውን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ከመቀጠፉ ባሻገር፤ በኢትዮጵያ ሊፈጸሙ ቀርቶ ሊታሰቡ አይቻልም የሚባሉ ነገሮች በአደባባይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተፈጽመዋል፤ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ የሕግ የበላይነት በብዙ ቦታዎች በኃይልና በስሜት ተሸንፎ ተመልክተናል፡፡
በርካታ አንደበታቸውን መጠበቅ ያልቻሉ ገዥዎች፣ የማሕበራዊ ሚድያ ንቁ ተሳታፊዎችና ጸሓፍቶች ያደረሱትን ጉዳት ታሪክ ዘወትር ሲዘክረው የሚኖር የሚታወቅ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ብዙዎች በኢ-ምክንያታዊነትና በስሜታዊነት የተነሣ ይሁዳና ይሁዳዊነት እጅጉን ተበራክቷል፤ ከከፍታ ወደ ዝቅታ፤ ከሙሌት ወደ መጉደል፤ ከክብረት ወደ እፍረት፤ ከአድናቆት ወደ ውርደት፤ ከሚፈልጉት ሕይወት ይልቅ ወደ ማይፈልጉት ሕይወት ገብተው ተጨማልቀው በአጭሩ ከመቀጨታቸውም በላይ የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ብዙዎች የብዙዎችን ሕይወት ከደስታ ይልቅ የስቃይ፤ ከተስፋ ይልቅ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ ከመኖር ወደ አለመኖር የለወጣቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ከፍቅር ወደ ጥላቻ የተለወጡ ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ በደልና በመበደል “እንደጀግንነት” እንዲታይ አድርጓል፡፡
ምክንያታዊነት ባልሠለጠነበት ሕዝብ ውስጥ እልም ያሉ ሃሰተኞች እንደእውነተኛ፤ አስመሳዮች እንደግልጽ፤ ገዥዎች እንደመሪ፤ ባሪያዎችና አሽከሮች እንደጌቶች፤ ገረዶች እንደነጻዎች፤ ጀብደኞች እንደጀግና፤ ባዶዎች እንደሙሉ፤ አላዋቂዎች እንደአዋቂ፤ አርቀው የማያስቡ እንደአርቆ አሳቢ፤ ትያትረኞች እንደእውነተኛ፤ ሰነፎች እንደጎበዝ፤ ከሃዲዎች እንደአማኝ፤ የቂም በቀልና የጥላቻ ባለቤቶች እንደአፍቃሪያን፤ ራስ ወዳዶች እንደለሌላው አሳቢዎች – – – ባጭሩ የብዙ ነገሮች ተገላቢጦሽ በተገላቢጦሽ እንዲታዩ ያስደርጋል፡፡ በማስደረግም ላይ ይገኛል፡፡
ምክንያታዊነት የአንድ የሠለጠነና ያልሠለጠነ ሕብረተሰብ የመለያ ድንበር ነው፡፡ የሠለጠነ ማሕበረሰብ አንዱና ዋነኛ መገለጫው በአኗኗራቸው ኹለንተናዊ ያለፈ፣ ያለና የሚኖር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ጤናማ የግል፣ የፈጣሪ፣ የመሰል፣ የአካባቢና የተፈጥሮ ሰላማዊ ግንኙነት ያለው ኾኖ ስናገኘው በአንጻሩ የኾነ ማሕበረሰብ ደግሞ በማስመሰል፣ በውሸትና በኹለንተናዊ ግጭቶች ውስጥ የሚኖር ኾኖ ይገኛል፡፡
የሀገራችንን ነባራዊ ወቅታዊ ኹኔታ መኾን ካለበትና ሊኾን ከሚገባው ይልቅ እየኾነ ካለው ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ አንጻር ስንመለከት እጅግ በጣም የተለያየ፣ ፈጽሞ ሊቀራረብ የማይችል፣ አብሮ ሊያሰራ የማይችል፣ ፍጹም ተቃራኒ ሀሳብና አቋም ያላቸው ኃይሎችና አካላቶች ሕብረት ፈጥረውና ሕብረት ፈጥረናል ብሎም ተስማምተናል ሲሉ መስማት የተለመደ ከኾነባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ ከምክንያታዊነት አንጻር ያለንበትና የነበርንበት መስተጋብር የሚጠቀስ ነው፡፡

በኢ-ምክንያታዊነትና በስሜት የሚነዳ ትውልድ ከዕድገት ይልቅ በዝቅጠት ውስጥ ሲኖር በምክንያታዊነት ውስጥ የሚኖር ትውልድ በብልጽግናና በከፍታ ውስጥ ይኖራል፡፡ ኢ-ምክንያታነትና ስሜታዊነት የሠለጠኑበት ማሕበረሰብ የአስመሳዮች፣ የባሪያዎች፣ የሃሰተኞች፣ የአሽከሮችና የገረዶች መጫወቻ ሲኾን ምክንያታዊነት የሠለጠነበት ማሕበረሰብ በአንጻሩ ግልጽነት፣ ሃቅ፣ ፍትሃዊነትና ነጻነት መለያዎቹ ይኾናሉ፡፡
“ምክንያታዊ ትውልድ እንኳንስ የራሱ ያለፈ ትውልድም ኾነ የሚመጣ ትውልድ አለኝታ ነው! ምክንያታዊ ትውልድ እያንዳንዱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በምክንያት በመምራት ያለፈ ትውልድ በጎ ዕሴት ጠባቂና አስጠባቂ፤ የራሱን ትውልዳዊ ኃላፊነት በመወጣት የሚቀጥለውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚመጣው ትውልድ መኩሪያና አለኝታ ይኾናል፡፡”
ሀገር እንደሀገር በሥልጣኔ ጎዳና ላይ ትራመድ ዘንድና ሕዝብ እንደሕዝብ ኹለንተናዊ ሰላምና ብልጽግና ይኖረው ዘንድ ምክንያታዊና ምክንያታዊ የአኗኗር ዘይቤን ባለቤት መኾን ያስፈልገዋል፡፡ ያለምክንያታዊነት ባሕልና እንቅስቃሴ ሥልጣኔና ዘመናዊነት ሕልም ብቻ ሳይኾን ቅዠትም ጭምር ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሕልምና ቅዠት ወጥተናልን? የችግሮቻችን አስኳል ኢ-ምክንያታዊነት ባሕል መኾን ነውና – በምክንያታዊነት ባሕል ካልተካነው በቀር ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ የማምጣት ጉዳይ ባዶ ትርጉም አልባ የቃላት ጋጋታ ብቻ ኾኖ የሚቀር ይኾናል፡፡ “ምክንያታዊ ትውልድ – አለኝታ ለትውልድ!
(Rationality Campaign)” ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!
ቸር እንሰንብት!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.