የኢሳት  ህልውና፤ በተጠቃሚዎች ድጋፍ  ይፅና – በትሩ ገብረ እግዚህአብሄር

Betru Gebregziabher

ኢሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶትና ሰቆቃ እንዲያበቃ ለአገር ፍቅርና ለዜጎች ክብር መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ ታጋዮች  በግለሰብም በቡድንም በድርጅትም ተደጋግፈው ያቋቋሙትና ግምባር ቀደም ታጋይና አታጋይ ለመሆን ያበቁት አገልግሎቱ የሠመረ ወጤታመነቱም የተመሠከረ መሥራቹም አገልጋዩም የኛ የሚሉት በሂደቱና በአድራጎቱ ሁሉ ሕዝባዊነት የተላበሰ ልዩ ተቋም ነው።

ይህ በአይነቱ ብቸኛ የሆነና በእልህ አስጨራሹ ሕዝባዊ ትግል ግምባር ቀደም ታጋይና አታጋይ ሆኖ የአምባገነኖቹን ግብግብና ውጣ ውረድ ተቋቁሞ ዛሬ ለደረስንበት የትግል ምዕራፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ተቋም እንዲኖር ኃሳቡን አመንጨተው ጊዜው በሚጠይቀው ስልትና ጥበብ አደራጅተው የሕዝቡን ድጋፍ አሰባስበው ለውጤት ያበቁት ግለሰቦች፤ ድርጅቶች፤ባለሙያዎች ክብርና ምስጋና ሹመትና ሽልማት ሊጎናጸፉ በሚገባቸው ወቅት የተቋሙን ህልውና የሚፈታተን ሁኔታ ውስጥ መዘፈቁ ያሳዝናል።

 

ባለድርሻዎችም በግንባታውና በትግሉ ወቅት ያዳበሩትን ትብብርና የዓላማ አንድነት ወደሚሸረሽር ጣት መጠቋቆምና ውዝግብ ማምራታቸው ተገቢም ጠቃሚም ስላልሆነ የሚመለታቸው ሁሉ የጀመሩትን ጉንጭ አልባፋ ክርክር አቁመው በወደፊቱ ራዕይና አላማ ላይ ያተኮረ አስተዋጾአቸውን እንዲቀጥሉ እስካሁን ድምፁ ጎልቶ ባልተሰማው የኢሳት አገልግሎት ተጠቃሚ ሕዝብ ስም፤ በአክብሮት ልንማጸናቸው ይገባል።

 

ኢሳት በማንና እንዴት ተቋቋመ የሚለውን ውዝግብ በግንባታው ውስጥ እጃቸው ያለበት ሁሉ የሕዝብና  የአገር ባለውለታ መሆናቸውን ሳንዘነጋ፤ ለጊዜው ለታሪክ ተመራማሪዎች እናቆየው።

 

በፈታኝ አገራዊ የሕዝብ ማዕበል ውስጥ የተፈጠረ አቻ የማይገኝለት ልዩ ተቋም እንደማንኛውም ድርጅት በተለመደ አሠራርና የአመራር ሥልት ለማካሄድ ለማሸጋገርም መሞከር ስለማያዋጣ ልዩ የሚያደርጉትን ባህርያት ለይቶ ተመጣጣኝ የሆነ ልዩ መፍትሄ መሻቱ ይሻላል።

 

የኢሳት መስራች ግለሰቦች ድርጅትና አመራሮች ለልዩ ጥቅምና ለዝና ብለው አላቋቋሙትም፤ የኢሳት ጋዜጠኞችም ለደሞዝና ለሹመት ብለው አልተቀላቀሉም፤ የኢሳት ደጋፊዎችም ትርፍ ያስገኝልናል ብለው አልተረባረቡም፤ ሁሉም በአገር ወዳድነት፤ በቆራጥነት ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ከፍለው ይህንን አይነተኛ የትግል መሳሪያ ተጠቅመው ታሪክ የማይረሳው ሕዝባዊ አገልግሎት የሠጡ ጀግኖቻችን ናቸው። የወደፊቱም ሂደት በዚህ አኩሪ ታሪክ ላአይ ካልተገነባ የእንቧይ ካብ ይሆንብናል።

 

በመሆኑም የኢሳት ጋዜጠኞች፤የቦርድና የድጋፍ አካላት አመራሮች ከጀርባው የነበረው ድርጅትም ለሚጋሩት የትግል ዓላማ በቅንነት በቆራጥነትና በሙሉ ስሜት ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ የሕዝብ አለኝታና ባለውለታ ያደረጉትን ተቋም በአሠሪና ሠራተኛ በአስተዳደር መርህና በተለመደ ሕጋዊ አካሄድ መልክ ለማስያዝ መሞከር ለተወሳሰበው ችግር የሚመጥን ዘላቂ መፍትሄ አያስገኝም።

ኢሳት ልዩ ነው። የተመሠረተውም የጎለበተውም ለዚህ የበቃውም ጊዜው የጠየቀውን ዘዴና ጥበብ እየተጠቀመ በጥንቃቄና በልዩ ስልት በመጓዙ ነው። ለዚህ ደግሞ መስራቾቹም አመራሮቹም ጋዜጠኞችም ደጋፊዎችም የየበኩላቸው ምትክ የለሽ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።  ለዚህም ሕዝባዊ ክብርና ሞገስ ምስጋናና ምርቃት ይገባቸዋል።

ለወደፊትም ይህንን በብዙዎች ርብርብ የተገነባና ውጤታማ የሆነ ልዩ ተቋም በዘላቂነት ለማስቀጠል  መሠረቱን ማስፋትና ማጠናከር አይነተኛ መፍትሄ ስለሚሆን ትኩረታችን በሽግግሩ ሒደት ላይ ቢያነጣጥር ይሻላል።

እስቲ በአገር ደረጃ ስንመኝ የነበረውን የሽግግር ሂደት ይህንን እንደ አይናችን ብሌን የምንሳሳለትን ተቋም የበለጠ ሕዝባዊ ወደሚያደርገው ሥርአት በማሸጋገር እንሞክረው።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ፤

1ኛ/ እስካሁን በኢሳት ምስረታ፤ አመራር፤ አገልጋይነት፤ ደጋፊነትና ተጠቃሚነት ከሚታወቁ አካላት የተውጣጣ “ምክር ቤት” ይቋቋም።

2ኛ/ ለጊዜው የበጀት የሠራተኛ የፕሮግራም የአደረጃጀት፤ለውጥ የማድረጉ ሂደት ይገታ።

3ኛ/ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ሕዝባዊ እርዳታና ብድር አፈላልጎ ቢያንስ ኢሳትን ለሦስት ወራት ማካሄድ የሚያስችል ገንዘብ ማስገኘቱን ተቀዳሚ ተግባር ይደረግ።

4ኛ/ ምክር ቤቱ አስፈላጊ ግብረኃይላት አቋቁሞ ኢሳት ሕዝባዊነቱ ተረጋግጦ በጠንካራና አስተማማኝ መሠረት ላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ያሉትን አማራጮች ገምግሞ የአጭር፤ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ለሕዝበ ውሳኔ እንዲቀርብ ይደረግ።

 

በዚህ ሂደት ኢሳት ሕዝባዊነቱ ተጠናክሮ በሙያተኞች ዳብሮ አገልግሎቱ ሰምሮ እንዲቀጥል ልዩ ለሆነው ብርቅዬ ተቋማችን የኛ የሆነ ልዩ መፍትሄ እንፈልግለት። ለቀሪው ወሳኝ አገራዊ ትግል የተለመደ ታግሎ የማታገል አገልግሎቱን ማበርከት እንዲችል በገንዘብም፤ በክህሎትም በአመራርም የተጠናከረ ቁመና እናስታጥቀው። እዚህ እንዲደርስ ታሪካዊ አስተዋጽኦ  ያደረጉ ሁሉ የመንፈስ እርካታ የሕዝብ አዎንታ፤የትውልድ ባለውለታ፤ መሆናቸውን አውቀው ዳግመኛ አሻራቸውን እንዲያኖሩ የበለጠ እድል እንፍጠርላቸው።

ኢሳት የአገር አድን ትግሉ ግምባር ቀደም ሚናውን አጠናክሮ መቀጠል እንዲችል የሁሉም አገር ወዳድ ድጋፍና ዕርዳታ ያስፈልገዋልና የኢሳት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሁሉ እንረባረብ፤ ያለፈውን ውለታ ሳንረሳ የወደፊቱን ራዕይ ለማሳካት በዓላማ አንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘነ እንነሳ።

ኢሳት የሕዝብ አለኝታነቱ በተግባር እንዳስመሰከረ ሁሉ ሕዝቡም የኢሳት አለኝታ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ጊዜ ዛሬ ነው።

 

የሕዝባዊ ትግሉ ፍሬ ይጎመራል!

ኢሳትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይን፤ ጀሮና ልሳንነቱን  አጠናክሮ ይቀጥላል!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.