የጌታቸው አሰፋ መኖሪያ አድራሻ ስለማይታወቅ መጥሪያውን ማድረስ አልተቻለም – የፌዴራል ፖሊስ

የፌዴራል ፖሊስ ትግራይ ክልል ለሚገኘው ቅርንጫፉ የፍርድ ቤት ትእዛዙን በፋክስ ቢልክም በመጥሪያው ላይ የተከሳሾቹ የመኖሪያ አድራሻ ባለመጠቀሱ ለማድረስ አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት 1ኛ የወንጀል ችሎት ግንቦት 16/2011ዓ.ም በነጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ላይ ሰጥቶ የነበረውን ትዕእዛዝ ውጤት ለመከታተል ነበር ለዛሬ ቀጠሮ የያዘው፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ትክክለኛ አድራሻ የያዘ መጥሪያ በድጋሚ ተዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱም የትግራይ ክልል ፖሊስ እንዲተባበር የሚያስችል ትእዛዝ እንዲፃፍ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በፃፈው ማመልከቻ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም አቃቤ ህግን የተከሳሾቹ አድራሻ ለምን በክስ ማመልከቻው ላይ አልተጠቀሰም በማለት ጠይቋል፡፡

ፌዴራል አቃቤ ህግም ትግራይ ክልል ከማለት ውጪ የተከሳሾችን ትክክለኛ አድራሻ እንደማያውቅ ገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎ አቃቤ ህግ ለተከሳሾቹ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ክሳቸው በሌሉበት እንዲታይ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በድጋሚ በትክክለኛ አድራሻ መጥሪያ ይላክልቸው ወይንስ በጋዜጣ ይጠሩ የሚለው ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 12/2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡

በተጨማሪም ችሎቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለፅ ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይደረግልኝ በማለት ባቀረበው አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 12/2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡

FBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.