ኢሳትን እያዳፈኑት ነው ወይንስ እያጠፉት ? (ድሉ)

ከሆነስ ማን ?

የዘጥኝ ዓመቱ ኢሳት አንድ ህጻን በዚህ እድሜው ሊከውን ይችላል ተብሎ ከሚታመነው በላይ ያደረገ ሚዲያ ነው ። በአገራችን ለሃያ ሰባት ዓመታት ስልጣንን ተቆናጦ ያለ የሌለ ኃይሉን አሰማርቶ በሕዝብ ኃብትና ንብረት ባቋቋማቸው የፕሮፓጋንዳ አውታሮች እርዛትን ብልጽግና ፣ ኋላ ቀርነትን እድገት፣ አፈናን ዲሞክራሲ ፣ መከፋፈልና ልዩነትን አንድነት እያለ አደንቁሮና አማራጭ አሳጥቶ ይገዛ የነበረውና ተራራውን አንቀጠቀጥኩ ባዩን የህወሀት መራሹን መንግሥት ውሸት እንደ ስጥ እያሳጣ ለሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ፈር ቀዳጅ በመሆን እንኳን ተራራ ኩይሳ ሳይርድ ወደ ጎሮኖው እንዲገባ ያደረገ የሕዝብ ባለውለታ ነው ።

ይንን አስተያዬት ለመስጠት ያነሳሳኝ ሰሞኑን በኢሳት ዙሪያ የተነሳውን እሰጣ ገባ አይቼ በጣም ስላዘንኩ ነው ። ሌላው ቀርቶ ሀሳቤን አንድ ላይ አመጥቼ ለመጻፍ የተቸገርኩበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ኢሳትን ለማጥፋት ህወሀት ብዙ ጥሮ ያልተሳካለትን ከሰባተኛው ሰማይ በወላጅ ነኝ ባዩ ግንቦት ሰባትም ሆነ በአዋላጆቹ ጋዜጠኞች ተወርውሮ ይፈጠፈጣል የሚል እምነትም ጥርጣሬም ስላልነበረኝ ነው ።

እያዬሁና እዬሳማሁ ያለው አስተያዬትም ሆነ የሚሰጡ መግለጫዎች የሚጋራቸውና የሚያሳምኑኝ ሆኖ አላገኘኋቸውም ። ማናቸውም ቢሆኑ ራሳቸውን ለመከላከል ካልሆነ በቀር በአገራችን ያለውን ግራ አጋቢ ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ፣ ለሀገርና ለወገን ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ መፍታት የሚቻልን ነገር አደባባይ አውጥቶ መነታረክና ጠላትን ጮቤ ማስረገጥ የሚሉትን ሆኖ አለ መገኘት ነው የሚሆነው።

ኢሳት አንድ ሚዲያ ሊከተለው የሚገባቸውን አምስት የጋዜጠኝነት መርሆዎችን ተከትሎ የሰራና አሁንም የሚሰራ የመገናኛ አውታር ነው ብዬ መናገር አልችልም ። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች አሉኝ አንደኛው ኢሳት ከህጋዊ ባለቤቱና ከዬትም የምጣ ኬት የፋይናንስ ፈሰስ ከሚያደርግለት አካል ነጻ ሆኖ መርሆችን የመተግበር አቅም ሊኖረው ስለማይችል ነው ። ሁለተኛው በአገራችን ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የመንግሥትን በሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ ማጋለጥና ሕዝብን ማነሳሳት ተቀዳሚ ተግባሩ በመሆኑ የሙያ ጊዴታው የሆኑ መርሆዎችን ከመከተል ይልቅ በካውንተር ፕሮፓጋንዳና በፕሮፓጋንዳ ላይ በማተኮር ህወሓትን በማስወገድ ላይ ያተኮሬ በመሆኑ ነው ።

አምስቱ መርሆዎች ፦

  1. እውነተኝነት እና ትክክለኝነት፣
  2. ገለልተኝነት
  3. ፍትሐዊነት እና ሚዛናዊነት፣
  4. ሰብአዊነት፣
  5. ለሚሰራዉ ሥራ ተጠያቂነት

አንድ ሚዲያ እነዚህን መርሆዎች ተከትሎ ለመስራት እንዲችል ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ዋናውና ወሳኙ የፋይናንስ ምንጩ ወይንም ባለቤትነት ሲሆን ሁለተኛው የጋዜጠኞች የሙያ ብቃት ነው ። በመንግሥት ወይንም በፖለቲካ ድርጅቶች የሚያዙ ሚዲያዎች ከላይ የተጠቀሱትን ሙያው ስነመግባሮችን ሊተገብሩ ይቅርና ሊያስቡም አይችሉም ። ምክንያቱም የሚጽፏቸው ወይንም የሚዘግቡት ዜና በድርጅቶቹ ካድሬዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ አሊያም ሳንሱር ተደርገው የሚቀርቡ በመሆኑ ነው ።

ወደ ኢሳት ስንመጣ ግን የግንቦት 7 አመራር የነበሩት አቶ አበበ ቦጋለ እንደሚሉት ሳይሆን መሬት ላይ ያለው ሀቅና እኔን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍ ስናደርግ የነበርነው የግንቦት 7 አባል ወይንም ደጋፊ በመሆናችን አልነበረም ። በዚህ አጋጣሚ አቶ ነአምን ዘለቀ ሀቁን በመናገሩ ሳላመሰግን አላልፍም ። የፋይናንስ ምንጭነትና ባለቤትነት ተያያዥ ቢሆኑም ኢሳትን በተመለከተ ግን የወቅቱ ህጋዊ የባለቤትነት መብት ያለው አካል ማን መሆኑን በይፋ የምናውቀው ነገር ባይኖርም ግንቦት 7 ግን ብቸኛው የፋይናንስ ምንጭ አይደለም ። ያ ማለት ግን ግንቦት 7 በኢሳት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ አልነበረም ማለት አይደለም። የኢሳት የቦርድ አባላትና ስመ ጥር ጋዜጠኞች የድርጅቱ ካድሬዎች ናቸውና ። ይሁን እንጂ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ተጽእኖ ሊፈጥር አይችልም ።

 

የማይችለውም ፦

  1. የኢሳት ጋዜጠኞች የሚዲያ እመቃ ሰለባዎች በመሆናቸው ተጽእኖውን ሙሉ በሙሉ አሜን ብለው የሚቀበሉ ባለመሆናቸው ፤
  2. ምንም እንኳን ግንቦት 7 በለቤት እኔ ነኝ የፋይናስ ምንጭ አባሎቼና ደጋፊዎቼ ናቸው ቢልም ሀቁ ሁላችንም የድርጅቱ አባል ያልሆን የምናውቀው በመሆኑ ምናልባት እኔን ጨምሮ የምናዋጣው ገንዘብ ወደ አንድ ቋት ፈሶ በግንቦት 7 እጅ ገብቶ ከአንድ ማእከል ወጪ ካልሆነ በቀር የፋይናስ ምንጩ ብቻውን ስላልነበር የመቶ ፕርሰንት እመቃ ለማድረግ አቅም አይኖረውም ።

ጋዜጠኞቹ መርሁን ተከትሎ ለመስራት የሙያ ብቃት ያንሳቸዋል የሚል እምነት የለኝም ነገር ግን ከግንቦት 7 በተጓዳኝ የህወሓትን ፕሮፓጋንዳ ለመምታትና ለማጋለጥ ሲባል ካውንተር ፕሮፓጋንዳ የግድ አስፈላጊ ስለነበር መርሆዎችን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም አዳጋች እንደነበር ግልጽ ነው።

ኢሳት ወላጅ አባቱ ማነው ለሚለው ንትርክ መፍትሄ ለመሻት የድኤንኤ ምርመራ የሚያስፈልገው አይመስለኝም ። ሀሳብ በማፍለቅና በማቋቋም የግንቦት 7 ድርሻ የላቀ መሆኑን ከጅምሩ የተገነዘብኩት ነበር ። በመሆኑም እንደ አንድ የሚዲያን ጉልበትና ኃይል እንደምገነዘብ ግለሰብ ኢሳት ለትግሉ ሊያበረክት የሚችለውን የላቀ ድርሻ ከግምት በማስገባት ለግንቦት 7 የነበረኝ ከበሬታ ትልቅ ነበር ። በጣም የገርመኝ ግን አንድ ህይወቱን ለመሰዋት ቆሜያለሁ ያንንም የማደርገው ለሥልጣን ሳይሆን ለሀገርና ለሕዝብ ነው ሲል የነበረ ድርጅት ሲከስም ደብቆ የነበረውን የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳቱ ክሬዲት ሀዎሩ አንሶት ለመጨመር ነው ወይንስ ኢሳትን ለማጥፋት ?

ማንኛችንም የግንቦት 7 ድርጅት አባል ያልነበርን ግለሰቦች በየወሩ ስንከፍል የነበረው ኢሳትን ማን ቢዎልድ ማን ብለን የዘር ሀረግ መዘን ሳይሆን ኢሳት ምን እያረገ ነው ብለን ተግባሩን አይተን ነው ። ግንቦቶች ግን ሙሉ ወጪውን በአባሎቻቸውና በደጋፊዎቻቸው

ቢቻ የሚሸፍኑት ከሆነ ካሁን በፊት ኢሳት የኛ ነው ያላሉት ለምድን ነው ? አሁን ደግሞ ለሕዝብ አሳልፈን እንሰጣለን ያሉት ለአባሎቻቸው ውይንስ ለየትኛው ሕዝብ ነው? ሕዝብ ያሉት አባሎቻቸውን ከሆነ በውስጥ መጨረስ ነበረባቸው እንጂ ማወጁ አስፈላጊ አልነበረም ። ይህ በጅምላ ሕዝብ ያሉት የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ ሊያጠቃልል አይችልም ምክንያቱም ኢሳት የሁሉም ሀብትና ንብረት ሊሆን ቀርቶ የሁሉም ወዳጅ አልነበረምና ነው ። አባላቸው ያልሆነውን ነገር ግን በየወሩ ስናዋጣ የነበርነውን እኔንም ጨምሮ ሳናስብ በድንገት ባለቤት አድርገውናል እንዳንል ለመርዳታችን እንኳን እውቅና ከመንሳታቸው በተጨማሪ የኢሳትን የወደፊት እጣ ፋንታ እንዲወስኑ የሾሙት ሶስት ተጽዕኖ ፈጣሪ የግንቦት 7 ካድሬዎችን ነው ።

ግንቦት 7 ሲከስም የኢሳትን እጣ ፈንታ ያወሳሰበው ለምንድን ነው ? የቦርድ አባል ሆኖ ለኢሳት ጥንካሬም ሆነ ድክመት ኃላፊነት የነበረው(ኤፍሬም ማዴቦ ) በሌላ ሚዲያ ቀርቦ ማበሻቀጡ ኢሳትን የማጥፋት ዘመቻ አካል ይመስለኛል ።

አበው ሲተርቱ አኗኗሬ ባይሰምር አሟሟቴን አሳምርልኝ ይሉ ነበር G7 ግን ለአሟሟቱም የተጨነ አይመስልም ።

 

ኢሳትን እያዳፈኑት ነው ወይንስ እያጠፉት ? እነ ማን ?

አንድ ባልና ሚስት በፍቅር ተጋብተው ወልደውና ከብደው እየኖሩ እንኳን እህል ውኃቸው ሲያከትም ይለያያሉ ። ሲለያዩም የሀብትና የንብረት ክፍፍል ይደረጋል ፤ የልጆቻቸውን እጣ ፋንታ ላይ ተወያይተው መፍትሄ ያበጁለታል ፤ ክዚያም የየራሳቸውን ህይወት በፈለጉት መንገድ ይመራሉ እንጂ ሀብት ንብረታቸውን አውድመውና ልጆቻቸውን በትነው በዘፈቀድ አይለያዩም።

ኢሳትን ስንወስድ አንድ ትልቅ በስሩ የሚያስተዳድራቸው ብዙ ምሁራንን ያቀፈ ተቋም ነው ። ይህንን ድርጅት ሀሳብ አፍልቀውና አውጣተው እንዲቋቋም ያደረጉ ግለሰቦችና ድርጅት አለ ። ሚዲያው የተቋቋመው ከአገራችን ውጭ የተመሰረተበት ሀገር ህግ በሚፍቅደው መሰርት ባለቤት ኖሮት ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ነው ። ስለሆነም ህጋዊ እውቅና የተሰጠው ባለቤት ሊሆን የሚችለው አንድ ግለሰብ ወይንም ከአንድ በላይ የሆኑ ግለሰቦች አክሲኦን ነው ። ግንቦት 7 በካድሬዎቹ አማካኝነት ከኋላ ሆኖ ከመሾፈር በዘለለ በድርጅቱ ስም አስመዝግቦ የመያዝ ህጋዊ መሰረት የለውም ። ከሆነ ሊሆን የሚችለው በካድሬዎቹ ስም አስመዝግቧል ማለት ነው ። ያም ቢሆን ምንም ክፋት አልነበረውም ።

ወደ ቁምነገሩ ስገባ በእኔ እምነት እሳት የተቋቋመው ወያኔ መራሹን ጸረ ሕዝብ መንግሥት ገርስሶ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማስፈን ሕዝብን ማንቃትና ማነሳሳት ብሎም ለውጡ እውን እንዲሆን ማገዝ ነው። አላማው ሕዝባዊ በመሆኑ ጸረ ወያኔ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ያማከለ ነበር በመሆኑም እኔን ጨምሮ የማነው ሳንል ተግባሩን በማዬት ደግፈናል ። ለመጨረሻው ውጤት ሳያበቃን ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ካለንም ይሄንን ማን አዬ እናመሰግናለን ብለን ከመተው ሌላ አማራጭ የለንም ።

ኢሳትን እያዳፈኑት ነው ውይንስ እያጠፉ እነማን ወዳልኩት ስመለስ እንደኔ እምነት ግንቦት 7 ሀብትሽ በሀብቴ ብሎ ኢዜማ የምትባል ሚስት ከማግባቱ በፊት ከፊሉን ንብረት ለክፉ ቀን ለማሸሽ የፈለገ የመስለኛል ያ ባይሆን ኖሮ ሶስት ጠንካራ ካድሬዎችን መድቦ እሳት እንደ ወትሮው እንዳይነድ አዳፍኑት ብሎ አይከስምም ነበር። ሌላው

ቦርዱንና ጋዜጠኞችን በተመለከት ሁሉም ባይሆኑ አብዛኞቹ የግንቦት 7 አባላት(ካድሬዎች) በመሆናቸው እርስ በርሳቸውም ሆነ ከራስ ጋር ከፍተኛ የሆነ ትግል ውስጥ የገቡ ይመስለኛል ምክንያቱም በአንድ በኩል በአባልነታቸው የንቅናቄው ድሲፕሊን ቀፍድዶ ይይዛቸዋል በሌላ በኩል የሙያውን መርሆ መጣሱ የህልና እረፍት ይነሳቸዋል። ይህ ደግሞ ሳይወዱ በግድ አንዱን እንዲመርጡ ያደርጋል። እየሆነ ያለውም ይህ ነው። በእኔ እይታ ኢሳትን ይዘው የሚገኙ ጋዜጠኞችም ሆኑ ጥለው የወጡት እሳትን ቀድሞ ማን ያጥፋው የሚል ፉክክር ካልሆነ በቀር ልዩነት አላይባቸውም ። በማጠቃለያ አንድ ማለት የምፈልገው አበው ሲተርቱ የባሌጌ ባለሟል ቂጥ ገልቦ ያያል ይላሉና እባካችሁ ከሁለቱም ወገን ያላችሁ ማንነታችሁን ለእኛ ተውልን እናውቃችኋለን ። ሙያ በልብ ነውና ጥንክራችሁ በመስራት ያጎደፋችሁትን ስማችሁን ለማደስ በየፊናችሁ ጣሩ።

 

አምላክ ፍቅር ያላብሳችሁ

ድሉ ነኝ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.