ታሪካዊውን ቡፌ ደ ላጋር ማፍረስ ተጀመረ

በለገሃር መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ሳይት ላይ የሚገኘው ታሪካዊውና ዕድሜ ጠገቡ ቡፌ ደ ላጋር እንዳይፈርስ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም፣ የሚታደገው ሳያገኝ ዓርብ ሰኔ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ መፍረስ ጀምሯል፡፡

ተገንብቶ ሥራ ከጀመረ 95 ዓመታትን ያስቆጠረው ቡፌ ደ ላጋር ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ታሪካዊ ሁነቶችን አስተናግዷል፡፡

ነገር ግን የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ድርጅት ቡፌ ደ ላጋርን ተከራይቶ እየሠራበት ለሚገኘው ቡፌ ደ ላጋር ትሬዲንግ ኩባንያ ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ከግንቦት 19 ቀን ጀምሮ ማፍረስ ስለሚጀመር ኩባንያው ያለውን ንብረት በማውጣት ቤቱን ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት እንዲያስረክብ አዟል፡፡

ይህ መረጃ ከወጣ በኋላ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ነብዩ ባዬ (ረዳት ፕሮፌሰር) ለኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ የቤቱን አጠቃላይ ታሪካዊ፣ ቅርሳዊና ጥበባዊ ፋይዳ በመመዘን የከተማ ልማት ፕሮጀክቱ ታሪካዊውን ቤት በማይነካ መንገድ እንዲከናወን አሳስበዋል፡፡

‹‹በዚህ ደብዳቤ ላይ ያቀረብነው ሐሳብ በድርጅቱና የኮንስትራክሽን ሥራውን በሚመራው ተቋም በሚገባ ታይቶ፣ ተጨማሪ ምክክር የሚደረግበት ጉዳይ ካለም ተወያይተንበት እስኪወስን ድረስ በታሪካዊው የጥበብ ቤት ላይ ምንም ዓይነት የማፍረስ ዕርምጃ እንዳይወሰድ፤›› በማለት ረዳት ፕሮፌሰሩ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡

ነገር ግን የረዳት ፕሮፌሰሩም ሆነ የተለያዩ የቅርስ ተሟጋቾች ውትወታ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

በአራት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይህ ታሪካዊ ቤት መኝታ ቤቶች፣ ሬስቶራንት፣ ባርና የተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎችን ያካተተ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለገሃር አካባቢ ስለሚካሄደው ልማት ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ ‹‹ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን  ግምት ውስጥ ባካተተ ዲዛይን መሠረት ይካሄዳል፤›› ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሳይሆን ቀርቶ ታሪካዊው ቡፌ ደ ላጋር ለመፍረስ ተዳርጓል፡፡ በእርግጥ ቡፌ ደ ላጋርን ለማፍረስ የታሰበው በዚህ ፕሮጀክት ብቻ አልነበረም፡፡

ከቄራ ተነስቶ በቂርቆስ በኩል ለገሃር ባቡር ጣቢያውን አቋርጦ፣ ከቸርቸል ጎዳና ዋና መንገድ ጋር ለማገናኘት ተጀመረው የመንገድ ፕሮጀክት ቡፌ ደ ላጋርን ይነካው ነበር፡፡

ነገር ግን በብዙ ውትወታ የመንገድ ሥራው ተቋርጦ ቡፌ ደ ላጋር ተርፎ ነበር፡፡ 36 ሔክታር ላይ በሚያርፈው የለገሃር ፕሮጀክት ምክንያት በርካታ ቤቶችና ሕንፃዎች እየፈረሱ ነው፡፡

1 COMMENT

  1. ቡፌ ደላጋር በለገሃር የሚገኝ ጥንታዊ ሆቴል ቤትና በደርግና ወያኔ ዝመን ደግሞ የዳንኪራ ቤት በተለይ የሳልሳና የሮማንቲንክ የፍቅር መተቃቀፍ ዳንስ ማሳያ ሆኖ ነበር:: የባለቤቱ ልጅም በወያኔ ዘመን በመመርዝ ጠንቅ ማረፉ ይታወቃል:: በለገሃር ዙርያ ለሚገነቡት ብዙ ቤቶች ግንባታ ያ ቤት መፍረሱ ቢያሳዝንም ከግባታውና የከመማዋ መስፋፋት የዜጎች ከፈተና የመኖሪያ ቤት ችግር መቀረፍ አንጻር ብዙ የሚያስውግዝ አይደለም:: ይልቁንስ የመጀምሪያው የከተማዋ ሆቴል የጣይቱ ሆቴል ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል:: ከተማዋ በፕላን የተመሰረተች ባለመሆኗ ከድሮው መሃንዲስ ሙሴ ሚናስ ጀምሮ የቤቶች መፍረስ ውዝግብ ያለባት ከተማ መሰረተልማቷን በሚያፍጥኑ ግንባትዎች መስፋፋት ያላስፈላጊ ትችት ለሃገር ስለማይጠቅም ይህን መሰሉን ውግዘት ማቆም ይበጀናል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.