በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ (ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ)

ሰኔ      2011 ዓ/ ም
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@gmail.com

ቀሲስ-አስተርአየ-ጽጌ
ቀሲስ-አስተርአየ-ጽጌ

የቀደሙ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አባቶች የመደመርን ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ይመለከቱት ነበር? ተብሎ በድያስፖራው ለተነሳው ጥያቄ ከሞላ ጎደል ለመመለስ መጀመሪያ ጳጉሜ 2ሽ 10 ዓ/ም በኢትዮጵያ ኢማባሲ ዋሽንግተን ዲሲ አዳራሽ ይህች ጦማር ቀረበች ። እንደገና ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ/ ም አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ስብሰባ ቀረበች። ለቤተ ክርስቲያናችንም ሊቃውንት ጉባዔና ለሚመለከታቸው ተቋማትም ቀርባለች።

“የመደመር ጽንሰ ሀሳብ ባባቶቻችን ግንዛቤ ምን እንደነበረ ወጣቶች ሰምተውት ስለማያውቁ፤ የዘመናችን ልሂቃንም በማወቅም ባለማወቅም እየናቁና እያጣጣሉ ከውጭ በወረሱት አፍራሽ ሀሳብ ህብረተ ሰቡን ግራ እያጋቡት ነው። ኢትዮጵያውያን እንዲነጋገሩባት፤ በያቅራቢያቸውም ላለው ወጣት እንዲያሿግሯት እንደገና ትቅረብ” ብለው የዲያስፖራው ጉባዔ በባህር ዳር ከተማ በሰኔ ወር መደረጉን የሰሙ ወገኖች ደጋግመው ጠየቁኝ።

ስለዚህ እንደገና እንድትቀርብ የተገፋፋሁበትን ምክንያት የምገልጽበትን እንደ መቅድም በመጠቀም፤ ይዘቷንና ቅርጿን ለመግለጽ መግቢያም አዘጋጂቸላት፤ ከዚህ ቀደም ካቀረብኩባት መንገድ ለየት በማድረግ በትንሽ መጽሐፍ መልክ አቅርቢያታለሁ። በመቅድሟ ልጀምር።

መቅድም

ከኛ በፊት የነበሩት ሊቃውንት ኢትዮጵያን የጠበቁባቸውን መስተጻምራት በቃልም በተግባርም ባለማሳየታችን፤ ይልቁንም የግል ክብርና ድሎት አሳዳጆች ሆነን በመታየታችን፤ በኛ በዘመኑ ቄሶች ድካም፤ የቀደሙ ሊቃውንት ቀሳውስት አባቶቻችንና ቤተ ክርስቲያናችን ባዲሱ ትውልድ ሲነቀፉና ሲተቹ ስሰማ ይሰቀጥጠኛል።

በዚህ ዘመን ያሉ ልሂቃንም በቀደሙ አርበኞች አባቶቻችን ዘመን ነበረ የሚሉትን እንከን እያረሙ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት የተጠቀሙባቸውን ሁለገብ መስተጻምራት የበለጠ እያዳበሩ፤ ቢችሉ ኢትዮጵያን ከነበረችበት ታሪካዊ ልዕልና ከፍ እያደረጉ፤ ባይችሉ ከበረችበት ዝቅ እንዳትል፤ ዜጎቿም የተጣመሩባቸውን ሁለገብ መስተጻምራት የበለጠ እያራቀቁና የዜጎችንም ኅብረተ ሰባዊ ሁለንተና እጅግ ከፍ ባለ ስነ ህሊና እንዲጣመር ከማስተማር ይልቅ፤ ብሔር ብሔር ሰቦች በሚል ህሊና መራዥ ቃላት በሥጋ በደምና ባጥንት የተጣመረውን ኅብረተሰብ በግድ እየፈለቀቁ ሲለያዩት፤ ኢትዮጵያንም ከወጣቱ ስነ ህሊና ለማጥፋት የሚያደርጉትን ሸፍጥና ደባ ሳይና ስሰማ ይዘገንነኛል።

ከኛ በፊት የነበሩት አባቶቻችን ካህናትና አርበኞች የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ እንደ ሙጫ ያያዙባቸውን መስተጻምራት ማሳየት ባለመቻለችን ወጣቱ ትውልድ ከመተቸት አልፎ በዱላ እየደበደበ ቢያባርረን የሚበዛብን አይደለም። ወጣቱ ትውልድ በቀደሙ አባቶቻችን እና በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሰነዝረውን ነቀፋና ትችት አንስቶ በማበላሸት ላይ ባለን በኛ በዘመኑ ካህናት ላይ ሊያደርገው ይገባል እንጅ፤ የቀደሙ አባቶቻችንና ቤተ ክርስቲያናቸውን መንቀፍ ፈጽሞ አይገባም። ምክንያቱም የቀደሙ አባቶች ኢትዮጵያን የጠበቁባቸው ሁለገብ መስተጻምራት ከዘመኑ ፖለቲካ ትምህርት እጅግ በጣም የበለጡና እንከን የሌለባቸው ፍጹማን ነበሩ ባይባልም፤ ቢያንስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጠብቀዋታል። ኢትዮጵያ እስከምትገነጣል የሚያደርስ መፈክር በትውልዱ ጭንቅላት በመክተት በጠላትነት እያነሳሱ ዜጎች ልጆቻቸውን እርስ በርሱ አላጋደሉም።

 

“ብሔር ብሔር ሰቦች” የሚለውን በቅኝ አገዛዝ ሥር በወደቁባቸው በሌሎች አገሮች ህብረተ ሰብ መካከል የነበሩ መደነቅ የሚገባቸው ልሂቃን፤ ወገኖቻቸውን ነጻ ለማውጣት ባንድ ወቅት እንደተጠቀሙበት የማይሰወራቸው፤ ሰባዊ ፍቅር የጎደላቸው የዘመናችን ልሂቃን፤ በቅኝ ግዛት ስር ወድቃ በማታውቀው ኢትዮጵያ፤ ዜጎቿም ከጢሰኝነት በተላቀቁበት ዘመን፤ ከጎረቤት አገሮች ኮርጀው ኢትዮጵያዊ ዜጋ የተጣመረበትን ትስስር በማላቀቃቸው፤ የኢትዮጵያንም ሉዓላዊነት በማክሰማቸው ወጣቱ ትውልድ ይገሰጻቸው፤ ያዋርዳቸውና ከመካከሉም እየመነጠረ ያባርራቸው ዘንድ መንቃት አለበት።

 

ከየጎጡ የተፈለፈሉት የዘመድ ጠላቶች ልሂቃን፤ ከባእዳን ቅኝ ገዥወች እጅግ የከፉ በመሆናቸውም፤ ብሄር በሄረ ሰቦች የሚለው መፈክር የፈዘዘና ያረጀ ሲመስላቸው፤ “አንተ ኩሽ ነህ። አንተ አይደለህም” የሚል እረፍት የሚነሳ ሰይጣናዊ መርዝ በደሙ ውስጥ በማሰራጨት ላይ እንዳሉም ወጣቱ ፈጥኖ ሊረዳቸው ይገባዋል።

 

የጥንት አባቶቻችን ለኢትዮጵያ አንድነት የጠቀሙባቸውን ሁለገብ መስተጻምራት ወጣቱ ቢረዳ፤ ከባእድ የጎረሱትን መርዝ የሚተፉበትን እነዚህን የመሳሰሉትን መርዘኞች ከመስማትና ከመከተል ራሱን አግልሎ፤ ከቅኝ ገዥወች በምን ትሻላላችሁ ብሎ አዋርዶ ያብርራቸው ነበር። ወጣቱ ትውልድ እንዳይነቃባቸው ሊቃውንት ካህናትን ከየአውደ ምህረቱ፤ ያርበኝነትና የፋኖነት ስሜት ያላቸውን ከየመድረኩ እያስወጡ እንዳያይ ዓይነ ልቡናውን በሚሸፍን፤ እንደይሰማ እዝነ ልቡናውን በሚያፍን ባዶ ስብከትና ፕሮፓጋንዳ አጭበረበሩት።

 

ወጣቱ ትውልድ መስተጻምራቱን ባለማወቁ ኢትዮጵያ አገሩም ችግር ላይ ወደቀች። እርስ በራሱም ለመጠፋፋት በዝግጅት ላይ ተሰለፈ። ከታላላቅ ሊቃውንት አባቶቻችን አንዱ የሆኑት መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ባንድ ወቅት፦

 

“ኢትዮጵያ በወራሪወች ያልተደፈረችባቸውን ዜጎቿም እርስ በርሳቸው የተጣመሩባቸውን መስተጻምራት ወጣቶቻችንን ሳናስተምራቸው ወደ ውጭ አገር መላክ፤ የኛን ምሳሌነት መጥፋት ለሚፈልጉ ባእዳን፤ የፈለጋችሁትን ሙሉባቸው ብለን ባዶ ሸክላ መላካችንን አንዘንጋ። ሲመለሱ የሞሉባቸውን አተላ በኢትዮጵያ ይደፉባታል። ለመጥረግ በሚጥሩት ላይ የስራ ሸክም ማክበድ ይሆናል”

 

ብለው የተናገሩት ተፈጸመ። መላከ ብርሃን አድማሱ ባወረሱን ቅኔያቸው ዛሬም እየተናገሩን ነውና። ሊሰማቸው የሚፈልግ (ምንት እረባሁ) የሚለውን መንካት ይችላል።

 

አስኳላ ተማርን የሚሉ ዜጎች፦ ኢትዮጵያ የተሰራችባቸውን ዘዴወች በጥንቃቄ እየተመለከቱ መሠረትነታቸው እንዳይፈርስ እየተጠነቀቁ፤ ጎጂ ነገሮችን እያረሙ፤ ካስኴላው የተማሯቸውን ጠቃሚ እውቀቶችን ኢትዮጵያ ተጠብቃ ከቆየችባቸው መስተጻምራት ጋራ በመደመር፤ በቀደሙ አባቶቻችን ዘመን ከነበረችበት ሉዐላዊነት በበለጠ ልዕልና ላይ ኢትዮጵያን ማስፈን ሲገባቸው፤ ራሳቸው በሁሉ ነገር ፈራሾችና፤ ሁሉ ነገርንም አፍራሾች ሆነው መገኘታቸው ከመላከ ብርሃን አድማሱ የሰማሁትን አረጋገጠለኝ። እሳቸው በሚጠሩበት ስም መላከ ብርሃን ተብየ መጠራቱንም ሸሸሁት። በዚህ ዘመን መፈጠሬንም እጅግ ጠላሁት።

 

በየዘመናቱ የውጭ ጠላት በኢትዮጵያ ላይ የሚነስነስውን ኅብረተሰብ በታታኝ መርዝ፤ አባቶቻችን እየጠረጉ በትንቅንቅ ያቋረጡትን ዘመን ከዘመናችን፤ ያባቶቻችንን ትውልድ ከትውልዳችን፤ አባቶቻችን የነበሩባትን ዓለም እኛ ካለንበት ዓለማችን፤ ኢትዮጵያ ለዘላልም እንድትኖር የተጠቀሟቸውን መስተጻምራት፤ የዘመኑ ልሂቃን “እስከ መገንጥል” ከሚሉት መርኋቸው ጋራ ወጣቱ እያነጻጸረ ቢመረምረው፤ የዘመናችን ልሂቃን ኋላ ቀር ባላገሮች እያሉ የሚነቅፋቸው አባቶቻችን ከዘመናችን ልሂቃን ይልቅ እጅግ የላቁ፤ ዘዴዎቻቸውም ከነሱ አገር አፍራሽ ዘዴወቻቸው እጅግ የረቀቁ እንደነበሩ ይረዳ ነበር።

 

ያባቶቻችን ዘዴዎች ከኛ ዘዴዎች እጅግ የረቀቁ እንደነበሩ መረዳት ብቻም አይደለም፦ Margaret J. WHEATLEY የተባሉት ሊቅ DISCOVERING ORDERING IN A CHAOTIC WORLD በሚል ርእስ በጻፉት መጽሐፍ (page 20) ላይ “While we humans observe and count separate selves, and pay a great deal of attention to the differences that seem to divede us, in fact we servive only as we learn haw to partispate in a web of relationships” እያሉ ቢሚያስተምሩበት ዘመን፤ የኛ ያስኳላ ትምህርት ልሂቃኖቻችን፤ ዓለምን ባስደነቀ ኩራትና ክብር አባቶቻችን የተሻገሩት የጨለማው ድንጋይ አደናቅፏቸው ባስከፊ ሁኔታ የእንግላል መውደቃቸውና ሁሉንም ያጡ ጎመኖች በመሆናቸው እጅግ ያዝንባቸው ያፍርባቸውም ነበር።

 

የቀደሙ አባቶቻችን እጅግ የተሻሉ እንደነበሩ ለትውልዱ ለማሳየት፤ መደመር የምንላት መርሆ በጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይ አንደበት ከመገለጿ በፊት፤ በያመቱ የምናስታውሰውን የደመራ በዓል ምክንያት በማድረግ ለአራት ዓመታት በማከተታል ቀርባ ነበር። ጳጉሜ 2ሽ 10 ዓ/ም በኢትዮጵያ ኢማባሲ ዋሽንግተን ዲሲ አዳራሽ በተደረገው

 

ስብሰባም ቀርባ ነበር። እንደገና ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ/ ም አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ስብሰባም ቀርባ ነበር።

 

ይህ ሁሉ ጥረት የቤተ ክርስቲያናችንን ያብነት ትምህርት ለተሳተፉ ኢትዮጵያውያን የመደመር ጽንሰ ሀሳብ እንግዳ አለመሆኗን ገልጾ ለማሳየት ነበር። ይሁን እንጅ በዚህ ዘመን በጠቅላይ ምኒስተር ዓቢይ አንደበት የተነገረችው የእንደመር መርሆና፤ በቀደሙ አባቶቻንችን በነበረችው የእንደመር መርሆ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ለማሳየት አሁን እንደገና በተሻለ መንገድ ቀርባለች።

 

በየዘመናቱ ከወደቁበት ተነስተው ከተበተኑበት ተስብስበው እንደመር ይሉ የነበሩት የቀደሙ አባቶቻችን በጸሎትና በተግባር ተጠንቅቀው ነበር። መጀመሪያ “ወእምኩሉ ምግባረ እኩይ አግህሰነ” ማለትም ክፉና ሸፍጠኛ ህሊና ካለው ሰው ጋራ እንዳንደምር ጥበቡን ስጠን” እያሉ፤ ቀጥለውም “ደምረነ ምስለ እለ ይድህኑ” እያሉ ነበር። ማለትም፦ ራሳቸውን ከሸፍጥ አላቀው፤ ህዝቡንም ከሸፍጠኞችና ከሸረኞች ለማላቀቅ ጸንተው ከተሰለፉ ታማኝ ወገኖች ጋራ ብቻ ደምረነ እያሉ በመጸለይ ይደመሩ ነበር። ከፍና ዝቅ እየደረገ ደረጃውን በሚቀያይር መሰላል ከምትመስል ሱስነት ይልቅ፤ በደመነፍስ ጽምረት ወደ ሰፈነችው ነፍስነት ኢትዮጵያን በማሻገር ይደመሩ ነበር።

 

የቀደሙ አባቶቻችን ከፍና ዝቅ እያለ በሚቀያየረው በሱሳቸው ላይ ኢትዮጵያን ሳይመሰረቱ፤ በማትቀያየረው በደመነፍሳቸው ላይ መስርተው ህዝባቸውን እንደ ሙጫ ያያዙባቸውን አምስቱን መስተጻምራት እንደገና ለመቃኘት ትድምርትንና ተግህሶን ለመግቢያየ መንደርደሪያ አድርጌ መጀመሪያ ጳጉሜ 2ሽ 10 ዓ/ም በኢትዮጵያ ኢማባሲ ዋሽንግተን ዲሲ አዳራሽ ቀርባ የነበረችው ጦማር እነሆ እንደገና አቀረብኳት።

 

ትድምርት እና ተግህሶ

 

ትድምርት ተግህሶ በጸሎት መጽሐፋችን ተደጋግመው የተጻፉት በጥንቃቄና በትኩረት ተረደተናቸው የሕይወታችን መመሪያወች አድርገን ለህዝብ እንድናስተምራቸው እንጅ ለጻማከናፍር አይደልምና ተግህሶን በማስቀደም ተራ በተራ እንመልከታቸው።

 

አባቶቻችን ኢትዮጵያን ለመጠበቅ የተጠቀሟቸውን መስተጻምራት በጥልቅ ለመረዳት ”ተግሀስ እመ እኩይ ወግበር ሠናየ“ በምትለው ሐረግ ላይ የተመሰረቱትን ትድምርትንና ተግህሶን አስቀድመን ብንመለከታቸው ያባቶቻችን ትድምርት እጅግ የረቀቀች እንደነበረች አጉልተው ያሳዩናል። ለሰባዊ ፍላጎት ተቃራኒ፤ ለመለኮታዊ ህግና ትእዛዝ እንቅፋት የሆነ ነገር ሁሉ እኩይ ነው። የጸዳ ህሊና ሳይኖረው የጸዳ መስሎ ሊደመርህ ከሚሞክር ጋራ አትደመር። ይህን መመሪያህ ሳታደርግ ከእኩያን ጋራ ብትደመር “ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርምር እራቅ ”(2ኛ ጢሞ 2፡23)። ብሎ በሊቁ በገማልያል ጉባዔ የተቀረጸው ጳውሎስ የተናገረው ይገጥምሀል” ብለው አባቶቻችን ነግረውናል።

 

“እስከመገንጠል ድረስ” እያለ ከሚሰብክና፤ አፍራሽ በሆነ ህግ ልምራችሁ ከሚል መንግስት ከመሸሽ በምድር ላይ ምን የምንሸሸው የከፋ አካል ይኖራል? እነዚህን የመሳሰሉትን መሪወችንና አስተማሪወችን ከህዝብ መካከል መንጥረን እንድናወጣቸው ፤ በእንክርዳድ፤ በጭልፊትና በቀበሮ እየመሰለ አትናቴወስ ነግሮናል።

 

መገንጠልን በሚሰብክ መንግስት መመራት ይቅርና እንድንታገለው፤ ህብረተ ሰብ እያመሰ ባዘጋጀው አሻሮ መሳይ ህግም እንዳንታሰር “ወእምተደምሮ በዕልወት ወርኩስ ምስለ አላውያን ወአረማውያን (102፡85: _86) የሚል ተጽፎልናል። ይህም፦ በእውነት ካልቆሙ ቃላቸውን በመቀያየር ህዝብ ከሚያወናብዱ ከከሀዲወችና ከጨካኝ አረማውያን ጋራ እንዳንተሳሰር እርዳን” ማለት ነው።

 

የአህያ ሥጋን ከመብላት የሚገታንን ጽዩፍነታችንን፤ ይህን የመሰለ ባህርይ ካላቸው ሰዎች ጋራ ምንም ተሳትፎ እንዳይኖረን የበለጠ እንድንጠቀምበት “ ንህነሰ ናስቆርር ኩሎ ግብሮሙ ለዕልዋነ ሃይማኖት ወኩሎ ፍልጠተ ወዐሊወ ህግ እስመ ርኩሳን እሙንቱ በኀቤነ“

 

(81 41)እያለ መጽሀፈ ቅዳሴያችን አጠንክሮና አጽንቶ ያስጠነቅቀናል።

 

ጧት ታይታ ማታ እንደምትጠፋ እጸከንቱ ናቸውና በሚፈጽሙት እኩይ ተግባር፤ በሚዘርፉት ሀብት የከበሩና የሚዘልቁ መስለው የሚታዩትንም እንድንርቃቸው አባቶቻችን “ኢትቅና ላዕለ እኩያን። ወኢትቅና ላዕለ ገበርተ አመጻ።እስመ ከመ ሳእር ፍጡነ ይየብሱ”(36፡1) ብሎ ዳዊት በተናገረው ስሜታችንን ቀርጸውት ነበር። ማለትም ክፉ ሰዎች በክፋ ስራቸው አብበው ለምልመው ብታያቸው እንደነሱ በሆንኩ ብለህ አትመኝ፤ ጊዜአዊ ኃይላቸውን እየተጠቀሙ የሚፈጽሙትን ተድላና ደስታ አጥብቀህ ሽሸው። እንደሳር ፈጥነው ሲረግፉ ታያቸዋለህ። ይልቁንስ ”ተግሀስ እመ እኩይ ወግበር ሠናየ“ እንደነዚህ ካሉት እኩያን ሸሽተህ የጎበጠውን ለማቅናት የተጣመመውን ለማስተካከል ከሚታገሉት ጋራ ተደመር። ከዚህ ቀጥለን ትድምርትን እንመልከት።

 

ትድምርት

 

ያብነቱ መምህራን አባቶቻችን ትድምርትን ባንድምታ ፈሊጣቸው በብዙ ምሳሌወች ነግረውናል። ከጠቀሷቸው ብዙ ምሳሌወች፦ ያእቆብ ዘስሩግ (መ. ቅ. ገጽ 350፡ 68) ሌሎችም እንደ እነ ጎርጎርዮስን የመሳሰሉት ሊቃውንት እየደጋገሙ የጠቀሷት የምንቆርባት ህብስት ናት (መ. ቅ. ገጽ 373፡ 27_28)።

 

“ወበከመ አስተጋባእካ ለዛቲ ኅብስት እንዘ ዝሩት ይእቲ ውስተ አድባር ወአውግር ወታጋቢአ ኮነት አሐተ ኅብስተ ፍጽምተ ወከማሁ ኪያነሂ አስተጋብአነ በመለኮትከ እምኩሉ ሕሊን እኩይ፡ ውስተ ሃይማኖት” ብለዋል። ማለትም፦ ይህች ህብስት አካታ የያዘቻቸው የስንዴ ፍሬዎች ሲዘሩ በጎርፍና በማእበል ከመወሰድ፤ ቡቃያነታቸው በቁጥቋጦ በእሾህ ከመታፈን ያዳንክ፤ አውድማ ላይ ወድቀው ሲበራዩ፤ ገለባውን ለይቶ ለሚያጠራቸው ነፋስ ሲበተኑ

ከመጥፋት አድነህ ፤ እንደገና ወደ ዱቄት ተለውጠው በውሀ ተለውሰው በእሳት ተዋህደው ወደ አንዲት ህብስትነት እንዲለወጡ ያደረክ” ይሉና፦ የተለያዩ ፍሬወች ተዘርተው ህብስቷን እስኪሆኑ ድረስ ያለፉባቸውን መከራ ወደ ህብረተ ሰብ በማምጣት፤ በብዙ መከራ ካለፉት ጋራ በመንፈስና በአካል እንደዚህች ህብስት ደምረን” ይላሉ።

 

በቃላቸው እያነበቡ፤ በሥጋቸውና በመንፈሳቸው በተግባራቸው እየተረጎሙ ያለፉት አባቶቻችን እነዚህን ከመሰሉ ኢትዮጵያውያን ጋራ መደመር እንዳለብን ደጋግመው ነግረውናል። እንዳንረሳትም በየሳምንቱ እሁድ “ደምረን ምስለ እለ ይድህኑ” እያልን በጸሎት መልክ እንድንደጋግማትም ሊጦን በምንላት መጽሐፋችን አስተምረውናል። ከዚህ ቀጥየ ወደ መግቢያዋ እሻገራለሁ።

መግቢያ

 

መግቢያዋን በሶስት ክፍል ማለትም፦1ኛዋ ክፍል አምስት መስተጻምራት ስትሆን በስሯ ከሀ እስከ ረ ተራ ፊደል የተዘረዘሩትን ንዑሳት አናቅጽ ይዛለች። 2ዋ ክፍል አርበኝነት ናት። 3ኛዋ ክፍል ከሀ እስከ ሠ የተረዘሩትን ንኡሳት አናቅጽ የያዘችው ኢትዮጵያዊት ቅኔ ናት። ቅርጽና ይዘታቸውን መቃኘት ከፈለጉ ከዚህ በታች ይመልከቱ።

ክፍል 1 አምስቱ መስተጻምራት

ሀ. ባለአገር፤

ለ. ባለጋራ፤

ሐ. ባለአምጣ፤

መ. ባለደም፤

ሠ. ባለቤት

ረ. ክልል

ክፍል 2 አርበኝነት

ክፍል 3 ኢትዮጵያዊት ቅኔ

ሀ. ኮፌዳ፤

ለ. ውጥንቅጥ፤

ሐ. ሰምና ወርቅ፤

መ. ሰረዝ ፤

ሠ. ዓባይ

 

ከዚህ በላይ ቅርጻቸውን የዘረዘርኳቸው፤ ከዚህ በታችም ይዘታቸውን የማብራራቸው አምስቱ መስተጻምራት ባብነቱ ትምህርት ቤት ሳለሁ የእለት ምግቤን (ውጥንቅጥ) ለማግኘት በገጠር በገዳማትና በአድባራት ከነበሩት ከሊቃውንት አባቶች የተማርኳቸው፤

ከባለአገሩም በፉከራና በቀራርቶ እየሰማሁ ያደኩባቸው ናቸው። የቀደሙ አባቶቻችን መስተጻምራት ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነና እንዴትስ እንደተጠቀሙባቸው ለመግለጽ በክፍል አንድ እጀምራለሁ።

ክፍል 1፦ አምስቱ መስተጻምራት

ከሀ እስከ ሠ የተዘረዘሩት አምስቱ መስተጻምራት፦ ባለ የምንላትን ሁለት ፊደላት መነሻ በማድረግ የህብረተ ሰቡን ስነ ህሊና ያጠናቀሩ ቃላት ናቸው። እነሱም፦ አገር፤ ጋራ፤ ደም፤ አምጣና ቤት፤ ናቸው። እነዚህ ቃላት የኢትዮጵያን ህዝብ ህብርነት ውህደት፤ ሰምና ወርቅነትና ሰረዝነትን የሚያንጸባርቁ ናቸው። በነዚህ መንፈስ ከተጣመረው ኢትዮጵያዊ ኀብረተሰብ ማህጸን ባለአገርነት ተጸንሶ ይወለዳል። ባለ አገር ምን ማለት ነው?

ሀ. ባለ አገር

አርበኝነትን ጸንሶ የሚወልደው ባለ አገር ምን ማለት ነው? በምዕራቡና በምሥራቁ ትምህርት ታዝሎ ወደኢትዮጵያ የገባው አባቶቻችን አተላ ያሉት nation nationalisim የተባለው ወራሪ ቃል የባለአገርን ትርጉም በኋላ ቀርነት ገልብጦ ኢትዮጵያውነትን ከወጣቱ ጭንቅላት አጥቦ እስኪያወጣው ድረስ፤ በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በተካተቱት ጎጆዎች፤ መንደሮች፤ አጥቢያወችና ወረዳወች የተወለደ ሁሉ ለመላ ኢትዮጵያ ሁለንተና ባለ አገር ነበር። ኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር አገሩ ነበረች። የባለአገር ትርጉም ክብር፤ ኩራት፤ እንጅ ውርደት ስድብና ኋላቀርነት አልነበረም። ለመወሀድ ከሚላላሳት ማርና ከሚተባበሳት ቅቤ ይልቅ የኢትዮጵያን ዜጋ እንደ ሙጫ ሆና አጣምራ የያዘችው ለደምነቱ ነበረች።

 

ለ. ባለ ደም

“እስመ ነፍስ ተሀድር በደም”(ዘሌ 17፡11) እንዲል መጽሐፍ፦ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አንዱ ላንዱ ባለ ደም ነው። በሰውነታችን የሚመላለሰው ደም የነፍሳችን ዙፋን ነው። ደም ከሌለ ነፍስ የለም። ህልውናችን ደማችን ነው። ባለደም ማለት፦ አንተ ለኔ የደሜ ባለቤት ነህ፤ እኔ ላንተ የደምህ ባለቤት ነኝ፤ ደምህን እጋራለሁ። ደምህ ደሜ፤ ደሜም ደምህ ነው። ህይወትህ ህይወቴ ነው። እኔ ያላንተ፡ አንተ ያለኔ፡ ህይወት የለንም ማለት ነው። ይሁን እንጅ በሩቅ ዘመን ዳህጽ አተረጓጎም፤ ትርጉሙ መሰረቱን ለቆ በግድያ ወደ ሚፈላለጉ ወገኖች ተገልብጧል። ቀጥለን ባለጋራ የምትለውን ቃል እንመለከታለን።

 

ሐ.ባለጋራ

ጋራ (አንድነት ወይም እኩል ) የምንላት በሁለት ፊደላት የተዋቀረች መስተጻምር የተለያዩ ስሞችንና ይዘት ያላቸውን አካላት በእኩልነት እያሰለፈች ለህልውናቸው የሚጠቅሟቸውን ነገሮች እኩል የሚካፈሉትን አካላት ታሳያለች። “ጋራ” የምትባለው ሁለት ፊደላት መስተጻምር “ባለ” የምንላትን አገናዛቢ ሁለት ፊደላት ተንተርሳ ወደ ህብረተ ሰብ ስትቀርብ፤ በክልል በጎሳ በቋንቋና በሃይማኖት ተሰንቅሮ በጎረጥና በከረረ ጥላቻ

የሚተያይበትን መንፈስና ስሜ አፍርሳ፤ ኅብረተ ሰቡን በማይበጠስ ስነ ልቡናዊ ሰንሰለት አስተባብራ የምታስተሳስር ነበረች። ጋራ የምትለውን ቃል ለየተ ባለ አነጋገር ስንጠቀም ደግሞ “አጋር” ትሆናለች። አጋር ማለት፦ የሚረዳ የሚታደግ የሚያግዝ ዘመድ ወገን ማለት ነው።

“አንተም ሰርተህ ብላ፤ አንችም ሰርተሽ ብይ፤

ያለ አጋር እንጀራ አይበላም ወይ” እንዲሉ።

“ባለ” ከእለት ምግባችን ከእንጀራ ጋራ ስትጣመር በልእንጀራ ትሆናለች። በወንፈል በደቦ በሀዘን በደስታ አብረው አድገው የደረሰባቸውን እያወጉ ለትውልዱ እያሻገሩ የሚያልፉ በሥጋ በደም የተሳሰሩ ማለት ነው። በመቀጠል የአንጣ ወይም አምጣን አጠቃቀም እንመልከት።

መ፦አምጣ አንጣ፦

ውነታችን ይመጋገባል፤ ይቀባበላል፤ ይረዳዳል፤ ይተጋገዛል፤ ይግባባል፤ ይዋዋሳል ይወሳሰዳል፤ ይበዳደራል፤ ያበደርኩሁ ያበደርከኝ፤ ያቀበልኩህ ያቀበልኝ፤ ያዋስኩህ ያዋስከኝ፤ የሰጠሁህ የሰጠኸኝ የምመልስልህ የምትመልስልኝ፤ የምታመጣልኝ የማመጣልህ ባለ አምጣህ ነኝ፤ ባል አምጣየ ነህ፤ በመባባል አንዱ ባንዱ ህሊና ውሥጥ ያለውን የወገንነትንና የዜግነትን መንፈስ ለመቀባበልና ለመወራረስ ይፈላለጋል ይሳሳባል። ይህም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ሁለንተና በእኩል ባለቤት ነው።

ሠ፦ ባለ ቤት

ባለ ቤት፦ ቤት ሁለት ትርጉም አለው። ለመኖሪያ የሚሰራው ህንጻ ሲሆን፤ ሌላው በውስጡ የሚኖሩት ባለ ቤቶች (ባልና ሚስት) ናቸው። ጥምረታቸውን ለመግለጽ ወንዱ ለሴቷ ባለቤቷ ነው። ባለቤቴ ትለዋለች። ሴቷም ለባሏ ባለቤት ናት። ባለቤቴ ይላታል። ቤቱ ሁለቱንም አጣምሮ የእኩልነት ንብረት ነው። ከዚህ በላይ በዘዘርናቸው በባለ አገር፤ በባለ ጋራ፤ በባለ ደምና በባለ አምጣ ለሚነካካ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያ መኖሪያቸውና ማደሪያ ቤታቸው ናት

ዘርፉ ቅጽሉና ምሳሌው ተሰማምቶ፤ ዜማውን ሳይሰብር፤ በማሰሪያ ግስ ህብር ተቀምሮ፤ በሚቃረን ሀሳብ (በፍርቅ ጸያፍ ሳይወላግድ) ሳይካለል የሚቀርብ አመርቂ ቅኔ ቤት መታ ይባላል። በኢትዮጵያ ያለው ህብረተ ሰብ እርስ በርሱ ሲጋባ፤ አንዱ ባንዱ ሰውነት፤ መንደር፤ ወረዳና አውራጃ ሰርጎ በመግባት ሲሰርግና ሲሰራረግ “ወሤምኮ ውስተ ኩሉ ግብረ እደዊከ” እንዳለው ሁሉም እርስ በርሱ ተሰያየመ። ማለትም፦አንዱ ካንዱ የተካለለበትን አጥር አፈረሰ ማለት ነው።

ረ፦ክልል

ክልል በዘመኑና በህብረተ ሰቡ ባህርይ መቀያየር ላይ ተመስርታ ዘመንና በዘመን ውሥጥ የተለያዩ ሚናወችን የሚጨወቱትን የሰዎችን ባሕርያት ትገልጻለች። ተጻራሪ የሆኑ የልዕልናና የውርደት ትርጉሞችን ትፈጥራለች። የክብር፤ የልዕልና፤ የሞገስና የግርማ መግለጫ ስትሆንወይኬልልዎ ለመድኃኔ ዓለም እያልን የኢየሱስ ክርስቶስን ልዑለ ባሕርይ

እንገልጽባታለን። ተልኳቸውን በተገቢው መንገድ የተወጡትን ለማሳየት ወደሰው ስናመጣት “ክብረ ወስብሐተ ከለልኮ ወሴምኮ ውስተ ኩሉ ግብረ እደዊከ። መዝ 8፡1᎗9 እንዲል፦ መከበርን መወደድን መፈቀርን መሾምን ታንጸባርቃለች።

ዘመኑ ተቀይሮ ዘመነመንሱት ሲሆን፤ ሰወች ተልእኴቸውን ሲስቱ “ሕቀ አህጸጽኮ” እንዲል፦ ክልል ሕጸጽ በምትባለው ቃል ታጅባ፤ ትርጉሟ ወደ ተቃራኒው ይገለበጣል። መጉደለን፤ መዋረድን ማነስን፤ መቀነስን፤ መካለለን፤ መወጋገድን፤ መቆራረጥን፤ መለያየትን ታመለክታለች። በዚህ ወቅት ኅብረተ ሰቡን አጥሮና ቀይዶ የያዘውን ክልል ደርምሰው፤ የተጋረደበትን ጥቁር መጋረጃ ቀዳደው ነጻ ለማውጣት የተዘጋጁ ፋኖወችና አርበኞች በህብረተ ሰቡ መካከል ይከሰታሉ።

ክፍል 2 አርበኝነት

አርበኛ ከማይደርቀውና ከማይነጥፈው ህብረተ ሰብ ማህጸንና አብራክ በመከራ ጊዜ የሚመነጭ ለኢትዮጵያ ዘበኛና ቤዛ ሊሆን ከየመንደሩ የሚወልድ ቡድን ነው። ቃሉ አኀዛዊ ለዛና ትርጉም አለው። ይሁን እንጅ ህብረተ ሰባችን በሩቅ ዘመን ዳህጸ ልሳኑ 40ኛ የሚለውን አኀዛዊ ቃል ወደ ልሙጥነት ቀይሮ አርበኛ ይለዋል። ለረዥም ዘመን በቅኝ ገዥዎች ያልተገዛ ኢትዮጵያውያንን የመሰለ ህዝብ ባንድ ወቅት የጀመረውን ነገር ጽንሰ ሀሳቡን ሳይረሳ፤ ስም አጠራሩን በዳህጸ ልሳን እየቀየረ ለትውልድ ማቀበሉ የተረጋገጠ ነው።

ለምሳሌ ኢትዮጵያን ጦቢያ፤ ነነዌ የሚለውን ነይነይ እያለ አጠራራቸውን በመቀየር እንደሚጠራቸው ማለት ነው። እንደዚህ ሁሉ ህብረተሰባችን 40ኛ የምትለውን አኀዝ ወደ ፊደለኛ አነጋግር በመለወጥ በልማዳዊ ዳህጸልሳን አርበኛ እንደሚላት ያብነት መምህራን ነግረውናል። የ40ኛን ስርጸት እንዴት እንደሚገልጿት ከዚህ በታች እንመልከት

ያንድምታው መምህሮቻችን የ40ኛነት ስርጸት ለመረዳት በዮቶርና በሙሴ መካከል

የነበረውን የማቀበልና የመቀበልን ጸጋ ተመልከቱ ይላሉ “ስምአኒ እንዘ እመክረከ

ወእግዚአብሔር የሀሉ ምስሌከ ወኩኖሙ ለህዝብ ወለእግዚአብሔር ወትበትክ ቃሎሙ ”

(ዘጽ 18፡19)ብሎ ዮቶር ለሙሴ የሰጠውን ምክርና ጥበብ ተቀብሎ፤ እስራኤላውያንን ነጻ

ለማውጣት ሙሴ በአርበኝነት ስሜትና መንፈስ ተንቀሳቀሰ። “ወአመ ተፈጸመ አርባ አመት

ሐለየ በልቡ የሐውጾሙ ለአኀዊኍ (የሐዋ 7፡ 23)። እንዲል፦ ማለትም፦የዮቶርን ምክር

የሰማው ሙሴ 40ኛው አመት በተፈጸመ ጊዜ ወገኖቹን ነጻ ለማውጣት ልቡ ተነሳ።

አባቶቻችን ከዚህ በመነሳት 40 ዘመንን ሰው ቁም ነገር ለሚሰራበት እድሜው ማእከል ናት

ይላሉ።

ህይወቱን በትግል ጀምሮ በንስሀ የፈጸመው ዳዊትም “እመሰ በዝኃ ሰማንያ ዓም

ወፈድፋዶንሰ እምእላ ጻማ ወህማም” (መዝ 89፡9) ብሎ በተናገራት ሐረግ፤ አባቶቻችን

አርበኛን ጽንሰ ሀሳብ አጠናክረዋታል። ይህም ማለት፦ሰው በዚህ ዓለም የቆይታ ዘመኑ ግፋ

ቢል ሰማንያ ነው። ሰውነቱ ሳይከብደው፤ ወገቡ ሳይያዝ፤ ቋንጃው ሳይቀየድ፤ ጉልበቱ

ሳይደነዝዝ፤ አእምሮው ሳይፈዝ፤ ህሊናው ሳይነፍዝ አቀበት ወጥቶ ቁልቁለት ወርዶ

የፈለገውን መፈጸም የሚችለው እስከ 80 ዘመኑ ነው። ሰው የፈለገውን የሚፈጽምባት አፍላ ዘመኑ የ80 ዘመኑ ማእከል የሆነችው 40ኛዋ ዕድሜ ናት።

የአርባኛነትን ጥንቅር በትኩረት እንመልከታት። የተባለችው ፊደል ሆና አርባኛን

በመቀየር አርበኛ ታሰኛታለች እንጅ አርባኛ40ኛማለት አኀዝ ነው። ነፍጠኛ የምትለውን ቅጽል የተረዳንባት የምንላት ፊደል ለአኀዝ ትራስ በመሆን ወደ መግለጫ ቅጽልነት እንደተቀየረች ማለት ነው። ለምሳሌ፦ ፈረስ በሚለው ላይ ስትደመር ፈረሰኛ፤ በአንድ፤ በሁለት፤ በአስር ቁጥሮች ላይ ትራስ ሆና ስትደመር ወደ ገላጭ ቅጽልነት ይለወጣሉ። እንደዚሁም 40 ቁጥር ላይ ትራስ ሆና በመደመር 40ን የአኀዝነትን ትርጉም ሳታስለቅቅ ግብር ገላጭ ቅጽል ታደርጋታለች።

 

አባቶች ሊቃውንት እንደሚሉት፦ በሀገር ላይ ዜጋን የሚፈትን ጠላት ሲከሰት 40ኛ ይጠራራል። 40ኛ (አርበኛ) የሠራዊት እጥረት ቢገጥመው ከራሱ 40ኛ ዕድሜ ዝቅ ወይም ከፍ ያለ ፋኖ (ወዶ ዘማች) በጥንቃቄ ይመለምላል። ይህም ማለት በጦር ሜዳ የሚሰለፍ ከ20 እስከ 60 ባለው እድሜ ክልል ያለ ዜጋ ነው። ከ20 አመት እድሜ በታች ያሉት ወጣቶች እንዲሰለፍ አይገፋፉም፤ ከ60 በላይ ያሉ አዛውንቶች እንዲዘምቱ አይደግፉም።

 

ከ20 አመት እድሜ በታች ያለ ወጣት በግንባር ቀደም ለጦርነት እንዲሰለፍ የማይገፋፉት በእሳታዊ ባህርዩ ፈጥኖ በመገስገስ በሚወስደው ርምጃ በጥንቃቄና በጥናት ተዘጋጅቶ ለመጣ ጠላት እንዳይጋለጥ ሊጠነቀቁለት እንጅ፤ በፍታውራሪ ተክለ ሐዋርያት እንደተገለጸው ፤ ከ20 እድሜ በታች ባለው ወጣት ውስጥ ያለውን ኃይል ዘንግተውት አይደለም።

 

የአለቃ ገ/ ዮሐንስ የቅኔ ተማሪ የነበሩት ታላቁ አባታችን ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት በአድዋው ጦርነት ጊዜ የተፈጸመውን ትዝታ ባሰፈሩበት መጽሐፋቸው ከገጽ 55 እስከ 76 ላይ እንደምናነበው፤ ከ20 እድሜ በታች ያሉ ወጣቶች በግንባር ተሰልፈው ከሚዋጉት 40ኞች ጋራ ተቀላቅለው በመዋጋት ላይ ሳሉ፤ 40ኞች ለይተው ከጦር ሜዳ በማውጣት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተቆጥተው ቢሸኟቸም፤ እንደገና እየተደበቁ ወደ ጦርነቱ ሜዳ በመቀላቀል ታላቁን ጀብዱ እንደፈጸሙ ነግረውናል።

 

በደማቸው ውስጥ በሰረጸችው በአርበኛነት ስሜት የዜግነታቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ያለፉት የዘመናችን ልሂቃን ባለገሮች እያሉ የሚንቋቸው አርባኞች አባቶቻችን፤ ወራሪዎችን ተዋግተው በማሸነፍ ድል የተቀዳጁባቸውን መሳሪያወች፤ የተሸለሟቸውን ለምድ፤ ቀሚስና ካባ እንደ ሌሎች ቆሳቁስ በሥጋ ለወለዷቸው አላወረሱም። እስከ ዓለም ፍጻሜ በምድር ላይ በምትቆየው በቤተ ክርስቲያናቸው እቃ ግምጃ ቤቶቻችን እንዲቀመጡ ያደረጉት፤ በየዘመናቱ የሚኖሩት ካህናት በየዘመናቸው ላለው ትውልድ፤ አባቶቻቸው ኢትዮጵያን ጠብቀው ያቆዩባቸውን መስተጻምራት የማይዘነጉ ቅርሶች መሆናቸውን እንዲመሰከሩ ነበር።

በመስተጻምራቱ አማካይነት ኢትዮጵያን በደመ ፍሳችን እንድትቀረጽ ወዳደረገችው ኢትዮጵያዊት ቅኔያች ለመሻገር በኮፌዳችን እንጀምራለሁ።

 

ክፍል 3 ኢትዮጵያዊት ቅኔ

ሀ. ኮፌዳ

 

ኮፌዳ ከሰሌን ወይም ከቄጠማ የምንሰራት በየመንደሩ እየዞርን በመለመን የምንሰበሰበውን ምግብ ለመያዝ የምታገለግለን ዕቃ ናት። ከህብረተ ሰቡ የምንሰበስበው ልዩ ልዩ ምግብ ወደ ኮፌዳችን ሲገባ ስሙን ለወጥን ውጥንቅጥ እንለዋለን። በቅኔ ትምህርታችን ኮፎዳችንን ሰም ኢትዮጵያን ወርቅ እናደርጋታለን። ከህዝቡ የምንሰበስበውን ውጥንቅጥ ህዝብ ገላጭ ሰም እያደረግን፤ በቋንቋና በሃይማኖት ተወናቅጦ በጠረፏ ክበብ ሰብስባ የያዘችውን አገራችን ኢትዮጵያን ወርቅ እያደረግን እንቀኛለን።

 

በወርቅነት የምንገልጻት ኢትዮጵያም ድንበሯ ቢገሰስ እኛነታችን ስለሚበታተን፤ ያለብንን ብሄራዊ ግዴታ፤ እዳና ፍዳ ከመክፈል የሸሸውንና የተኛውን ህሊናችንን የሚገርፍ ቅኔ እንቀኛለን። ይህም ማለት በሰምነት የምታገለግለን ኮፌዳችን ብትቀደድ ውጥንቅጣችን ስለሚፈሰብን እንዳትቀደድ እንጠነቀቅላታለን። ኮፌዳችንና ውጥንቅጣችን ህብረተ ሰቡን የምንማርባቸው ለቅኔ ትምህርታችን መነሻችና ፊደሎች ናቸው። ተደበላለቆ ለተጣመረው ህብረተ ሰባችን በሰምነት ከማገልገሏ ባሻገር ውጥንቅጥ ሌላም ትርጉም አላት።

ለ. ውጥንቅጥ

 

ውጥንቅጥ ተጨማሪ ባህርይ ገላጭ ትርጉም አላት። ቃሏን ሰንጠቀን በሁለት መንገድ እንጠቀምባታለን። ውጥን (ጅምር) እና ቅጥ (ቅርጽ) ብለን እንሰነጥቃታለን። ውጥን የምትባለውን ቃል ቅጥ ለምትባለው ቃል ገላጭ ቅጽል በማድረግ፤ እንዳይጎብጥና እንዳይወላገድ ሆኖ በኢትዮጵያዊት ቅኔ ስነ ልቡናው የተወጠነ ኢትዮጵያዊ ማለት እንደሆነ አስረድተውናል።

 

የበለጠ ስትብራራ ቀጥ ያለ አቋም ያለው የማይወላውል ኢትዮጵያዊ ማለት ይሆናል ብለውም ነግረውናል። ሌላም ትርጉም አላት። በመስተጻምራት ተዝጎርጉሮ፤ ተነባብሮና ተባብሮ በሰምና ወርቅ የተገመደ፤ ባእዳን ሊተረጉሙት የማይችሉት የተወናቀጠ ኢትዮጵያዊ ስነ ልቡና እንደሆነም ገልጸውልናል። ከቅኔወቻችን አንዷ የኢትዮጵያውነታችን ስነ ህሊና የተገመደችባት ሰምና ወርቅ የምናላት ቅኔያችን ናት። ምን እንደምተመስል እንመልከታት።

ሐ. ሰምና ወርቅ

 

ሰምና ወርቅ ማለት ምን ማለት ነው?የሁለቱ ባህርያት የተላያዩ ናቸው። ሰም በቀላጭነት ባህርይዋ ለወርቁ ቅርጽና ይዘት ትለቃለች እንጅ ከወርቁ ጋራ አብራ አትዘልቅም። ስለዚህ ከወርቅ ጋራ ዕሪና (equilibrium) ስለሌላት የህብረተ ሰብ መግለጫ ሆና አታገለግልም። እኔ ወርቅነኝ እያለ በህዝብ ፊት ቆሞ የሚናገር ራሱን አቅላጭ፤ ሌላውን ቀላጭ ማድረግ ስለሆነ ፍርቅ ጸያፍ ለይቶ ያላወቀ ተማሪ ነው። በሌላ በኩል አድኖ በሚበላ አውሬና ታዳኖ በሚበላ እንስሳ መካከል ባለው ጥላቻና ፍቅር እንደሚለካ መምህራን

 

አስተምረውናል። ከዚህ ቀጥየ ይዘቷ ከሰምና ወርቅ በመስፋት ኢትዮጵያውነታችንን በድርብርብ መንፈስ ስለምትገልጸው ሰረዝ ስለምታበለው ቅኔ ከዚህ በታች ትንሽ መግለጽ ጠቃሚ ይመስለኛል።

መ. ሰረዝ

 

ይህች ቅኔ የበህረተሰቡን ድርብርብነትና የርስ በርስ መሳሳል ባህርይ የምትገልጽ ስለሆነች ሰረዝ ተብላለች። በድርብርብ ባህርይዋ ድርብርብ አካል ባለው በቀይ ሽንኩርትና፤ ድርብርብ ጥርስ ባላው ዶመ በሚስል በብረት ሞረድ ትመሰላለች። ጥርሱ ሲረግፍ ድድ ብቻ ሲሆን እየተወቀረ እንደገና አዲስ ጥርስ በማውጣት ብረት በሚስልና ጠጣር ጥራጥሬ በሚፈጭ የድንጋይ አይነትም ትመሰላለች። በዚህ የይዘት አቅሟ ብዙ የደራረቡ ወርቆችንና ብዙ ሰሞችን ደራርባ ስለምትይዝ ከመደበኛው ሰምና ወርቅ ቅኔ በይዘቷ ትሰፋለች። የተደራረቡትን ሰሞችናንና ወርቆችን በቅጽሎች እና በማሰሪያ ግሶች በዕሪና (equilibrium) ህብር እያደረገች አምስቱን መስተጻምራት አጉልታና አራቃ የያዘች ናት።

 

በዚህች ቅኔ ሊቃውንቱ ሳይወቀሩትና ሳይሳሉት ዳዊት በመድገም ብቻ የቄስ ተማሪ ነበርኩ ብሎ ማውራት ቅኔዋን ማርከስ፤ ሊቃውንቱን ማሳነስ ነውና ተገቢ አይደለም ይላሉ አባቶች።

 

ወደ ኢትዮጵያዊነት ስናመጣት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደ ቀይ ሽንኩርት ድርብርብ አካላትና ባህርያት አሉት። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየራሱ ቁመና ባባቱ ከሁለት ጎን፤ በናቱ ከሁለት ጎን፤ ቢያንስ ከአራት ድርብርብ ቤተ ሰቦች በተሸከመው ደም ግባት ሁሉንም አጣምሮ ኅብር የሚያደርግ ሰረዝ ቅኔ ነው።

 

ሁሉም አንዱ ያላንዱ ዶማና የዛገ ነው። አንዱ ላንዱ ሞረድ ነው። ይሞራረዳል ይሳሳላል። ባለአገሮች አባቶቻን ይህችን ሰረዛዊት ጽንሰ ሐሳብ መሰረት በማድረግ በሃይማኖት በቋንቋና በገጸ ምድር አሰፋፈር ምክንያት እንዳንለያይና እንዳንከፋፈል፤ ይልቁንም እንድንሞራረድ እንድንሳሳል በኅብርነት እንድንኖር በቅኔያቸው አስተምረውናል። ኅብር እና ሰረዝ በጥቂቱ የመወራረስ ባህርያት አሏቸው። በተለይ ህብር ለጠቅላላ ዜግነታችን መገለጫ ስለሆነችና በተለይም “ብሄር ብሄረ ሰቦች” በሚል መርሆ በተበታተንበት ወቅት ብንመለከታት ያባቶቻችንን ጥበብ የበለጠ ለመረዳት ትረዳን ይሆናል ብየ ስላሰብኩ ከዚህ በታች እንመልከታት።

ሠ. ኅብር

ኢትዮጵያዊ ሁሉ እርስ በርሱ ኅብሬ ነህ መባባሉን ስለሚያፈርስበት፤ ያስኳላ ተማሪ ብሄር ብሄረሰቦች የሚለውን ከፋፋይ እኩይ ዘዴ ኢትዮጵያዊት ቅኔያችን አትቀበለውም። አባቶቻችን ኢትዮጵያዊት ኅብርነታችንን በብዙ ምሳሌዎች ይገልጿታል። ከብዙ ምሳሌዎች አንዷ ነቢዩ ኤርምያስ “ነብር ዝጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን ይቀይራልን?” (ኤርምያስ 13፡23) ብሎ የተናገራትን ናት።

 

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ባንድ ነብር ሰውነት ላይ ያሉትን ነጠብጣቦች ይወክላሉ። በቦታ የተለያዩ ነጠብጣቦችን የተሸከመው የነብሩ አንድ አካል፤ በወረዳና

 

ባውራጅ ተለያይተው ያሉት ጎሳዎችን የተሸከመችውን አንዲት ኢትዮጵያ ይወክላል። ህብሮች ኅብርነታቸውን ሳይቀይሩ ሳይጠፋፉ የነብሩን አካል እያደመቁ እንደሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ባህርያቸውን ሳይቀይሩ ባንዲት ኢትዮጵያ ተባብረው ይኖራሉ።

 

ነቢዩ ኤርምያስ ኢትዮጵያዊ ስነ ሕሊናችንን ከማይቀየረው ከነብር ዝጉርጉነት ጋራ አነጻጽሮ በጥያቄ የገለጸው፤ እራሱ ኤርምያስ ነጻነቱን ተገፎ ሰባዊ ክብሩን ተዘርፎ እመቀ እመቃት በወደቀበት ወቅት፤ አቤሜሌክ የሚባል ሰው በገመድ ጎትቶ ከወደቀበት ጉርጓድ አውጥቶታል። ከተወረረበት ጉድጔድ ተጎትቶ የወጣባትን ገመድ መምህሮቻችን ለወርቃማዋ አርበኛነታች መግለጫ ህብር እያደረጉ አስተምረውናል።

 

አቤሜሌክ ኤርምያስን ከገባበት ጉድጓድ ያወጣባትን ገመድ በአርበኝነ ስሜት፤ አቤሜሌክ እንዳርበኛ፤ እያደረግን ስነ ልቡናችን እንቀኝበታለን። አቤሜሌክ በአርበኛነቱ “በእኔ ስለታመንክ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም። አድንሀለሁ። ነፍስህም እንደምርኮ ትሆናለች እንጅ አትወድቅም”(38፡13) የሚል ጸጋና በረከት እንደተጎናጸፈባት፤ ኢትዮጵያውንም በፈጣሪያቸውና በረሳቸው ጽኑ እምነት ላይ የተመሰረተችው አርበኛነታቸው በጠላት ላይ ድል የመቀዳጀት ጸጋና በረከት ይጎናጸፉባትል እያልን እንድንቀኝ አስተምረውናል። በቅኔ ትምህርታችን የኢትዮጵያዊነትን ስነ ልቡና ከምንቃኝባቸው አንዷና ዋናዋ የዓባይ ወንዛችን ናትና በዚህ አጋጣሚ ዓባይንም ሳንዳስሳት ማለፍ ኢትዮጵያዊነታችን አትፈቅድም።

 

ረ. ዓባይ

 

በመስተጻምራቱ አማካይነት ኢትዮጵያን በደመ ፍሳችን እንድትቀረጽ ያደረገች

ያፋችን መፍቻ ቅኔያችን ኮፌዳችን እንደነበረች ተመልከተን ነበር። አሁን ደግሞ ከኮፌዳችን

ጋራ እያነጻጸርን የኢትዮጵያዊነታችን የጥንቅር ቅኔ እንደሆነች ዓባይን እንመለከታለን።

ዓባይ በምድረ ኢትዮጵያ አካል የሚፈሱትን የአፍላጋት ክምችት (ገባር ወንዞች) እየሰበሰበች

በመያዟ፤ ከየመንደሩ የምንሰበስበውን ውጥንቅጥ ሰብስባ ከምትይዘው ከኮፌዳችን ጋራ

እያነጻጸርን ከላይ የተገለጹትን ሰምናወርቅ፤ ሰርዝና ህብር ቅኔ እንቀኝባታለን።

 

በሌላ በኩል ቅድስት ኢትዮጵያ አገራችን፤ እናትነትን ካገርነት ጋራ አጣምራ የያዘች ለኛ ለዜጎቿ ወላጅ እናታችን፤ ለግብጾች የእንጀራ እናታቸው መሆኗን በጥልቅ አንክሮ እናይባታለን። ዓባይ ከግሼ እየመነጨች በኢትዮጵያ አካል የሚፈሱትን የአፍላጋት ክምችት (ገባር ወንዞች) ሰብስባ በእናት ኢትዮጵያችን አካል የምትፈስ ደም መሆኗንሞ በተደሞ እንቀኝባታለን።

ከኢትዮጵያ ጡት ልጆቿ ከግብጻውያንና ጋራ የምንጋራው መጽሐፈ ቅዳሴያችን

”ወእንዘ በርስእ ሀለወት፡ ኩሎ ተሐድስ፡ ወበበ ትውልድ ምስለ ነፍሰ ጻድቃን ትትፋለስ“

እንዲል፦ ዓባይ ጥንታዊት ስትሆን የማታረጅ የስነ ልቡናችንን ቅኔ ሰንቃ በየትውልዱ አካል

በመፍሰስ በአርበኝነት ወኔና መንፈስ እያደሰችን እንደምትኖር ተምረንባት ነበር።

ለምለሚቷ ኢትዮጵያ እናታችን ከማህጸኗ የፈለቁትን እንደ አጼ ቴወድሮስ፤ እንደ በላይ ዘለቀ

 

የመሳሰሉትን ጀግኖች፤ እንደነ መላከብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የመሳሰሉት ሊቃውንት

እያጠጣች ያሳደገችበትን ከሰውነቷ የሚፈልቀውን ውሀ፤ በተፈጥሮ እጓለ ማውታነታቸው የነጻነት ድርቅ ያጠቃቸውን ሱዳናውያንንም ግብጻውያንንም ጠጥተው እንዲረኩ “ኑ ! የነጻነትን ውሀ ከኔ እየጠጣችሁ እርኩ” እያለች ስትጋብዝ በኖረችው እናትነቷ የምትከበር ናት።

 

ስለዚህ እናንት ልሂቃን ነን የምትሉ ወገኖች ሆይ! “ብሄር ብሄረ ሰቦች” በሚል ፈጠራ የወጣቱን ጭንቅላት እያዞራችሁ፤ እርስ በርሱ እንዲጠፋፋና ኢትዮጵያንም እንዲበታትናት የማድረግ ደባችሁን አቁሙ! ይልቅስ በዚያ ፋንታ አባቶች እንደሙጫ የሰሩባቸውን መስተጻምራት፤ በኮፌዳችንና በዓባይ ወንዛችን በተመሰረተችው ቅኔ የተገለጸችውን ኢትዮጵያን፡ ወጣቶች እንዲገነዘቧት በሚገባቸው ቋንቋ ለማስተማር ብትጥሩ፤ አገራችንን ቅድስት ኢትዮጵያን በባቶቻችን ዘመን ከነበራት ምሳሌነቷ እጅግ በተሻለና በላቀ መፍለቅለቅ የምሥራቋ ኮከበጽባህ ማድረግ ትችላላችሁ። ኢትዮጵያዊትን ቅኔ በሚቃረን እኩይ መርኌችሁ ብትቀጥሉ ግን ልታጠፏት ታጥቃችሁ ከተሰለፋችሁባት ኢትዮጵያ በፊት እራሳችሁ ትጠፋላችሁ።

 

ተባርዮን የማያስቀር ያባቶቻችን አምላክ፤ ዓይነ ልቡናችሁን ይክፈትላችሁ!

 

 

1 COMMENT

  1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአብዛኛው ጻጻሳት ካህናት ለፈቃደ ስጋ ተገዝተው እምነትን እንደ አይሁድ ካህናት ስርአትና ልምድ አድርገው በደረታቸው በተሰደረው አብረቅራቂ መስቀል በእጃቸው ይዘው እጅግ በአማረ ልብሰ ተክህኖት አጊጠው ምዕመኑን በዘነጉበትና ያለ ይሉንታም ለመንግስት በፍርሃት በአደሩበት ሰዕት እግዚአብሔር ጨርሶ እልተወንምና እንደ እነውነተኛ የተመረጡ አራት አይና እንደ ቀሲስ አስተርአይ የመሰሉ መልዕተኛ እውነትን ግልጥ አድርገው የሚያስተምሩ ሰጥቶናልና የተመሰገነ ይሁን!በዘመኑ ሁሉ አምላክ የፈጠረውን ህዝብ ብርሃንን ከጨለማ እየለየ የምያስተምር መልዕክተኛ ይሰጣል!ግን ምንያህል አንበብበን ወደ አዕምሮአችን አዝልቀን እንለወጥ ይሆን!እናንተስ በቤተክርስትያን መስተዳድር ቁንጮ ላይ ተቀምጣችሁ አምጡ እንጅ መስጠትን እጃችሁ ያለመደ በአይሁድ ስርአትና ልማድ ተተብታችሁ እራሳችሁን ብመስቀሉ ለውብት የዋላችሁ ክንቱዎች የክርስቶስ ፍርድ ወደ እናንተም የሚመጣ እድያውም በስሙ የነገዳችሁ ከበዳዮች ከግፈኞች ተባብሪችሁ እውነትን በሀሰት ለውጣችሁ ለምታስተምሩ ደላዮች እንዲሁም በደልን እያያችሁ ለስጋችሁ እድራችሁ ዝም ያላችሁ ጻጻሳት ካህናት ድያቆና አስተማሪዎች ከእኝህ መልዕክትኛ ምን ተማራችሁ?አይናችሁን ግለጡ!አንደበታችሁ ለእውነት ይገለጥ አእምሮአችሁ እንደ ሙሴ በደልን ይጠየፍ!እኔስ በእናተ ባፍርምና ብርቃችሁም ዝም ብሎ ያልተወን አምላክ እንደ እኚህ አባት እያስነሳ ይናገራል!ይወቅሰናልም!!ፍርድም አለ!ደሀን ማሰብ ክምታገኙትም መስጠትን ኣእውቁ!ጃንጥላ እየዘቀዘቁ ገንዝብንም መሰብሰብም ተጠየፉ!ይብቃችሁ!ከእግዲህ ለራሳችሁ ስትሉ ንቁ!ተለወጡ!ሳዖልን የቀየረ እምላክን እናንተንም ይለውጥ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.