አገር ትዳን ከተባለ ኢህአዴግ የተባለ የወንብድና ቡድን ከሥሩ መነቀል አለበት – ሰርፀ ደስታ

የኢትዮጵያን ጉዳዮች በደንብ ላስተዋለ ኢትዮጵያ እንደ አገር እሰካሁን መቆየቷ ራሱ አስገራሚ ይሆንብናል፡፡ ባለፈው ሜይቴክ የተባለ የዘረፋ ድርጅት ፈጸመው የተባለውን ሙስና ሲካበድ አይተን ብዙዎቻችን ገርሞናል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቻችን ብዙም አልደነቀን፡፡ እውነታው ከሜይቴክ በሚከፋ ብዙ ቦታዎች አገር በመንግስትነት በተደራጀ ቡድን እየተዘረፈች ብቻም ሳይሆን እየተሟጠጠች እንደሆነ እናያለንና፡፡ ይህን አስመልክቶ አቶ ሱሌመን ደደፎ በግልጽ ነግረውናል፡፡ ሌላው ጋር ያለውን ብትሰሙ ሜይቴክ ማረን ትላላችሁ ነበር ያሉት፡፡

የመንግስትን መዋቅር ሙሉ በሙሉ የያዘው ኢህአዴግ የተባለ የዘረፋ ቡድን ኢትዮጵያ በሜጋ ፕሮጄክቶች ሥም በኢትዮጵያ ሥም በብድር መልክ ገንዘብ ከየአገራቱ ተበድሮ ገንዘቡን ለአባላቱ አከፋፍሏል፡፡ የስኳር ፕሮጄክቶች በሚል የጠፋውን ገንዘብ ለሰማ ሜይቴክ ዘረፈው የተባለውን ይቺ በዘረፋ አታስጠይቅም ይላል፡፡

ብዙ ሰው እየገባው አደለም፡፡ ችግር አለ፡፡ ከእኛ ይልቅ ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያን ጉዳይ ያሳሰባቸው ይመስላል፡፡ 100 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት አገር እንዲህ በወንበዴዎች መዋቅር ሥር ከዚህ በኋላ ከቀጠለች አደጋ ላይ እንደሆነች የተረዱት ይመስላል፡፡ እኛ ግን አንኳን ሊገባን ቀርቶ ያሳሰብን እንኳን አይመስልም፡፡ እንደኖህ ዘመን ሰዎች አገር እየጠፋች በዘረፋና ውንብድና እንደልብ እያናጠሩ የሚፈነጩትን እያደነቅን አለን፡፡ የሚገርመው በተቃዋሚ ሥም የፖለቲካ ቡድን ነን የሚሉት ሁሉ ሕልምና አላማቸው ይሄ እንደልብ የሚዘረፈውን ገንዘብ የመያዝ ወይም ከቅንጥብጣቢው መቋደስ እንጂ የአገርና የሕዝብ ቁጭትና አላማ የላቸውም፡፡

ዛሬ የምታዩት የፖለቲካ ቁማር አገርን ከመቀየር አንጻር ሳይሆን ከዘረፋው ለመሳተፍ ወረፋ የያዘ ነው፡፡ አገር እየወደመች ዝም በሉ ይሉናል፡፡ የእነ ብርሀኑ ነጋን ለአብይ ሰባኪ መሆንን ሳይ እነዚያ ሁለት ሁለቱ ጓደኛሞች ትርክት ይታሰበኝና ግን አልመጥነው ይለኛል፡፡ ሁለት ጓደኛሞች መንገድ ሲሄዱ ውለው ሲመሽ ደክሟቸው ሜዳ ይተኛሉ፡፡ አያ ጅቦ ሆዬ ይመጣና የአንዱን እግር መቆርጠም ይጀምራል፡፡ የጓደኛው እግር ሲቆረጠም የሰማው ሌላው ምንድነው የሚነቋቋው ብሎ ጓደኛውን ሲጠይቀው ዝም በል ዝም በል ጅብ የእኔን አገር እየበላ ነው እንዳይሰማን ይለዋል፡፡ ይሄን የተረዳው ጓደኛው እንዴ አንትን ጨርሶ ወደኔ መምጣቱ አደለ እንዴ ይልና ከመኝታው ሲነሳ ጅቡ ይሸሻል፡፡ እነ ብርሀኑ እያሉን ያሉት ዝምበሉ እንዲህ ነው፡፡ በእርግጥ እየተበላ ያለው የእነ ብርሀኑ አግር ሳይሆን የእኛ (ኢትዮጵያውያን) ነው፡፡ ዝም በሉ ይሉናል፡፡ እያለቅን፡፡

በአዴን በለው ኦፒዲ ሌላ አሁን መዋቅሩን የያዘው የዘረፋ ቡድንን ከላያችን ላይ እስከወዲያኛው ከአልተወገደ ጤንነት የለም፡፡ እነዚህ ሰዎች እድሜ ልካቸውን ማስመሰልን የተካኑ ስለሆነ በማስመሰል ይሄው ሕዝቡን አሁንም ያደናግሩታል፡፡  በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እንደፈለጋቸው ይፈነጩበታል፡፡ በራሳችን ገንዘብ እኛን ያታልሉናል፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለ2012 ለተማሪዎች ዩኒፎረም፣ ደብተር ምናምን ይቀርባል የሚል ወሬን ሰዎች በስፋት ሲያሰራጩት አየሁ፡፡ እንግዲህ አይደረግም አይባልም፡፡ የሚገርመኝ ግን ብዙዎች ይሄን ጉዳይ የሚያሰራጩት በእንዲህ ያለ የውንብድና እቅድ ከመጠን በላይ እያደነቁና መንግስት ማለት እንዲህ ነው አይነት እያሉ ነው፡፡ አዝናለሁ፡፡ መንግስት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተሟጦ ስለጠፋብን አሁን አይገባንም፡፡ ለመሆኑ ይሄ ነገር እውነት ከሆነ የአዲስ አበባው ከንቲባ ከኪሳቸው ነው እንዴ የሚለግሱት? መንግሰት እንደመንግስት ትምህርት ቤት ይሰራል፣ መብራት ለደቂቃም እንዳይጠፋ ያሟላል፣ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ያሟላል፡፡ ደብተርና ዩኒፎረም አድላለሁ? በማን ገንዘብ ገዝቶ? እያንዳንዱ በመንግስት ያለ ገንዘብ የሁሉም ዜጋ ነው፡፡ ይሄ ደብተርና ዩኒፎረም ታዲያ ገጠር ከከተማ ሳይል ለሁሉም ለማድረስ ይሆን? እንግዲህ አሁን ከማየው ይሄን አይነት የወሮባላ አይነት እቅድ ሰዎች እያደነቁት ናቸው፡፡ የማንን ገንዘብ ነው እንትና የሚወስንበት? ችግሩ እንዳናስብ ስላደነዘዙን ከአልሆነ በቀር እንዴት ይሄ ምን ማለት እንደሆነ አይገባንም፡፡ ልብ በሉ መንግስት እንደመንግስት በጣም መረዳት አለባቸው የሚለውን ዜጎቹን በልዩ መልክ እቅድ አውጥቶ ማገዝ ይችላል፡፡ ትምህርትንም ለማበረታት ከሆነ ከትምህርት ጋር የተያያዙ ክፍያዎችን በነጻ ወይም በቅናሽ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲዎችን ከክፍያ ነጻ ማድረግ፡፡ የመንግስት እቅዶች ግን በቀዳሚነት ሰዎች የተረጅነት ስሜት እንዲያዳብሩና በቀጥታ በሚሰጣቸው ሳይሆን እንደዜጋ ይገባኛል ብለው በሚያስቡበት ነው መሆን ያለበት፡፡ ያም ሆነ ይህ ይሄ አሁን አዲስ አበባ ላይ ይታደላል የተባለው እውነት ከሆነ ዩኒፎረምና ደብተር እቅድ የወንበዴዎች ማደንዘዣ እንጂ የመንግስት አሰራር አደለም፡፡ አይደረግም አይባልም ደግሞ፡፡ ባለፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለእርዳታ ገንዘብ ሲያድል አይተናል፡፡ የመንግስት የሆነው ባንክ ገንዘቡን እንደፈለገው እንዲበትን ሥራአስኪያጁ ይወስናል፡፡ ችግር የለውም፡፡ አሁንም ከንቲባው እንደፈለገ አውጥቶ ሕዝብን ገንዘብ ይበትናል አይደረግም አይባልም፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉና አገርን እንደአገር ማስቀጠል የሚችሉ ፕሮጄክቶች ከነጭርሱም የተዘነጉ እየመሰለ ነው፡፡ አሁን የሚታየው የኃይል መቋረጥ የግድቦች ውሀ አለመያዝ ምክነያት ቢሰጠውም መሠረታዊ ችግሩ ግን ግድቦቹ በቂ ውሀ እንዲይዙ ታቅዶ ስላልተሰራ የመመረተውን ኃይል በበቂ ማጠራቀም አለመቻል ነው፡፡ ግድቦቹ በቂ የሆነ ክትትል ከአልተደረገላቸውና በወቅቱ መያዝ ያለባቸውን ውሃ ማጠራቀም ከአልቻሉ አሁን እጥረት ቢኖር ታዲያ ምን ይገርማል? ይሄ ብቻም አደለም ግድቦቹ በክትትል ማጣት ምክነያት እስከወዲያኛውም ከአገርልግሎት ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰብበት፡፡ አሁን ያለው አያያዝ ይሄ ነውና፡፡ ትኩረት ይሰጥልናል በሚሉትና በቴሌቪዥን ሰዎችን ያማለልልናል በሚሉት በሚሉት ሥራ ላይ ነው እንጂ አሁን የተያዘው አገርን በማሰብ አደለም፡፡ የቀረችውን እያሟጠጡ እናያለን፡፡

አገር እንድትተርፍ ብዙ ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ብዙ መሥዋዕትነትም የከፈልን ብዙዎች አለን፡፡ ዛሬም ቢሆን ግን ስለአገር መታሰብ የሚገባውን ለማሳሰብ ነው ሕዝብ ሁሉ እንዲረዳው ያስፈልጋል፡፡ አገር በወንበዴዎች እያለቀች ነው፡፡ ፕሮጄክቶች የሉም፡፡ በአገር ሥም ገንዘብ ከሌሎች ተቀበለው ገንዘቡን ሙልጭ አድርገው ወስደው ይሄው አገር ባለእዳ ሆና ቀርታለች፡፡ በፕሮጄክቶቹ ሥም አሁንም ያላትን እያሟጠጡት ነው፡፡

አብይ አህመድ ተስፋ ተደርጎበት ብዙ ታስቦ ነበር፡፡ ግን ያላስተዋልነው ነገር ኢሕዴግ በተባለ የውንብድና ተቋም ውስጥ እድሜውን ሁሉ እንደሰራና እንዴት ማስመሰልና ሕዝብን ማታለል እንደሚቻል ሲሰለጥን የኖረ ነው፡፡ ፊት ለፊት ያለምንም ሀፍረት ዋሽቶ ማሳመን የኢህአዴግ የተባለው የውንብድና ቡድን  መርኅ ነው፡፡ ዛሬ አብይን ብዙ ሰው እያደነቀ ነው፡፡ ከአብይ ሌላ ማንም ሰው የለም አገር መምራት የሚችል የሚሉት ተራ ሰዎች ብቻም ሳይሆኑ ምሁር ነን የሚሉትና ፖለቲካ ቡድን መሪ ነን የሚሉትን ጨምሮ ነው፡፡  መለስም እንዲሁ ሲባልለት ነበር፡፡ ችግሩ አብይም ሆነ መለስ ስልታቸው ከእነሱ መጥቆ ያለን ሰው ከሥራቸው በማራቅ ራሳቸውና ማግዘፍ ስለሆነ ሰው ቢያደንቃቸው አይገርምም፡፡  አብይ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ላይ በሚኒስቴርነት የተሸሙትን እናስተውል፡፡ ስንታቸው ናቸው እስኪ እንደሚኒስቴር ራሱን መምራት የሚችል? አብዛኛው ኢህአዴግ የተባለው ቡድን መዋቅር ውስጥ ያሉ ትምህርት አንኳን በመደበኛው መስመር አልፈው አሁን ያሉበት የደረሱ አደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ብዙ ምጡቅ ዜጎች አሏት፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳን ቅድሚያ ሊታሰብ የሚገባው አገርንና ሕዝብን እየዘረፈ አሁንም የቀጠለውን ኢህአዴግ የተባለ የውንብድና ተቋም ከመሠረቱ ማፍረስና አገርን በኢትዮጵያውያን እጅ ማስገባት ነው፡፡

ከገባችሁ እውነቱ ይሄ ነው፡፡ የሚታየው እውነት እንደመንግስት እየተሰራ አደለም፡፡ በእርግጥ የመንግስት መዋቅር የፈረሰው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተበትኖ በወንበዴዎች የተተካ ጊዜ ነው፡፡ አልበሽር ከ30 ኣመት በላይ የመራት ሱዳን የመንግስት መዋቅር ስለተረፈ መከላከያው ለጊዜወም ቢሆን የመንግስቱን ሥልጣን ይዞ አገር እየመራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይሄን የሚመስል መዋቅር እንኳን የላትም፡፡ ዛሬ መከላከያ የተባለው የኢሕዴግ የቡድኑ የራሱ እንጂ የኢትዮጵያ አደለም፡፡ የደርግ እየተባለ የሚጠራው የመከላከያ ተቋም በኃይለስላሴም የነበረው ራሱ ነበር፡፡ የአገር ተቋም ሲሆን ከቡድን ቡድን ሳይሆን አገርንና ሕዝብን በመጠበቅ ይቀጥላል፡፡ የግብፁ መከላከያ አገሪቱን ብዙ ጊዜ ከጥፋት እያዳነ ለመሪዎች ሲያስረክብ አይተናል፡፡ ከሙባረክ፣ ሙርሲ፣ ከሙርሲ አልሲሲ ሲቀጥሉ መከላከያው ግን የግብጽ በመሆኑ አገርንም ታድጎ እሱም ቀጥሏል፡፡ እንኳን ሙርስ ሙባረክም የራሱ ሰራዊት አልነበረውም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ያው ሰራዊት ግን የኢሕዴግ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሕዝብ የሚያውቀው በኢሕዴግነቱ እንጂ በአገር መከላከያነቱ አደለም፡፡ በዋናነት የሚመራውም በኢሕዴግ አባል በሆኑ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በምርጫ ቢሸነፍ እንኳን አሁን ያለው ሰራዊቱን ይጠቀማል፡፡  ሠራዊቱን በሥነልቦናም በብቃትም የአገርና ሕዝብ እንዲሆን እስካልተደራጀ ድረስ ችግር ነው፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ ብዙ በጎ አሳቢ እንዳሉ ዘንግቼው አደለም፡፡ የኔ ችግር አደረጃጀቱ ላይ ነው፡፡ በሥነልቦና እኔ አገርንና ሕዝብን መጠበቅ ነው ዓላማዬ እንጂ የፓርቲ አገልጋይ አደለሁም ብሎ ማሰብን፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከክፉ ይጠብቅ! አሜን

ሰርፀ ደስታ

2 COMMENTS

  1. በጣም ድንቅ አስተያዬት ነው፡፡ ኢሀዲግ የሚባል መርገምት የአጋንቶች ስብስብ እስካልጠፋ ድረስ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ውስጥ ውስጡን ምስጥ እንደጨረሰው እንጨት አንድ ቀን ተገንድሳ መውደቋ አይቀርም፡፡ እነዚህ ሞራል የሚባል ጠብታ የሌላቸው ወሮ በሎች ከብድር እና እርዳታ ገንዘብ ጀምሮ የዚህን ደሃ ምስኪን ህዝብ ኪስና መሬት ሙልጭ አድርገው ዘርፈዋል፡፡ እንደ ቀበሮዋ ተርት ምንትስ ይወድቃል ብል ስትከተል ዋለች እንደሚባው የግም 7ባቶቹ አቶ ብርሁኑ ነጋና አንዳረጋቸው ጽጌ ዝም በሉ ኢሀዴግ በሚሰራው ድልድይ ወደ ዲሞክራሲ እንሻገራል ይሉናል፡፡ ምንም ከስተታቸው የማይመሩ በሽተኞች፡፡ ለማንኛውም እርማቸውን ያውጡ ከዚህ በኋላ ምንም እንደ አብረሃም በግ የሚታልል እንደይመስላቸው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.