ቴዲ አፍሮ በአፍሪካ ሕብረት ሊሸለም ነው

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ለወጣት አፍሪካውያን አርአያ በመሆን ላበረከተው አሰተዋኦ በአፍሪካ ሕብረት የዋሽንግተን ዲሲ ጽሕፈት ቤት የዕውቅና ሽልማት ሊበረከትለት ነው።

በሕብረቱ የዋሽንግተን ዲሲ ጽሕፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ቴዲ አፍሮ ከኢትዮጵያም አልፎ ለመላ አፍሪካ ወጣቶች በአርዓያነት የሚጠቀስ አርቲስት መሆኑን አመላክቷል።

በመጪው ሐምሌ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚካሄደው የአፍሪካ ሩጫ ጋር ተያይዞ በሚሰናዳው ዝግጅት ላይ ሽልማቱ እንደሚበረከትለት ታውቋል።

በዋሽንግተን የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ ዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ ሽልማቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ከኢትዮጵያም አልፎ ለመላ አፍሪካ ወጣቶች አርዓያ ነው።
አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን በሙዚቃው ዘርፍ ተግቶ በመሥራት ለአፍሪካ ወጣቶች ያበረከተዉ አስተዋፆ የጎላ በመሆኑ የሚሰጠው ዕዉቅና ትርጉም ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

ከመድረክ ሥራዎቹ ባሻገር የበጎ አድራጎት ክንውኖቹ የአፍሪካ ሕብረት ዝግጅቶቹን ተጠቅሞ ለማጉላትና የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ከተነሳባቸዉ ዓላማዎች መካከል መሆናቸውንም ዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ ጠቁመዋል።

የታላቁ የአፍሪካ ሩጫ ውድድር ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጋሻው አበዛ ደግሞ ለአርቲስቱ የሚበረከተው ሽልማት ወቅታዊ፣ ምክንያታዊና ለኢትዮጵያውያንም አኩሪ መሆኑን ገልፀዋል።

ለአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን የሚሰጠው ዕውቅና ካበረከተው ተምሳሌታዊ ሚና ባሻገር ለአፍሪካ አህጉርም ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

የሩጫ ውድድሩ የተዘጋጀው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በሰሜን አሜሪካ ሦስት ከተሞች በነበራቸው ጉብኝት በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ ኢትዮጵያን ጋር በነበራቸው ውይይት ቀኑ የኢትዮጵያ ቀን ሆኖ እንዲከበር የከተማው ከንቲባ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው።

በመጪው ሃምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም “ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ” በሚል የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

ውድድሩ በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ ኖቫ ኮኔክሽንስ በሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅትና በዋሽንግተን ዲሲ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።

የሩጫ ውድድሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ከተጋባዥ ታዋቂ የአፍሪካ አትሌቶች ጋር የሚሳተፉበት መሆኑንም ከአዘጋጆቹ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ታላቅ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ በየዓመቱ የሚካሄድ ብዙኃኑን የሚያሳትፍ የጎዳና ላይ ሩጫ መሆኑ ይታወቃል።

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2011ዓ.ም (አብመድ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.