ምግባሩ ከበደ (ነፍሱን ይማረውና) ለምን ተገደለ? (አሁንገና ዓለማየሁ)

ምግባሩ ከበደ ለምን ተገደለ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ምግባሩ ከበደ ማን ነበረ?ምን አቋም ነበረው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል በሚል የማውቃትን ትንሿን ለማካፈል እሞክራለሁ።

አፍሪካ ውስጥ ራዕይ ያላቸው፣ ሐቀኛ የፖለቲካ ሰዎችና የሕዝብ አስተዳደሪዎች በረቀቀና በተቀነባበረ መልኩ ብዙ ጊዜም አለም አቀፍ እጆች ከበስተጀርባ እየመሩት የተገደሉበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

የእንዲህ ዓይነት ሰዎች ግድያ ትኩረት የሚደረግበትም ምክንያት ሐቀኛና ንጹህ ስብእናቸው ላይ ተመስርተው ወገናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚችሉ በወገናቸውም ጥቅም ላይ ለመደራደር ፍላጎት የሌላቸው ልበ ሙሉዎች በመሆናቸው ነው። በንጽህናቸው ላይ ተመሥርተው ያለፍርሃት ያለክፋትም የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአደራ፣ የተቀበሉትንም ሥራ በትጋት ይወጣሉ። በቀላሉ ተተኪ አይገኝናለቸውም በሚል ትክክለኛ ስሌት ባእዳን ወይም ተላላኪዎቻቸው ያንድን ሕዝብ ጥቅም ለመጋፋት በሚያደርጉት ዘመቻ ውስጥ በቅድሚያ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ለማስወገድ ትኩረት ይሰጣሉ።

ሰሞኑን በግፍ ስለተገደሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖች የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ፣ አንዳቸውንም በአካል የማላውቃቸውን ሌሎችን ለጊዜው ሳልጠቅስ በሕይወቴ አንድ ጊዜ ብቻ ያየሁትን እና የማይረሳ ትውስታ የተወብኝን አቶ ምግባሩን ለማንሳት እፈልጋለሁ። ዓላማዬም ስለስብእናው የማውቀውን እጅግ ጥቂት በመመስከር ከኅሊና ፍርድ ነጻ ለመሆን ነው። ሌሎች ይበልጥ የሚያውቁት አስፍተውና አስፋፍተው የዚህን ምርጥ ኢትዮጵያዊ ወንድም ታሪክ ቢጽፉለት እጅግ ደስ ይለኛል። የሌሎቹን ሟች ወገኖቻችን ታሪክም እንዲሁ።

እዚህ ላይ ለአንባቢው የሚከተለውን አስቀድሜ መግለጽ እወዳለሁ። በሀገራችን የአምባገነኑን የደርግ ውድቀት ተከትሎ ኤርትራን ላስገነጠለውና ኢትዮጵያን በጎሳ የሚከፋፍል ሥርዓት ለዘረጋው የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሥርዓትም ሆነ ለካድሬዎቹ ምንም አክብሮት ያልነበረኝ መሆኑን ነው። እርግጥ ጥላቻም አልነበረኝም። እነዚህ ወገኖች መሐይም፣ ሆድ አደር፣ ወይም ስሑት የባእዳን ተላላኪዎች መሆናቸውን ስለምረዳ እና እምነቴም ስለማይፈቅድልኝ ማለት ነው። ይሄን ካልኩ አቶ ምግባሩን ያገኘሁበትንና ለዚህ ምስክርነት ያበቃኝን አጋጣሚ ልግለጽ።

በቀድሞው አጠራር በጎጃም ክፍለ ሀገር በምስራቅ ጎጃም (ዛሬ አማራ ክልል) በምትገኘው የደብረ ወርቅ ጥንታዊ ቤተክርስትያን ውስጥ አንድ ታላቅ ሥራ ለመሥራት መሠረት እየተጣለ ነበር። በደብሩ ያለውን ገናና የአብነት ትምህርት ቤት ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማጣመር ቤተክርስትያንን የሚመራ ትውልድ ለማሰልጠን የሚያስችል ተቋም ለመገንባት በቤተክህነት የስብሰባና የሲምፖዚየም መርሐ ግብር ተይዞ ነበር። ለጊዜው በእለቱ የመዘገብኩበት ማስታወሻ አጠገቤ ስለሌለ ዝግጅቱን ቤተ ክህነት ይሁን ለየት ያለ ማህበር ይሁን ወይንስ ማህበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው እርግጠኛ አይደለሁም። ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ነፍሳቸውን ይማረውና ጊዜው የፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የሥልጣነ ክህነት ዘመን ነበርና እሳቸውም በቦታው ተገኝነተው ነበር። በዚህ ዕለት በመጀመሪያ ያስደነቀኝ አጋጣሚ አቡነ ጳውሎስ ያደረጉት ንግግር ነበር። በቤተክርስትያን ውስጥ ሕወሐት/ኢሕአዴግ እጁን አስገብቶ መፈንቅለ መንበር አካሄዶ የሾማቸውና በውጭም በሀገር ውስጥም ቤተክርስያንን በጎሳና በጎጥ የከፋፈሉ ስለነበሩ እንደ ካድሬ እንጂ እንደ መንፈሳዊ አባት ሳላያቸው በመኖሬ፣ ካድሬያዊ እንጂ መንፈሳዊና ሀገራዊ ቁም ነገር ያለው ነገር ጠብቄባቸው አላውቅም ነበር። ይህንን ስል እኔ ቅዱስ ነኝ ለማለት አይደለም። በተቃራኒው። በጥምቀትና በመስቀል በዓላት ከመንፈሳዊ ሥልጣናቸው የማይጠበቅ ንግግር አንድ ሁለት ጊዜ ሲናገሩ ሰምቼ ነበር። የሆነ ሆኖ እሳቸው ንግግር ሲጀምሩ ውጭ ቆይቼ ሲጨርሱ ብመለስ እወድ ነበር። በዚህ ዕለት ግን ታዳጊ ልጆች ይዤ ሄጄ ስለነበር መጥፎ ምሳሌ ላለመሆን፣ የነርሱንም አእምሮ ላለመመረዝ ተቀምጨ ማዳመጡን መረጥኩ።

ንግግራቸውን ስሰማ እጅግ በጣም ነበር የተገረምኩት። ፓትርያርኩ ያደረጉት ንግግር ከአንድ መነኩሴ (መነኮሰ = ሞተ) በትክክል የሚጠበቅ፣ ከአንድ አረጋዊ የሚጠበቅ፣ ከአንድ አባት የሚጠበቅ፣ ለትውልድ አደራ የሚያስገነዝብ ቁም ነገር አዘል ነበር። አባት አባት እንጂ ካድሬ ካድሬ የማይሸት መልእክት። እሞታለሁ የሚል እንጂ እኖር ባይ የማይናገረው ትሁትና

አደራ የተሞላበት ንግግር። ጆሮዬን እንደተጠራጠርኩ ንግግሩ አባታዊና መንፈሳዊ ይዘቱን ሳይለቅ ተጠናቀቀ። በራሴ እጅግ አፈርኩ። በጥላቻ ታውሬ ምንም ፍሬ እንደሌላቸው ምርትና ገለባቸውን ባንድ ላይ ኮንኜ ነው የኖርኩት ብዬ አዘንኩ። ያመለጠኝ ዘመን ጸጸተኝ። መልሼ ደግሞ መነኩሴ ወይም ሐኪም ቀንህ ደርሷል ብሏቸው ይሆናል እንዲህ የተናገሩት ብዬ ራሴን ለማታለል ሞከርኩ። የዚህን ዕለት ንግግራቸውን አንባቢውም ሰምቶ መልእክቴን ያምን ዘንድ በእለቱ ከቤተክህነት አንድ ቀጭን መነኩሴ ዝግጅቱን በፕሮፌሽናል ካሜራ ስለቀረጹት የሚችሉ ሰዎች ቀረጻውን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉት በዚሁ አጋጣሚ እማጸናለሁ። ይህ ከሆነ በዚያው ከዚህ በታች ስለ አቶ ምግባሩ የምናገረውንም ነገር ማረጋጥ ያስችላል።

ፓትርያርኩ ንግግር ካደረጉ በኋላ የጎጃም ይሁን የምሥራቅ ጎጃም ወይም የአማራ ክልል – ብቻ ደብረወርቅ ቤተክርስትያን ያለችበትን ሀገረ ስብከት የሚያስተዳድሩት ጳጳስ – ወደ መድረኩ ይጋበዛሉ። ካልተሳሳትኩ ስማቸው አቡነ ዮሴፍ መሰለኝ። እርግጠኛ አይደለሁም። እኒህ ሊቀ ጳጳሳት መድረኩ ላይ ቆመው ንግግር ሊያደርጉ ሲዘጋጁ አንድ ሱፍ የለበሰ ሎጋ ወጣት በዝግታ ወደ አዳራሹ ይገባል። እርሳቸውም ከተፈቀደልኝ የኔ ንግግር ይቅርብኝና ይህ አሁን ወደ አዳራሹ የገባው ወጣት በኔ ፋንታ ስለ ፕሮጄክቱም ሆነ ስለ መንግሥትና ሕዝብ ድርሻ መልእክት ያስተላልፍ ይላሉ። ወጣቱ በመርሐ ግብሩ የተካተተ አልነበረም የመጣውም ባጋጣሚ ነበር። በመቀጠልም ወጣቱ ይህ ፕሮጄክት በሚንቀሳቀስበት በምሥራቅ ጎጃም የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊ መሆኑን ያስረዳሉ። በሥራቸው እጅግ ቀና ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚያደርግላቸውም ይገልጻሉ። ወጣቱ የኢሕአዴግ ባለስልጣን መሆኑን ስረዳ ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ ቅጥፈት በተሞላው የካድሬዎች ወሬ የደነቆርኩ እና የተሰላቸሁ ስለሆነ ተፈናጥሬ ወጥቼ ልሄድ ምንም አልቀረኝም ነበር። እነዚያን ታዳጊዎች አስቤ አደብ ገዛሁና

ተቀምጬ ቀረሁ። (ከሀገሬ ርቄ መኖሬ በብዙ መልኩ የሚከፋኝ ሲሆን ከኢቲቪና ከካድሬ ቱሪናፋ መራቄ ግን ተመስገን የሚያሰኘኝ ጉዳይ ነበር ::) ገና ወጣት ቢሆንም ለጋው ባለስልጣን በግርማ ሞገስ ወደ መድረኩ ቀረበና ከሕወሐት ኢህአዴግ ካድሬዎችም ሆነ ከቀደሙት የደርግ ሰዎች ታይቶ በማይታወቅ ትህትና እና አንደበት ለቤተክርስትያን አባቶችና ለታደሙት ምእመናን ሰላምታ ሰጥቶ አጭር ግን በጣም ትምህርታዊ ንግግር አደረገ። ያ ወጣት አቶ ምግባሩ ከበደ ነበር።

ለመንግሥት ሥራ አዲስ አበባ እንደመጣ ባጋጣሚ ሁሉም የመጣበት ጉዳይ በማለዳው ስላለቀለት ጊዜውን ሊጠቀምበት በመፈለግ በከተማው ምን የሚካሄድ ነገር አለ ብሎ ሲያጠያይቅ ስለዚህ መርሐ ግብር ይሰማል። ጉዳዩን የሚያውቀውም ስለሆነ ከደረስኩኝ ጠቃሚ ነገር ልማርበት እችል ይሆናል በማለት ወደ ቤተክህነት እንዳመራ በመግለጽ ንግግሩን ጀመረ። የንግግሩ ይዘት ኢትዮጵያውያን በእጅ ያለንን ወርቅ ዋጋ ባለመረዳት የኛን ጌጥ በማዝረክረክ ሌሎች የሚጥሉትን ትርኪ ምርኪ ደግሞ እየለቃቀምን በሁለት በኩል ኪሳራ እያገኘን እንደሆነ የሚያስረዳ ነበር። ከመንፈሳዊው አስተምህሮ ጋር በቀጥታ ሳይያያዝ ቤተክርስትያን ለሀገር እድገትና በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ያላትን ታላቅ ድርሻ ታሳቢ አድርጎ መንግሥት ሊያግዛት ይገባል አለ። ትምህርትን፣ ታሪክን፣ ሥነ ጽሑፍን፣ ዜማን፣ ሥነ ሕንጻን፣ ሕግን፣ ሕክምናን፣ አስተዳደርን በተመለከተ ያለውን ይዛና አስፋፍታ አዲስም ፈልስፋ ለትውልድ ያስተላለፈች መሆኗን ጠቁሞ ዛሬም ቢሆን ሕንጻዎቿ ብቻ ሳይሆኑ ጥንታዊ፣ ትውፊታዊ ሥርዓቷም በቱሪስት መስሕብነት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንኳን ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ እንደሆነ አስረዳ። ሰውን በመቅረጽ በኩል ያላትን በጎ አስተዋጽኦ በተመለከተም ከቅኔና ከፍልስፍና፣ ከትርጓሜ መጸሕፍት ትምህርት ቤት የወጣ ምሁር ባሕርዩ ዓለምን እንዲንቅ፣ ምንም ነገር ብርቁ እንዳይሆንም ተደርጎ ስለሚሳል፣ በሙስና እና በሌላ ልክስክስ ተግባር ውስጥ አይሳተፍም። በዚህም ቤተክርስትያን ዛሬ አገርን ለውድቀት እየዳረጋት ያለውን ዓይነት የሞራል ልሽቀትና ሙስና የሚጸየፍ የሰው ኃይል በማምረት ለሀገር ጠቃሚ አገልግሎት ታበረክታለችና ልትበረታታ እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶቿ ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል አለ። አቶ ምግባሩን ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ያገኘሁት ያን ዕለት ቢሆንም ፈጽሞ ልረሳው የማልችል ትውስታ በአእምሮዬ ውስጥ ቀርጾብኛል። ምንም ማስታወሻ ሳይዝ፣ ሳይዘጋጅ ወይም ሳይጋበዝ፣ በድንገት ቀርቦ እጅግ ልብ የሚነካ፣ ከለጋ እድሜው አንጻር እጅግ የላቀ ብስለትና ጥልቀት ያለው፣ ትናንት እና ነገን የዋጀ ንግግር ስላደረገ የሚያምንበትን መናገሩ ያስታውቃል። በዚህ አጋጣሚም የወጣቱን ታላቅነት ዓይተው በፓትርያኩ አጠገብ ንግግር እንዲያደርጉ የተያዘላቸውን ዕድል ለምግባሩ ያስተላለፉለትን አባት እጅግ አድርጌ ማመስገን እወዳለሁ። የምግባሩን ነፍስ ይማር። ብዙ ባለ ራዕይ የአፍሪካና የሌላም ሀገር ወጣቶች እና ጎልማሶች ላይ እንደደረሰው ለሀገሩ ሊሰጥ የሚችለውን ታላቅ አስተዋጽኦ ማበርከት በሚችልበት መልካ ተቀስፎ እንዲወድቅ ተደርጓል። እስኪ ሌሎችም ስለዚህ ሰው የምታውቁትን አካፍሉን። ለወገኖቹ ሁሉ መጽናናትን ይስጥ። እግዚአብሔር የሟቾቹን የሥራ ባልደረቦቹንም ነፍስ ይማር። የሁሉንም ልጆቻቸውን ያሳድግ።

 

አሁንገና ዓለማየሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.