ሕግ እንዲከበር የወተወተው የሕግ ባለሙያ ጨለማና ቀዝቃዛ ቤት ውስጥ ታስሯል! (ጌታቸው ሽፈራው)

የወግሰው በቀለ ይባላል። በፌደራል ጠቅላይ ቃቤ ሕግ የኢኮኖሚ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ነው። የወግሰው በቀለ በሕግ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ትችቶችን ያቀርባል። በሀገራዊ ጉዳዮች ጠንካራ ተሳታፊ ነው። አሥራት ሚዲያ ላይ ቀርቦ መንግስት ሕግ እንዲያስከብር ወትውቷል። መንግስት ሕግ ማስከበር አለመቻሉን ተችቷል። ከአሥራት ሚዲያ ባሻገር ባልደራስ ባደረገው ስብሰባ ተገኝቷል በሚል ወከባ ሲደርስበት እንደነበር ተገልፆአል።

በባሕርዳሩ ክስተት ሰበብ በርካታ የአማራ ተወላጆች ለእስር ሲዳረጉ ከታሰሩት መካከል የወግሰው በቀለ አንዱ ነው። የወግ ሰው በቀለ ጨለማ ቤት እንደታሰረና ቤተሰብ እንዲሁም የሕግ ባለሙያ እንዳያገኝ እንደተከለከለ ተገልፆአል። በጨለማና በቀዝቃዛ ቤት መታሰሩ ለጤናእክል እንደዳረገው ለፍርድ ቤት መናገሩ ተገልፆአል።

በሕግ ጉዳይ ላይ ትችት በማቅረባቸው ከታሰሩት አማራ አቃቤ ሕጎች መካከል የወግሰው አንዱ ነው። ጠ/ሚ ዐቢይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ጠንካራ ትችት ያቀረበው ጥጋቡ ባዬ እንዲሁም ታከለ የተባለ ሌላ ዐቃቤ ሕግም ለእስር ተዳርገው ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

የባሕርዳሩ ክስተት ሰበብ የሆነው ለፓርቲ አባላት፣ ተቋማትን ይመራሉ ለተባሉ እንደነ ጀ/ል ተፈራና ኮ/ል አለበል አማረ ብቻ ላይ ሳይሆን በየትኛውም መስክ ያለውን አማራ እያዳረሰ ነው። ሕግ ይከበር ያሉት የሕግ ባለሙያዎችም በማንነታቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገዋል። ሕግ ይከበር ስላሉ ጠባብና ቀዝቃዛ ጨለማ ቤት ውስጥ ቅጣት እየተፈፀመባቸው ነው። ሕግ ይከበር በማለታቸው የሕግ ባለሙያና ቤተሰብ እንዳያገኛቸው ተከልክለዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.