የአማራ ክልል መንግስታዊ መዋቅሮችና የአዴፓ አደረጃጀት መደበኛ ስራውን እያከናወነ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

የአማራ ክልል መንግስታዊ መዋቅሮችና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አደረጃጀት መደበኛ ስራውን እያከናወነ መሆኑን የአዴፓ ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረዋል።

ሊቀ መንበሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሰኔ 15 ቀን የተፈጸመው ጥቃት የክልሉን መንግስት የማፍረስና ስልጣንን በአቋራጭ የመያዝ ሙከራ ነው ብለዋል።

በዚህም ጥቃቱን የፈጸመው ቡድን በባህር ዳር ዙሪያ የሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሞክሮ እንደነበርም ተናግረዋል።

በመግለጫቸው ቡድኑ የክልሉን ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት፣ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን እና የአዴፓን ፅህፈት ቤት ለመቆጣጠር ሞክሮ እንደነበርም አንስተዋል።

ሊቀ መንበሩ በወቅቱ ለተፈጠረው ነገር ምክንያት ይኖራል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ድርጊቱ ከመፈጸሙ ከቀናት በፊት በባህር ዳር በነበረው ህዝባዊ ውይይት በአመራሮች ዘንድ የተለየ አቋም እንዳልነበር ገልጸዋል።

በወቅቱ የክልሉ ህዝብ ከሰላምና ፀጥታ አኳያ ለሚያነሳው ጥያቄ የተሰራው ስራ በተገመገመበት ወቅትም የአቋም ልዩነት አለመኖሩን ጠቅሰው፥ ድርጊቱ ስልጣንን በመፈለግ የተፈጸመ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በክልሉ መሻሻል እያሳየ ያለ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩንም አስረድተዋል።

ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራም በክልሉ የፀጥታ አካላት ብቻ እየተከናወነ መሆኑም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን በክልሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሰበብ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ግለሰቦች አልታሰሩም ነው ያሉት።

አሁን ላይ አዴፓ ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ያሉት ሊቀ መንበሩ፥ የክልሉ ህዝብም ግለሰቦች በሚፈጥሩት አጀንዳ ሊጠለፍ እንደማይገባው አሳስበዋል።

በዳዊት መስፍን/አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 1 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ)

1 COMMENT

  1. አይ የእርስዎ ነገር:: የሠላም መደፍረሱንም በተለይ የሦስቱን ሰዎች መሞትና የአንዱን መቁሰል እዚሁ ከቤትዎ ሳይነሱ ሰምተው ሲያበቁና የሦስቱን ወታደሮች መሞት ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እያሉ አዳምጠው አሜሪካን ሀገር ስደርስ የመጀመሪያ ስልክ የደረሰኝ ሊሰሙት የሚከብድ ሰውነት የሚርድ ብለው ለማልቀስ የቃጧት የሲቃ ድራማ ታሪካዊ ናት:: ይኼንን አልሰማሁም ካሉ መቼም ሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አላት አዴፖም ፕሬዚደንት አለው አይባልም:: ግን ግን እንባዋ ከመነጸርዎ ስር ኩልል ብሎ ሲወርድ ይታወስዎታል:: እኔ አይቼዋለሁ:: የእንባ ኪኒን ይሰጧችሗል ልበል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.