‹‹ዜጎች ያለስጋት እንዲኖሩና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ኅብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡›› አቶ ንጉሱ ጥላሁን

አቶ ንጉሱ ጥላሁን
አቶ ንጉሱ ጥላሁን

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2011 ዓ.ም (አብመድ) ዜጎች በሀገራቸው ያለስጋት መኖር እንዲችሉና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ኅብረተሰቡ በተደራጀ አግባብ ተንቀሳቅሶ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለፁ፡፡
ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሠላምን ለማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር መሪዎች ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በአንድነት፣ ሠላም፣ ልማትና በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትናንት ከደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ መሪዎች ጋር በደሴ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚስተዋለው ሥርዓት አልበኝነት፣ የስልጣን ጥማት፣ የግል ጥቅም ፍለጋ፣ የደቦ ፍርድና የሀሰት መረጃ የሕግ የበላይነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

“ኢትዮጵያን በብሔርና በዘር ከፋፍለው እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚሠሩ የጥፋት ኃይሎች መኖራቸው ኅብረተሰቡን ለስጋት ዳርጓል” ብለዋል፡፡

መንግሥት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ማንኛውም ሰው በየትኛዉም ቦታ ያለ ስጋት የመኖር መብቱ እንዲረጋገጥም በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በየጊዜው የሚነዙ መሠረተ ቢስ መረጃዎች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እያመሩ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሠለፍና ተቀናጅቶ በመንቀሳቀስ ለሠላምና ለሕግ የበላይነት መከበር የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

“ከዚህ በኋላ በሕዝብ፣ በመንግሥትና በአገር ላይ ለሚደቀኑ አደጋዎች መንግሥት አይታገስም፤ አጥፊዎችን በመለዬትም ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል” ሲሉም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ ደግሞ ከአጎራባች ክልሎች፤ ዞኖችና ወረዳዎች ጋር በመቀናጀት ለውጡን፣ ሠላምንና አብሮነትን ለማስቀጠል እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ ወጣቱ በሀሰት መረጃ ወደ ጥፋት እንዳያመራ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡም የፖለቲካ ጥቅመኞች መጠቀሚያ ሳይሆን የወሎን የመቻቻል፣ የአንድነትና የሠላም ተምሳሌትነት ለሌሎች በተግባር በማሳዬት ከመንግሥት ጎን እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ባለፈው ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በተከሰተው የፀጥታ ችግር መስዋዕት የሆኑ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎችን ራዕይ በማሳካት አንድነታችንን እናስቀጥላለን” ያሉት አቶ ሰይድ የወሎ ሕዝብና መሪዎች ድርጊቱን አውግዘው በእልህና በቁጭት ለሠላምና ለልማት መነሳታውን ተናግረዋል፡፡

መሪዎች ከዞን እስከ ቀበሌ በየደረጃው ሕዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

“በጥፋት ኃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከተማ አስተዳደሩ የድርሻውን እየተወጣ ነው” ያሉት ደግሞ በደሴ ከተማ አስተዳደር የአዴፓ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ወይዘሮ ምሳዬ ከድር ናቸዉ፡፡

“ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ከሕዝብ ጋር በመወያዬት እየፈታን ነው” ብለዋል፡፡
የአንድነት፣ የሠላም፣ የልማትና መቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት ሴቶች የኃላፊነት ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከ1 ሺህ 500 በላይ የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቅቋል፡፡

1 thought on “‹‹ዜጎች ያለስጋት እንዲኖሩና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ኅብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡›› አቶ ንጉሱ ጥላሁን

  1. ANDM still plays the role of a servant. Amharas are being arrested en mass from every part of the country. the organisation that claims to represent them is working with the same group that arrests amharas. Amharas are the first victims in every political system in ethiopia.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.