የዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 3/2011 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥቂት ማንነታቸውን ያልገለጹ ወጣቶች በፈጠሩት ወከባ እንደተደናቀፈበት ባልደራሱ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ወጣቶቹ ችግሩን የፈጠሩት መግለጫው ከተነበበ በኋላ ነው፡፡ በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች ምንም ርምጃ አልወሰዱም፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሰባቢ እስክንድር ነጋ ከጅምሩም ወደ ቢሮ እንዳይገባ ፖሊስ ከልክሎኝ ነበር ብሏል፡፡ መግለጫው ኢትዮጵያ እንደገና የህሊና እስረኞች ሀገር ሆናለች ያለ ሲሆን ዲያስፖራውም ይህንኑ ለዐለም እንዲያሳውቅ ተጠይቋል፡፡ የህሊና እስረኞችም ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ሕዝቡና ዐለም ዐቀፉ ኅብረተሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ በባሕር ዳር የተፈጠረው ቀውስም የኢሕአዴግ ውስጣዊ ችግር ውጤት እንጅ ከጋዜጠኞቹና ከባላደራው ጋር የሚገናኝ አይደለም- ብሏል ሰብሳቢው፡፡

2. መንግሥት የባሕር ዳሩን ኢንዱስትሪ ፓርክን ሙሉ በሙሉ ለሆንግኮንጉ “ሆፕ ለን” ኩባንያ እንዳስተላለፈው የአማራ መገናኛ ብዙኻን ዘግቧል፡፡ ኩባንያውም ፓርኩን ዛሬ ተረክቧል፤ በቅርቡም ምርት እንደሚጀምር ተገልጧል፡፡ ፓርኩ የተገነባው ጨርቃ ጨርቅን አልባሳት እንዲያመርት ነው፡፡ ግንባታው ግን እስካሁን ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም፡፡

3. 3 የትግራይ ትእምት ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻዎችን ለግል ባለሃብቶች ሊሸጡ እንደሆነ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ አክሲዮን ለመሸጥ የተዘጋጁት ኩባንያዎች የመሰቦ ሲሜንቶ ፋብሪካ፣ ሱር ኮንስትራክሽንና ትራንስ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ የክልሉ ከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በውጭ ሀገራት ያሉ የትግራዋይ ተወላጆች አክሲዮኖችን እንዲገዙ ጥሪ አድርጓል፡፡

4. የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን (አብን) በገንዘብ ትረዳላችሁ ተብለው ታስረው የነበሩ ግለሰቦች በዋስ መለቀቃቸውን ቪኦኤ ትናንት ዘግቧል፡፡ ፖሊስ 56 ግለሰቦችን ለ10 ቀናት ያሰረው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን፣ ሜታ ወረዳ ሲሆን ነዋሪነታቸውም ከጨለንቆና ቁልቢ ነው፡፡ አብን ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ሳለ ግለሰቦቹ በምን የወንጀል ድንጋጌ እንደታሰሩና ዋስም እንዲጠሩ እንደተደረጉ ዘገባው አላብራራም፡፡

5. ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዐመት ያስመዘገበቻቸውን የፕሬስ ነጻነቶች ወደኋላ የመመለስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል- ብሏል አምነስቲ ትናንት ባወጣው መግለጫ፡፡ በቅርቡ የ“አሥራት” ቴሌቪዥንና የ“በረራ” ጋዜጣ አዘጋጁ በሪሁን አዳነና የቀድሞዋ “ዕንቁ” መጽሄት አዘጋጅ ኤሊያስ ገብሩ ታስረው በጸረ ሽብር አዋጅ መከሰሳቸውን አውስቷል፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ ሚንስቴር የጦር ሠራዊቱን ስም የሚያጎድፉ ያላቸውን ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኻንን ለመክሰስ እንደተዘጋጀ ትናንት መግለጹም ስጋት እንደፈጠረበት ገልጧል፡፡ መንግሥት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታና ክሳቸውንም እንዲያቋርጥ ጠይቋል፡፡

6. መንግሥት የኢንቨስትመንት አዋጁን እያሻሻለ ነው፡፡ የሚሻሻለው አዋጅ በአየር ትራንስፖርት፣ ፖስታ አገልግሎትና የጦር መሳሪያዎች፣ ጥይቶችና ተቀጣጣይ መሳሪዎች አምራችነት፣ በኤሌክትሪክ ሃይል ምርትና ስርጭት ዘርፎች የግል ኩባንያዎች እንዲሰማሩ እንደሚፈቅድ ፎርቹን አስነብቧል፡፡ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዳይሬክተሮች ቦርድም የግሉ ዘርፍ ያለ ድምጽ ውክልና ይኖረዋል፡፡ የተሻሻለው አዋጅ በመጭው ዐመት የመጀመሪያ አጋማሽ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሏል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.