ወደድንም ጠላንም መሪ የለንም ( ሄኖክ የሺጥላ )

ቡዙ ውይይቶች ፣ እልፍ ጽሁፎች ፣ ግጥሞች ፣ ለቅሶዎች ፣ ምሬቶች ፣ ብስጭቶች ፣ መብከንከኖች እና ወዝተ ተደምረው ለውጥ ማምጣት አልቻሉም ። መበደላችን ገሞራ እንደመታው ባህር ወደ ሰማይ ቢንጠራራ ፣ ስለ ስቃያችን ማለቂያ የሌለው ሰልፍ ብንጠራ ፣ የምድር ላይ የማር እንጀራ ( ሰም ) እስኪነጥፍ የሃዘን ጧፍ እና ሻማ ብናበራ ፣ ጉልበታችን እስኪብረከረክ ፣ ድምጻችን እስኪዘጋ ብንጮህ እና ሰልፍ ላይ ብንቆምም ፣ መሪ የሌለው ትግል የትም አያደርሰንም ።

ጥያቄ አንድ
ለምሳሌ ሁለ ገብ ትግል ስንል ምን ማለታችን ነው ? ( ብረት፣ ሕዝባዊ አመጽ ፣ ገለመኔ ፣ ጂኒ – ጃንካ እንዳትሉኝ ) ። ጥያቄ የሁለገብ ትግል አይነቶች ምንድን ናቸው አላልኩም ። ሁለ ገብ ትግል ምን ማለት ነው፣ ነው ያልኩት ? እሺ ያን ትግል ማን ነው የሚመራው ? እንዴት ?

እኔ በግል ብስጭቴ ተነስቼ አንድ የወያኔ ባለስልጣንን ስቃወም ፣ ወይም ስለተቃወምኩኝ ያንን የሁለ ገብ ትግል አካል አድርጎ ለሕዝብ ማቅረብ ፣ የመሪና የስትራቴጂ ችግሮች እንዳሉብኝ የሚያሳይ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም ። ያልተደራጀ ፣ ያልተዋቀረ ፣ አጋጣሚዎችን መሰረት አድርጎ የሚግል እና ጋብ የሚል የትግል እንቅስቃሴ መሰረቱ መሪ ማጣት ነው ። ለዚህም ያልተማከለ እና መሪ የነጠፈ እንቅስቃሴ ዋነኛ ማሳያው ፣ አንዳንዴ ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚያደርጏቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው ። ለምሳሌ በግል ተነሳስተው ፣ በራሳቸው ልፋት ፣ ጥረት እና ድካም አብይ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ካሉት ሰዎች ውስጥ አቶ ከበደ አንዱ ነው ። አቶ ከበደ የግንቦት ሰባት አባል ነው ። እስከማውቀው ድረስ ፣ አቶ ከበደ እስከ ዛሬ ድረስ ያበረከታቸው ጉልህ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች አንዱም በግንቦት ሰባት ( እንደ ድርጅት ) የተሰላና ፣ ይሆን ዘንድ የተሴረ አይደለም ። ይህ ምንን ያሳያል ? እናንተው መልሱት !

ጥያቄ ሁለት
መሪ ማለት ምን ማለት ነው ? እስከሚገባኝ መሪ ማለት ፣ አእምሮው የመፍትሄ ሃሳቦችን ማፍለቅ የሚችል ፣ ህዝቦችን አንድ አድርጎ መጏዝ የሚችል ፣ ትግሉ የሚጠይቀውን ማናቸውም ነገር መጀመሪያ በራሱ ላይ የሚሞክር ። አፈር መብላት ካለበት አፈር የሚበላ ፣ መሞት ካለበት የሚሞት ፣ ተምሳሌታዊ ስብእና ያለው ፣ ግዙፍነቱ ፣ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በሰበሰበው የትምህርት ደረጃው ወይም ፣ በገነባው ፎቅና የጋሽ አጃግሬ እልልታ ሳይሆን ፣ በተጨባጭ በሚያመነጨው የመፍትሄ ሃሳብ እና የሃስብ ቅቡልነት የሚለካ ማንነት ያለው ሰው የሆነ እንደሆነ ነው ።

ጥያቄ ሶስት መሪ አለን ወይ ?

መሪ አለን ካለን ፣ የመሪ የማንነት ትርጉም ላይ ተራራ የሚያህል ግርዶሽ የጣለብን መሆን አለብን እላለሁ ። እኔ እንደተረዳሁት መሪ የለንም ። መሪ ነን የሚሉ ሰዎች ራሳቸው ወይ መሪ እስኪመጣ ነው መሪ የሆኑት ፣ ወይ ምን አገባኝ በቃ መሪ ነኝ ብለው ነው ቁጭ ያሉት ።
ይህንን የምልበት ዋነኛ ምክንያቴ ደሞ ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ማቅረብም ሆነ ፣ ዝብርቅርቁ በወጣ እና የስራ ተዋረድ በሌለው የትግል ስልት ውስጥ ብቅ እያሉ ሊቀ መንበራዊ ንግግር ማድረግ መሪ ያስብል ይሆናል ግን መሪ አያደርግም ። መሪ ለመሆን ፣ ራእይ ያስፈልልገዋል ፣ መሪ ለመሆን የጠላትን ደካማ ጎን ማወቅ ይጠይቃል ፣ መሪ ለመሆን መጀመሪያ የስልጣን አባዜ ከላያችን ላይ መውጣት / ወውረድን ይጠይቃል ። ከምንም በላይ መሪ ለመሆን ተከታይ መሆንን ይጠይቃል ።

ሲገባኝ ኢትዮጵያ ያጣችው ኢትዮጵያዊ መሪ ነው ። ኢትዮጵያ ያጣቸው የነብሱን ዋጋ ለሷ ህልውና የሚመነዝር ልጅ እንጂ ፣ በአቦ ሰጥ የሚ ውተፈተፍ መሪና ማገናዘብ ያቃተው አድርባይ ተከታይ አይደለም ። ለውጥ እንፈልጋለን ስንል ፣ መጀመሪያ ለውጡን የሚመጥን መሪ እንፈልጋለን ። ነጻነት እንፈልጋለን ስንል ፣ የዛ ነጻነት አቻ ስብእና ያለው መሪ ያስፈልገናል ። ሀገራችን ስንል እንድንሰማ ፣ በድርጅት ፍቅር ታውሮ በነገር የምቀራደድ እና በሐሰት ትግል የምሞዳሞድ ሳይሆን የሚያዋህድ መሪ እንፈልጋለን ። ከምንፈልገው የተራራ ጫፍ ላይ ያልደረስነው ፣ የፈረሳችንን ሸኾና ከተራራው ግርጌ በመሪ እጦት ስለተቀበረ ነው ። በሊቢያ ለታረዱት ወንድሞች ለማዘን መሪ አይስፈልግም ፣ ግን ያንን ሃዘን ወደ ለውጥ እንቅስቃሴ ለመምራት መሪ ያስፈልጋል ፣ የመለስ መሞት ለለውጥ አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር ፣ አጋጣሚው ለውጥ ያልሆነው ፣ ያንን ለመጠቀም የትዘጋጀ ሕዝብ ስለሌለ ሳይሆን ፣ ያንን አጋጣሚ ወደ ለውጥ መቀየር የሚችል መሪ ስለሌለ ነው ፣ ቀጣዩ ምርጫ ሌላው የለውጥ አጋጣሚ ነው ፣ ስለ ምርጫው ማውራት ( ማንኛውንም አይነት ወሬ ሊሆን ይችላል ) ምንም የሚፈይደው ነገር የለም ፣ ግን ይህን ኢ-ፍትሃዊ ምርጫ ወደ ፍትሃዊ አመጽ መቀየር የሚቻለው መሪ ሲኖር ብቻ ነው ። ። አንድ የመንግስት ባለስልጣንን ማዋረድ ትግል ነው ያለው ማን ነው ? እሱ ትግል አደለም የብስጭታችን ልክ ነው ፣ የመጨታችን ጣራ ነው ፣ ወደ ትግል መነሻ መንገድ ሊሆን ይችላል ፣ ግን ትግል አይደለም ። እስካሁን መሪ ሳይሆን ፣ ስለ አጋጣሚዎቹ ክፋት የሚተነትን ፖለቲከኛ ነው ያለን። እሱን ደሞ የትም አለ ! በርካሽ ሁሉ አለ ። በብላሽ ( እንዳለው ቲመርጋ ሙዝ ነጋዴው ) በብላሽ ሁሉ አለ !

መደምደሚያ

አንዱ ነው ፣ ከመጠን በላይ ሙዝ በልቶ ፣ ልውጣ አልውጣ እያለ ሲተናነቀው አንድ ሰው ያየዋል ። ” ምነው እንዲህ ከምትጨነቅ ለምን በጣትህ ጎርጉረህ አታወጣውም?” ይለዋል ፣ የማርያም ጣቱን እያሳየ ። ታዲያ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው ፣ ” አይ ለሱ ( ለትንሿ ጣቴ ) የሚሆን ቦታማ ባገኝ ፣ ሌላ ሙዝ እጨምርበት ነበር ። ለሚገባው ይግባው !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.