ትህነግ/ሕወሓት ለምን ደነገጠ? (ጌታቸው ሽፈራው)

የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር ትህነግ/ TPLF አስቸኳይ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫው የተምታታና በድንጋጤ የተሰጠ ለመሆኑ ይዘቱ ምስክር ነው። በተለይ በአዴፓ አመራሮች ላይ የተፈፀመውን ግድያ በተመለከተ የተሰጠው መግለጫ ትህነግ/ሕወሓትን ለምን ደነገጠ የሚል ጥያቄ ያጭራል። ትህነግ/ሕወሓት በመግለጫው የመጀመርያ ነጥብ ያደረገው የጀኔራሎቹን ግድያ ሲሆን ግድያው በውጭና በሀገር ውስጥ ኃይሎች የተቀነባበረ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሞ ተጣርቶ እንዲቀርብ ይጠይቃል። በአንፃሩ የአዴፓ መሪዎች ግድያ ፓርቲው ውስጥ በነበረ ችግር የተፈጠረ መሆኑን ደምድሞ እንደገና ምርመራው ተጠናቅቆ ይፋ እንዲሆን ለመምከር ይሞክራል። አንዴ ሶስተኛ ወገን የለበትም ብሎ ይደመድማል። ጥፋቱ የአዴፓ ነውና ሕዝብን ይቅርታ ይጠይቅ ይላል። ቀጥሎም ምርመራው ተጠናቅቆ ይፋ እንዲሆን ይጠይቃል። ሶስተኛ ወገን የለበትም፣ የአዴፓ ጥፋት ነው የሚለው ባልተጠናቀቀና በማያውቀው ምርመራ መሆኑን የሚናገረው የራሱ መግለጫ ነው!

ትህነግ/ሕወሓት በጥድፊያ መግለጫ እንዲሰጥ ያደረገው የአዴፓ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ግድያው ላይ ሴራ እንዳለበት መግለፃቸው ይመስላል። አቶ ደመቀ መኮንን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰው ናቸው። ምርመራው በቅርብ ርቀት እየተከታተሉም ይሆናል። ትህነግ/ሕወሓት በአንፃሩ መቀሌ ሆኖ “የሶስተኛ ወገን እጅ የለበትም” እያለ ይበሳጫል። እነ አቶ ደመቀ የሶስተኛ ወገን አለበት ብለው ማመናቸውን “ልክስክስ” አቋም ብሎ ዘልፏል። አብሬያቸው አልሰራም አይነት ማስጠንቀቂያም ሰጥቷል።

የትህነግ/ሕወሓት የድንጋጤ መግለጫ:_

1) በምርመራ ላይ ባለ ጉዳይ ላይ ቀድሞ የወሰነ መግለጫ ነው። በምርመራ ላይ ብቻ ሳይሆን በፍርድ ቤት ሂደት ላይም ጫና የሚያሳድር የአንድ ወገን መግለጫ ነው! አዴፓ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሚወተውተው ትህነግ/ህወሓት በምርመራ ጉዳይ ላይ ቀድሞ በመግባትም ሆነ በፍርድ ቤት ጉዳይ የሚያሳድረው ጫና ይቅርታ ሊያስጠይቀው የሚገባ ነው።

2) የክልሉ መንግስት ምርመራውን እየመራ ባለበት ወቅት የሶስተኛ ወገን የለበትም ብሎ መደምደሙ ስህተት ከመሆኑ ባሻገር መግለጫው ትህነግ/ሕወሓት ለምን የድንጋጤ መግለጫ ሰጠ? ለምን ሶስተኛ ወገን አለ ሲባል ደነገጠ የሚሉ ሌሎች የምርመራ ክሮችን የሚስብ ነው!

3) ከአዴፓ አመራሮች ጋር በአንድ ቀን የተፈፀመውን የእነ ጄ/ል ሰዓረ መኮንን ግድያ ሶስተኛ ወገን (የውጭና የሀገር ውስጥ ብሏል) እጅ ያለበት መሆኑን የጠቆመው ትህነግ/ህወሓት የአዴፓ መሪዎች ላይ የተፈፀመው ሌላ ወገን የለበትም ለማለት ለምን ደፈረ? የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

4) የትህነግ/ሕወሓት ትልቁ ድፍረት የአዴፓ መሪዎች ላይ የተፈፀመው በውስጥ ጉዳይ መሆኑን ሕዝብ አውቆት ያደረገ ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል። የትኛው ሕዝብ ነው? የአማራ ሕዝብ ከመጀመርያው ጀምሮ፣ እነ ደመቀ መኮንን ሳይናገሩም የሌሎች እጅ ሊኖርበት እንደሚችል ትህነግ/ሕወሓት መግለጫውን ሲሰጥ እንዳሳየው ያሉ መደነባበሮችን እየጠቀሰ ሲሞግት ቆይቷል። ትህነግ/ሕወሓት ግን በድፍረት ተነስቶ ሕዝብ አውቆት ያደረ ጉዳይ ነው ሲል መግለጫ ሰጥቷል።

ትህነግ/ ሕወሓት ለምን በዚህ መጠን ደነገጠ? ትልቅ ጥያቄ ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.