ፌዴራሊዝም በምን ቅርፅ ቢሆን ለኢትዮጲያ ይጠቅማል – ስለ አቶ ሌንጮ ለታ (መላኩ ግርማ)

ህገ መንግስታዊ መሰረት ባለው የጎሳ ፖለቲካ ሃገር እንደዚህ እየተናወጠች ባለችበት ሰዓት ‘ፌዴራሊዝም በምን ቅርፅ ቢሆን ለኢትዮጲያ ይጠቅማል’ በሚል የተዘጋጀ ባለ ሁለት ክፍል ዩቲዩብ ቪዲዮ ስመለከት ፥አርእስቱ ቀልቤን ሳበውና ከፈቼ መከታተል ጀመርኩ።ይህን ቪዲዮ እንድከታተል ተጨማሪ ምክንያት የሆነኝ የሃሳብ አቅራቢ ከነበሩት የመጀመርያው፥የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር መስራች አባል የሆኑትና ህገ መንግስቱንም ከመለስ ዜናዊጋ በመሆን አብረው አርቅቀዋል እየተባለ ስማቸው የሚጠራው አቶ ሌንጮ ለታ መሆናቸው ነው።

አቶ ሌንጮ ዕድሜ ጠገብና በሃገራችንም ፖለቲካ ዕድሜ ልካቸውን ሁሉ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ቆሜለታለሁ ላሉት ህዝብ ጥቅም በገባቸው መልኩ ሲታገሉ የኖሩ በመሆናቸው አክብሮቴ በዚሁ እንዲደርሳቸው እፈልጋለሁ።ሃቀኛ እይታን ለማጋራትና መግባባትንም ግብ ከማድረግ አኳያ እሳቸው የተናገሩትን መዝግቤ ከዚህ ፅሁፍ መጨረሻ ላይ አያይዤዋለሁና ፥ከአፋቸው ያልወጣውን በሃሰት መሰረት አድርጌ የመከራከር ፍላጎት እንደሌለኝ ይታወቅልኝ።

ካቀረቡት ሃሳብ አንዱ የህገ መንግስቱ እኛ የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሎ መጀመር ህገ መንግስቱን ለሚተቹ ሰዎች ዘግናኝ እንደሆነና እኛ የኢትዮጲያ ህዝብ ብሎ እንዲጀምር እንደሚፈልጉ ገልፀው ይህም የተፈለገበት ምክንያት ኢትዮጲያ የአንድ ህዝብ የአንድ ብሄር ሃገር ሆና እንድታይ ከመፈለግ ነው  ይላሉ።

ከዚህ በፊት የነበሩ መንግስታት ይህንን ለመተግበር በሄዱበት ርቀት ተቃርኖው እንዳደገና እሳቸውም ማንነታቸው እንዳይፋቅ ነፍጥ አንስተው የታገሉት ሃሳብ እንደነበረና ሶማልያንም እንደምሳሌ በመግለፅ ያብራራሉ።አንድ ቋንቋ አንድ ባህል አንድ ህዝብ መኖሩ የሰላምና ህዝብ መረጋጋት መሰረት ሊሆን እንደማይችል ሩቅ ሳንሄድ ሶማልያን መመልከት ጠቃሚ እንደሆን ያስረዳሉ።

ከተለያዩ የፌዴሬሽኑ ተቃዋሚዎች ከሚሏቸው አመለካከቶች የዜግነት ፖለቲካ አራማጆችን እንደምሳሌ ይጠቅሱና እስካሁን በኢትዮጲያ የዜግነት መብት ተከብሮ ስለማያውቅ የዜግነት ፖለቲካ ከብሄር ፖለቲካ የበላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ትክክል እንዳልሆነና እንደውም በሃገራችን የነበረው ሁኔታ የጎሳ ፖለቲካን አስፈላጊነት የሚያጠናክር እንጂ የዜግነት ፖለቲካ አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም ይላሉ።

በመጨረሻም ያነሱት ሃሳብ ህገ መንግስት የሚለው ቃል በፈረንጆቹ ኮንስቲትዩሽን የሚለውን ቃል በትክክል እንደማይገልፅና ከህገ መንግስት ወደ ህግ ሀገረ ብንሻገር ነው በማለት የነበሩት ህገ መንግስቶች ከመንግስታት የተሰጡ እንጂ በህዝብ ስምምነት ያልፀደቁ እንደነበሩ በሚከተለው አገላለፅ አቅርብውታል።ይህም እሳቸው ከመለስጋ አብረው አፀደቁ እየተባሉ ስማቸውን እያስነሳ ያለውንም የአሁኑ ህገ መንግስት እንደሚጨምር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

“በሃምሳ አምስት ግርማዊ ጃንሆይ መጀመርያ የሰጡንን ህገ መንግስታቸውን አሻሻሉ።ማንንም ሳይጠይቁ ምንም ውይይት ሳይካሄድ ።መንግስቱ (ደርግ ) አስራ ሶስት ዓመት ከገዛ በኋላ የራሱን ህገ መንግስት ደግሞ አወጣ።ኢህአዲጎችም አራት ዓመት እንደዚህ ከገዙ በኋላ ኢትዮጲያን አሁን ያለውን ህገ መንግስት ሰጡን።የሚሻለው ወደ ህግ ሃገር ብንሻገር ነው።”

የአቶ ሌንጮንና የሌሎችንም ትንታኔዎች ከተመለከትኩ በኋላ የተረዳሁት ውይይቱ በጥቅሉ የብሄረሰብ ቋንቋና ባህል መከበር እንዳለበት ከመስማማት ውጪ ተጨባጭ የሆነና ፌዴራሊዝም በምን ቅርፅ ቢሆን ለኢትዮጲያ ይጠቅማል ለሚለው ጥያቄ የአማራጭ ሃሳቦችን አቅርቦ የተወያየ አልነበረም።ሰልዚህ ዋና ዋና ሃሳቦችን ለአቶ ሌንጮና የሳቸውን ሃሳብ ለሚጋሩ በማቅረብ የራሴን ዲስኩር ላቅርብ።

ህገ መንግስቱ እኛ ኢትዮጲያውያን ብሎ ቢጀምርና ኢትዮጲያ ብዝሃነት ያላት ሃገር እንደሆነችና የኢትዮጲያ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን የመጠቀምና የማሳደግ መብት እንዳላቸው ቢጠቀስ ምን ችግር አለው።ለብዙ ሺህ አመታት የኖረችን ሃገር ለምን ልክ ትላንት ወያኔ የሆኑ ሰዎችን አሰባስቦ እንዳቋቋመው ዕድር ተመስላ ትቀርባለች።እኛ ኢትዮጲያውያን ብሎ ማሰብ በህዝቦች መሃከል የነበረውንና ወደፊትም እንዲኖር የምንፈልገውን ተባብሮ ድህነትን መዋጋት ከጠላት መመከትና በሰላምም አብሮ ከመኖር አንፃር ያለው እንደምታ እንዴት ሊገባን አልቻለም።

አቶ ሌንጮ በትክክል እንደገለፁት በሃገራችን ኢትዮጲያ የዜግነት መብት ተከብሮ አያውቅም።ነገር ግን ይህ እንዴት የጎሳ ፖለቲካን የተሻለ ስለመሆኑ እንደ ማስረጃ ይቀርባል። የጎሳ ፖለቲካ በሃገራችን ከተንሰራፋ ይኽው ሃያ ስምንት ዓመታትን አስቆጠረ። የጎሳስ ፖለቲካ መች የህዝቦች የዜግነት መብት መከበር ዋስትና ሆነ።እንደውም በፊት በዜጎች ላይ ከመንግስት ይደርስ የነበረው የዜግነት ጭቆና ፋፍቶና ሌላ ዜጎችን በገዛ ሃገራቸው እንደሁለተኛ ዜጋ የሚታዩበትን አሳዛኝና አሰቃቂ ሁኔት መፍጠሩን እንዴት እንዘነጋዋለን።ባንድ በኩል የአንድ አካባቢ ሰዎች ቋንቋቸውን እንዲጠቀሙ ቢፈቅድና ያም የዜግነት መብት አስከበረ ብንል ፥እነዚሁ ሰዎች ወደሌላው የሃገራቸው ክልል ሲሄዱ በሃገራቸው ሁለተኛ ዜጋ ያደርጋቸዋል።ምሳሌ አማራ በጉራፈርዳ ፥ኦሮሞ ከሱማሌ፥ ደቡቦች ከቡራዩ።

ሱማልያን እንደምሳሌ አድርገው እንደጠቀሱት ህዝቡ በመሃከሉ ሌሎች ልዩነቶች ስላሉ አንድ ቋንቋ አንድ ሃይማኖት እያለው አንድ መንግስት ሆኖ ለመቆም አለመቻሉን እንደምሳሌ እንዳቀረቡት በሃገራችንም እንደዚሁ ብሄር በተባሉት እንኳ መለስተኛ የቋንቋ የባህልና የአስተሳሰብ ልዩነቶችን በመጨፍለቅ አንድ ቋንቋ አላቸው በሚል ብቻ ኦሮሞውን ሁሉ ኦሮምያ በሚባል ክልል፥አማራውንም እንደዚሁ አማራ በሚባል ክልል ወዘተ መጨፍለቅና ትክክለኛ ለህዝቡ ቅርብ የሆኑ አስተዳደሮች እንዳይኖሩ ማስመር ለምን አስፈለገ።

አሁን ሃገራችን ያለው የጎሳ ፌዴራሊዝም ፤የጎሳ ፌዴራሊዝማችን አይነካብን በሚል የሚገለፅ አንድ ሃሳብ ሳይሆን ፤ከታች ወደ ላይ እንደ አነባበሮ የተደራረቡ የተለያዩ የፖለቲካ ውሳኔዎችን የያዘ ሲሆን፤ አሁን ያለውንና ወደፊት እንዲሆን ከመሻት አኳያ ኢትዮጲያ ትበታተን ከሚሉ እስከ ንጉሳዊ ስርዓትን በተወሰነ ደረጃ መመለስ እስከሚፈልጉ  በተለያየ የአመለካከት ጎራ ያሉ ኢትዮጲያውያን ፥ያሉንን ልዩ ልዩ ሃሳቦች ስናጠቃልልና ፌዴራሊዝም በምን ቅርፅ ቢሆን ለኢትዮጲያ ይጠቅማል ስንል የሚከተሉትን በዝርዝር ተመልክቶ መወያየት ጥቅሙ አሌ የማይባል ነው።

ፌዴራሊዝም በምን ቅርፅ ቢሆን ለኢትዮጲያ ይጠቅማል

ባለ አስራ አምስት አብይት መስፈርት – ፌዴራላዊ አወቃቀር አማራጮች

I II III IV
15 ሃገሪቱ በፕሬዜዳንት ትመራ።ውስን ስልጣን የሚኖራቸው ሰለሞናውያኑ ይመለሱና የፕሮቶኮሉን ስራ ይስሩ No No Yes No
14 ሃገሪቱ በፕሬዜዳንት ትመራ No Yes No Yes
13 ሀገሪቱ በጠቅላይ ሚንስትር ትመራ። ፕሬዜዳንቱ ፕሮቶኮሎችን ይፈፅም Yes No No No
12 ኦሮምኛ የፌዴራል መንግስቱ ሁለተኛ የስራ ቋንቋ ይሁን No Yes Yes Yes
11 ለአብሮነት አመቺ ስለሚሆን አካባቢያዊ አስተዳደሮች ሁሉም አማርኛን እንደ ሁለተኛ የስራ ቋንቋ ይጠቀሙ No Yes Yes Yes
10 አካባቢያዊ አስተዳደሮች ካርታ ደርግ መጨረሻ ላይ ወዳመጣው 30 አስተዳደር ይቀየሩ No No No Yes
9 የአካባቢያዊ አስተዳደሮች ካርታ ወደ ቀድሞው 13ቱ ይመለሱ። No No Yes No
8 የአካባቢያዊ አስተዳደሮች ካርታ አሁን ያሉት ክልሎች ይሁኑ Yes Yes No No
7 አካባቢያዊ አስተዳደሮች እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ብቻ ይረጋገጥ No Yes Yes Yes
6 የአካባቢያዊ አስተዳደሮች እራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ይረጋገጥ Yes No No No
5 መንግስትና ፖለቲካ ውስጥ ዜጎች የሚኖራቸው ተሳትፎ በነዋሪነት ላይ የተመሰረተ ይሁን No Yes Yes Yes
4 መንግስትና ፖለቲካ ውስጥ ዜጎች የሚኖራቸው ተሳትፎ በዘር ላይ የተመሰረተ ይሁን። Yes No No No
3 መሬት በቋንቋ መከለል አለበት Yes Yes No No
2 ዜጎች  ቋንቋቸውን በአካባቢያዊ አስተዳደራቸው ይጠቀሙ Yes Yes Yes Yes
1 ዜጎች  ቋንቋቸውን ይገልገሉ ባህላቸውን እንዲያበለፅጉ ይበረታቱ Yes Yes Yes Yes

 

ማስታወሻ – አራቱ በዋናነት ለምሳሌ የቀረቡ የፌዴራሊዝም አማራጮች ናቸው።

አማራጭ 1 – አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ነው።

አማራጭ 2 – አንቀፅ 39ና የጎሳ ፖለቲካ ይቅር፥ተጨማሪ ክልላዊና ፊዴራላዊ ቋንቋ ይኑር።

አማርጭ 3 – አማራጭ ሁለት ከአስራ ሶስቱ ክፍላተ ሃገራትና ሰለሞናውያን ለፕሮቶኮል።

አማራጭ 4 – አማራጭ ሁለት ከደርጉ ሰላሳ አስተዳደሮችና ፕሬዜዳንታዊ ስርዓት።

የዛ ‘ፌዴራሊዝም በምን ቅርፅ ቢሆን ለኢትዮጲያ ይጠቅማል’ በሚል የተዘጋጀ ውይይት አሁን ያለውን ህገ መንግስት መቃወም ማለት ፌዴራሊዝምን በጥቅሉ ማውገዝ ማለት እንዳልሆነ በማጤን ያሉትን አማራጮች እንደዚህ ዘርዝሮ ቢተች ጠቃሚ ይሆን ነበር።

መላኩ ግርማ

አትላንታ

የአቶ ሌንጮ ንግግር ቃል በቃል (ባብዛኛው)

Source – https://www.youtube.com/watch?v=5CidKZV_h24

እኛ የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሎ ይጀምራል። ይሄ ነው አወዛጋቢው ።ውዝግቡን የሚያስነሳው ይሄ ነው።ተቃዋሚዎቹ ይህ መክፈቻ ሃረግ ይዘገንናቸዋል።የሚመርጡት እኛ የኢትዮጲያ ህዝብ ብሎ እንዲጀምር ነው።ያ እነሱ የሚመርጡት ኢትዮጲያ የአንድ ህዝብ የአንድ ብሄር ሃገር ሆና እንድታይ ነው የሚፈልጉት።ይሄን ግን የቀድሞው መንግስታት ሞክረውታል።የኢትዮጲያን ህዝብ የተለያዩ ማህበረሰቦችን አንድ ላይ አዋህደው አንድ ብሄር ብቻ እንዲሆንና በዛም መሰረት የኢትዮጲያ ህዝብ ተብሎ እንዲታወቅ አንድ ወጥ የሆነ ማህበር እንዲኖር ሞክረዋል።ያ ነው ጦርነት ያስነሳው።አንዳንዶቻችን ጫካ ገብተን የተዋጋነውኮ ማንነታችን እንዲፋቅ እንዲጠፋ ተሞክሮ ነው።ያንን ተቃውመን ነው።ህግኮ ያወጣ መንግስት ነውኮ አንዳንድ ቋንቋዎች እንዲደመሰሱ ብሎ።ቋንቋን ከደመሰስክ ብሄርን ደመሰስክ ማለት ነው።ያንን መደምሰስ የማንፈልግ የተቃወምን ቡድኖች ጫካ ገብተን ተዋጋን።ለዛ መፍትሄ ነው ተብሎ ነው የብሄሮቹ ፌዴሬሽን የተዋቀረው።አንድ ቋንቋ አንድ ባህል አንድ ህዝብ መኖሩ የሰላምና ህዝብ መረጋጋት መሰረት ይሆናል ብለን ካሰብን ሩቅ መሄድ አያስፈልግም እዚሁ ጎረቤታችን ያለችውን ሶማልያን መመልከቱ በቂ ነው።የጌሊ ቋንቋ እንዲጠፋ እንግሊዞች ሰርተዋል ግን የስኮቲሽ ናሽናሊዝምን ለመደምሰስ አልቻሉም።ቋንቋም ጠፍቶ ማንነትም ጠፍቶ ግን እራሱን በሌላ መልኩ ሊገልፅ ስለሚችል ያ ፊዩታይል ኤርት ነው ብዬ ነው የምወስደው እኔ ።

የፌዴራሽኑ ተቃዋሚዎች የተለያዩ አማራጮችን ሲያቀርቡ እናያለን።አንድ ብቻ ልውሰድ የዜግነት ፖለቲካ ብለው የሚናገሩ አሉ። የዜግነት ፖለቲካ ከብሄር ፖለቲካ በላይ እንደሆነ አድርገው የበለጠ አዋሃጅና አንድነትን የሚጠብቅ አስመስለው ያነሱታል።ግን ትልቁ ነገር በኢትዮጲያ የዜግነት መብት ተከብሮ ያውቃል ወይ ብለን ከጠየቅን ሌላ ነገር እንረዳለን።የዜግነት መብት መገለጫዎች ሶስት ስብስቦች አሉ። የመጀመርያው የሲቪል መብቶች ናቸው።

የሲቪል መብቶች በህግ ፊት እኩል መሆን የፐርናል ኢንተግሪቲ መከበር ናቸው ሁለተኛው የፖለቲካ መብቶች ናቸው እንኚህ ደሞ በፖለቲካ መሳተፍ የመምረጥ የመመረጥ መብት ያካትታል።ሶስተኛው ሶሻል ራይትስ ይባላል።ይህ የትምህት ዕድል ማግኘት የህክምና ዕድል ማግኘት የስራ ዕድል ማግኘት ይሄን ይሄን ያካትታል።አሁን አሁን አንዳንድ ፀሃፊዎች የቋንቋና ባህል መብትም ተጨምሮ አራተኛ የመበት ስብስቦች ካልኖሩ ዜግነት አይሟላም የሚሉ አሉ እኔም ከዚህ እስማማለሁ።ለምን ቋንቋ ካልተጨመረ ሶስቱ ይሸረሸራሉ።

ስለዚህ የዜግነት ፖለቲካ ብሎ የሚቀርበው በዚህ አኳዧኋን ካየን አሁን ያለውን ፌዴሬሽን ያጠናክራል እንጂ አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም።አሁን ያለው ህገ መንግስት ብዙ ጉድለቶች አሉት።መሻሻል የሚፈልጉ ጉድለቶች አሉት ነገር ግን ፌዴሬሽኑን ለማፍረስ የሚፈልግ ማንም ሰው ካለ ኢትዮጲያንም ወደማፍረስ እንዳይመራ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።በመጨረሻ አንድ የማነሳው ነገር እኔ ህገ መንግስትና ኮንስቲትዩሻን የተለያዩ ናቸው ብዬ ነው የማምነው።ኢትዮጲያ እስከዛሬ ህገ መንግስት ነው እንጂ ያላት ኮንስቲትዩሽን ኖሯት አታውቅም።ኮንስቲትዩሽንና ህገ መንግስት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።ሌሎች ሃገሮች ህገ መንግስት ኖሯቸው አያውቁም ። ኮንስቲትዩሽን ነው ያላቸው።በአማርኛ ደሊበሬትሊ ሚስትራንስሌሽን አለ።ህገ መንግስት ብለው የቀረፁትን ሰነድ በእንግሊዘኛ ሲተረጉሙት ኮንስቲትዩሽን ብለውታል።ነገር ግን የተለያዩ ነገሮች ናቸው።ህግ መንግስት  መጀመርያ ዚህ ሃገር የታየው ግርማዊ ጃንሆይ በሰላሳ አንድ የመጀመርያው ህገ መንግስት ሲያፀድቁ ያሉት ነገር ነበር።ሳንጠየቅ ሳንገደድ መልካም ፍቃዳችን ሆኖ ለኢትዮጲያ ህዝብ ህገ መንግስት ሰጠን።የሚሰጥ ህገ መንግስትኮ ኮንስቲትዩሽን አይደለም።ስጦታ ነው ማለት ነው።

የሚሰጠው ግለሰብ ወይም አካል ከህገ መንግስቱ በላይ ነው።ህገ መንግስት ከኮንስቲትዩሽን የተለየ ነገር ነው።አሁን የሚያስፈልገን ምንድነው ኮንስቲትዩሽን ነው።ሌላ ቃል ብንፈልግለት ይሻላል የሚል ዕምነት አለኝ እኔ።ህገ መንግስት ማለት እኔ ግዕዝ ባላውቅም የመንግስት ህግ ማለት ነው።መንግስት የሚያወጣው ህግ በዚህ እገዛሃለሁ ብሎ የሚያወጣው ሰነድ ነው እንጂ የሃገር ህግ አይደለም።ኮንስቲትዩሽን ግን የሃገር ህግ ነው።ሀገሩ የተስማማበት ኮምፕሮማይዝ አድርጎ የደረሰበት ገዢውም ተገዢውም የሚተዳደርበት ዶኩመንት ነው።ህገ መንግስት ግን የመንግስት ህግ ነው።መንግስት ሲፈልግ ያከብረዋል ሲፈልግ ያፈርሰዋል።ሲፈልግ ይቀይረዋል እንደፈለገ ያደርገዋል ይሄ አዲስ ነገር አይደለም።

በሃምሳ አምስት ግርማዊ ጃንሆይ መጀመርያ የሰጡንን ህገ መንግስታቸውን አሻሻሉ።ማንንም ሳይጠይቁ ምንም ውይይት ሳይካሄድ ።መንግስቱ አስራ ሶስት ዓመት ከገዛ በኋላ የራሱን ህገ መንግስት ደግሞ አወጣ።ኢህአዲጎችም አራት ዓመት እንደዚህ ከገዙ በኋላ ኢትዮጲያን አሁን ያለውን ህገ መንግስት ሰጡን።የሚሻለው ወደ ህግ ሃገር ብንሻገር ነው።እና ይሄን ብዬ ውዝግብ ፈጥሬ በዚሁ አበቃለሁ።አመሰግናለሁ።

3 COMMENTS

 1. Killil named oromo, amhara, tigre, somali, afar etc should be scrapped. this is the idea of cesesionist ethno liberation fronts, olf ,tplf.
  Tplf ‘s political programme is to create tigre republic. olf is the same. using the constitution lencho letta carved out what he calls oromia. his ambition was to create oromo republic.
  tigre libberation front did not push for cessession in the last 27 years because they had the opportunity to loot and plunder ethiopia unopposed. now that privilege is gone, they are back again pushng for cessession. that is their ambition.
  both olf and tplf are anti ethiopia. they have proved this time and time again.

 2. Mamo; if “both olf and tplf are anti ethiopia” that together claim to represent about 50% of the population, what is ‘Ethiopia’ they are enemies of? According to you then, Ethiopia (and Ethiopians) are the rest, better the 25% Amhara and so called ‘Ethiopianists’. If so, why do you blame them, since they are not claiming your ‘Ethiopia(ns)’?

 3. Dear Melaku,with due respect to your presentation and recognition to the sacrifice of Lencho for Oromo cause, I do not consider his ideas as credible based on his inconsistency positions and irrelevant immature statements .Lencho was a co-signer of failed constitution of current Ethiopia where his comrade Negasso apologized the people of Ethiopia before his death as it was not a constitution with the participation of people as a democratic constitution jut a fabrication of rebel leaders who stood all against the military Junta with a dream of sharing power. Lencho once said he prefer to be a minster of bigger Ethiopia than the smaller Oromoia and regarding his refugee life he said it would be better to come back to the warmth of home (Ethiopia) instead of freezing at the of cold Europe where he spent as refugee.
  Please choose sound reliable commentator for such decisive political issues.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.