መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በምስራቅ ጎጃም ዞን መርጦ ለማሪያም ወረዳ ጎንቻ በተባለ ስፍራ መመታቱ ታውቋል።

እንዲህ መሆናችን ያሳዝናል!

መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በምስራቅ ጎጃም ዞን መርጦ ለማሪያም ወረዳ ጎንቻ በተባለ ስፍራ መመታቱ ታውቋል። ትናንት ማታ ከምሽቱ 4ሰዓት ላይ ወታደሮቹ ወደ መንደሩ ሲዘልቁ ያየቻችው እህቱ “ወንድሜ መጡልህ! እጅህን እንዳትሰጥ!” በማለት ወደወታደሮቹ እየተኮሰች ወደቤት መሸሿን ተናግራለች። ትናንት በሰባት መኪና ተጭኖ ወደአካባቢው የገባው ሰራዊት ወንድሜን ለመያዝ እንደመጣ ስላወኩ አድፍጨ ስጠብቅ ነበር ያለችው እህቱ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የቆሰለው ከዘመተበት ገዳይ ሰራዊት ጋር ራሱን ለመከላከል ባደረገው ፍልሚያ መሆኑን ገልጻለች። በተኩስ ልውውጥ ሲመታ አብሬው ነበርኩ ያለችው እህቱ ከተመታ በኋላ ጫካ ለጫካ ወስጄ ወደገደል ውስጥ በመግባት ህዝቡ እንዲያድነን ኡኡታየን በማሰማቴ ለጊዜው በተሰማሩብን አውሬዎች ከመበላት ተርፈናል ብላለች። ህዝቡም መቶ አለቃ ማስረሻን አሳልፈን አንሰጥም ብሏል። ህዝቡ በካባድ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ማስረሻ ወዳለበት አካባቢ ሊገባ የነበረን ቁጥሩ የበዛ ሰራዊትም ድልድይ በመስበር እንዳስቆማቸው ታውቋል። ህዝቡ “ማስረሻ የኛ ልጅ ነው። እኛ ሞተን ሳናልቅ እሱን አትወስዱም።” ያለ ሲሆን አንዳንድ ወታደሮች ገፍተው ለመግባት ሲሞክሩም ህዝቡ የማስጠንቀቂያ ጥይት እየተኮሰ ባሉበት አቁሟቸዋል። በአሁኑ ሰዓት ህዝቡ እና ወታደሮቹ ከድልድዩ ወዲህ እና ወዲያ መፋጠጣቸው ታውቋል። ወታደሮቹ ማስረሻን አሳልፋችሁ ካልሰጣችሁ አካባቢውን በከባድ መሳሪያ እንደበድባለን በማለት እየዛቱም ነው።

ማስረሻ መናገር እንደማይችል እና ህክምና አለማግኘቱ ለህይወቱ ያሰጋዋል ያለችው እህቱ በአሁን ሰዓት የአካባቢው ህዝብ ባህላዊ ህክምና እንዳደረገለት ገልጻለች። “ወንድሜን ላጣው ነው። ማስረሻን ላጣው ነው።” በማለትም አንብታለች። አባቷ ከቀናት በፊት መታፈናቸውን ሲቃ እየተናነቃት የተናገረችው እህቱ “ይህን ግፍ ለዓለም ንገሩልን” ብላለች። ይህ እንዳይሆን ብዙ መስራት ይችሉ የነበሩት የአማራ አክቲቪስቶች እርስ በርስ በጎጥ ሲነካከሱና ዛሬም ቢሆን እንትና ይመረጥ አይመረጥ እያሉ በማያገባቸው የአዴፓ የውስጥ ጉዳይ ሲፈተፍቱ ይስተዋላል። ከዚህም አልፎ በድጋሚ የተነቃቃውን የህዝብ ትግል “የለም፤አልተደረገም፥ውሸት ነው” እያሉ እኛ ፖለቲካውን ካልተቆጣጠርነው “ባርነቱ ይሻላል” የሚል እንድምታ ያለው የሁነት እና ድርጊት ማስተባበያ ሲጽፉም እየታዘብን ነው። ትግሉን የኛው ሰዎች የሚመስሉን(ምናልባትም ከልብ ያልሆኑ) አክቲቪስቶች እየተረባረቡ ሲያዳፍኑ ማየት በርግጥ በጣም ያማል። ይበልጥ የሚያመው ደግሞ ይህን የማስረሻን ስቃይ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ ሲሯሯጡበት የማየቴ ነገር ቅርብ መሆኑን መረዳቴ ነው። የአማራ ብሄርተኝነት የሚባለው ትግል በከፊል የቁማር ቤት መሆኑን እያረጋገጥሁ ነው። አሁንም ቢሆን መለየት ያለብንን ሰዎች በትክክል እና በጊዜ ካላወቅን የአማራ ብሄርተኝነት ለጥቂቶች የገንዘብ ምንጭ ለአብዛኛው አማራ ደግሞ የመከራ ድግስ የመሆኑ ነገር አይቀሬ መሆኑን ነው።

ቅዱስ መሃሉ

2 COMMENTS

  1. I am sure that this activity can split the amhara region into pieces. I advise everyone to stop persecuting Masresha and Zemene. If not the outcome will be rather worse.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.