“ካልደፈረሰ ኣይጠራም” መዘዝ ቀላል ኣይደለም – መስፍን ነጋሽ

የህወሓት እና የአዴፓ የቃላት ጦርነት አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ከታየ ሃላፊነት የጎደለው፣ ብስለትና አርቆ አስተዋይነት የራቀው ተግባር ነው። ይህ በፖለቲካ አመራሮች መካከል የተደረገ “የቃላት” ውርወራ በበታች ሹማምንት እና በተራው ዜጎች እንዴት ወደ ተግባር እንደሚተረጎም በቅርቡ እናየዋለን። ውጤቱ ንጹሐን ዜጎችን የሚጎዳ፣ የሁለቱን ክልሎችና ሕዝቦች ግንኙነት ለጊዜውም ቢሆን የሚያስተጓጉል፣ ባለው የአገሪቱ የጸጥታ ችግር ላይ ተጨማሪ ውስብስብ ደንቃራ የሚፈጥር መሆኑ አይቀርም።

በእነዚህ መግለጫዎች ማንኛው ወገን እውነት ተናገረ ወይም ተሳሳተ የሚለው የፖለቲካ ልሒቃን የቅንጦት ጉዳይ ነው። መዘዘኛው ነገር የመግለጫዎቹ ድምጸትና መልዕክት ነው። ከዚያ በተረፈ የመግለጫዎቹን ቃላት ከሁለት ቀናት በኋላ የሚያስታውሳቸው ጥቂት ሰው ነው።

የሁለቱም ድርጅቶች አመራሮች በዚህ የመግለጫ ጦርነት በመሳተፋቸው ታሪካዊ ሥሕተት ሠርተዋል። ቀዳሚው አጥፊ ህወሓት ነው። ጥፋቱም ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው። የቅርብ ጓዶቻቸው ሲገደሉ በዐይናቸው የተመለከቱ ገና ከኀዘን ስሜት ያልወጡ አመራሮችን፣ ግድያውና መዋቅራዊ መዘዙ ከፈጠረበት ድንጋጤ ለመውጣት የሚባትት ድርጅትን በዚህ ወቅት በዚህ መሰል ተንኳሽ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ መግለጫ መግፋትና መተንኮስ ፈጽሞ የተሳሳተ፣ የማይጠቅም አሳፋሪ ተግባር ነው። ከዚህ ድባብ ተነስተው ከተመለከቱት፣ የአዴፓ ምላሽ በድምጸቱም ሆነ በይዘቱ የሚጠበቅ ነበር።

አስቀድሜ እንዳልኩት፣ የየትኛው ድርጅት መግለጫ ብዙ ነጥብ አስቆጠረ የሚለው ጉዳይ ከአገር ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ብዙ የሚጠቅም አይመስለኝም። አሁንም ነገሩን በተከታታይ መግለጫና ምልልስ ከማካረር ይልቅ ማብረዱ ይሻላል።
ፓርቲና የመንግሥት መዋቅር ተደባለቀው በሚሠሩበት አገር፣ የሁለቱ ፓርቲዎች ፍትጊያ የመንግሥትን መዋቅር በእጅጉ ሊጎዳው እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ቢሮክራሲው እና ሌሎችም የመንግሥት አካላት (መከላከያውን እና ደኅንነቱን ጨምሮ) በአንጻራዊ ተቋማዊ ነጻነት የሚንቀሳቀሱ ቢሆኑ ኖሮ የፓርቲዎቹ ጠብ ባላሳሰበን ነበር።

ቢሰሙንም ባይሰሙንም፣ ቢደርሳቸውም ባይደርሳቸው፣ የአዴፓ እና የህወሓት አመራሮች ከዚህ በኋል አንዱ ስለሌላው መግለጫ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ማሳሰብ፣ መጎትጎት ያስፈልጋል። አጨብጫቢዎችና አዳማቂዎችም ተደርበው እንዳይጮኹ መገሰጽ ይገባል።
ጠቡን የሰፈር ጎረምሶች ድብድብ አናስመስለው። የቃላት ጦርነቱ በብዙ ችግሮች ተሰቅዛ ለተያዘች አገራችን ተጨማሪ ቁስል ሊፈጥር እንደሚችል እናስታውስ። ለግጭት ነጋዴዎች ገበያ አናቁምላቸው። አገር እንደ ኩሬ ውሃ “ካልደፈረሰ አይጠራም” በሚል መርህ አይያዝም። ውሃ ሲደፈርስ ውሃ አይሞትም፣ አገር ሲደፈርስ ሰው ይሞታል። ውሃ ደፍርሶ ይጠራል፤ አገር ደፍርሶም አይጠራም።
አገርስ አይደፍርስ! ድፍርሳችን መቼ ጠራ?!

========================
ቅድመ ሁኔታዎች እና ደንቦች ተፈጻሚ ይሆናሉ!!
ቅድመ ሁኔታው፤ ሐሳብና መረጃ ለመለዋወጥ መፍቀድ…
ደንቡ፤ ስድብና ከርዕሰ ጉዳይ ወጥቶ መዘባረቅ፣ የኀይል ጥቃትን ማበረታታ/መቅስቀስ ከመድረኩ ያስባርራል

1 COMMENT

  1. Yahulu tere-woyanie tgl ageritun adega ketachuhalna wegdu neber. Gn ahunm ageritu yebelete adega lay nat eyalen new. Amara yebase tqat eyetefetemebet new. Atchuhm eyetebale new. Ageritu yashaten tihun enji sqayachn enchohaln.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.