አማራ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማለት የለበትም (በገ/ክርስቶስ ዓባይ)

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓ/ም

የገደለው ባልሽ
የሞተው ወንድምሽ
ሐዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽም አልወጣ!

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በባህር ዳር የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ፤ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እጅግ በጣም ልብን የሚነካ ጉዳይ ነው። በተለይ ደግሞ ለአለፉት በርካታ ዓመታት በፈጠራ ትርክት፤ በዙሪያ መለስ ግፍ፤ እየተሰቃየ ለሚገኘው የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ጉዳት መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው። ይህም አልበቃ ብሎ  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ወንድማማች አማራዎችን ለመከፋፈል የተቀነባበረው ሴራ ጥሬ ሐቁ ወደፊት እስከሚታወቅ ድረስ፤ ድንገት በተፈጠረው ዱብ ዕዳ መነሻነት ግን የአማራን ሕዝብ በጎጥና በወንዝ በመከፋፈል ኃይሉን ለማዳከምና አንድነቱን ለመበተን ለሚሹ የጊዜው ፖለቲከኞች፤ ሠርግና ምላሽ እንዳይሆን በጥሞናና አርቆ በማስተዋል አማራው ቁጭቱንና ንዴቱን ውጦ፤ ሐዘኑን አምቆ በመያዝ፤ ተጨማሪ የወገን ኪሣራ እንዳይከሰት በልበ ሙሉነትና በቆራጥነት በመቆም የጀመረውን ህልውናውን የማስጠበቅ ትግል መቀጠል አለበት።

የአማራው መከፋፈልና ውድቀት ለነዶ/ር ዓቢይ ምናቸውም አይደለም፤ እየሠሩም ያሉት በዚህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር የተሠማሩ ቡድኖችን በመፍጠር ላይ ተጠምደው ነው። ለማስመሰል ብዙ ብዙ ሊያወሩ ይችላሉ። ሐቁ ግን ሌላ፤ እጅግ ሌላ ነው። በእርግጥ ጉዳት ካለ የተጎዳው አማራና አማራ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ሰበብ ትግሉ ለአንድ ሴኮንድ እንኳ ሊገታ እንደማይችል አማራው ከመቸውም በላይ በአንድነት በመቆም ማስረገጥ ይኖርበታል። ለዚህ ሁሉ ዋናው ችግር ለዘመናት ሲጋቱ በቆዩት መፍትሔ በሌለው የበታችነት ትርክት ባህር ውስጥ እራሳቸውን ከተው የሚዳክሩ አካላት ከማይመጥናቸው የአመራር ማማ ላይ በውጣታቸው ነው።

ዶ/ር ዓቢይ ትናንት የአሞገሰውንና የአከበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ትንኝ በመቁጠር እየቀለደበት ይገኛል። ይህም የበታችነት አንዱ መገለጫ የሥነ አእምሮ ጠበብት (Over Compensation) የሚሉት ዓይነት መሆኑን አማራው መገንዘብ ይኖርበታል። ባለሥልጣኑ ዓይኑን በጥሬጨው አጥቦ ከጠቅላይ ሚንስትር የማይጠበቅ ተግባር ላይ እየተሳተፈ ክብሩን በየጊዜው እያዋረደ መሆኑ የአዳባባይ ምስጢር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የማስመሰል ዲስኩሩና ድራማው ስለሰለቸው አንቅሮ ከተፋው ውሎ አድሯል።

የለገጣፎን ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀል እያወቀና መመሪያም እየሰጠ አላወቅሁም ብሎ የሚክድ፤ በጌድኦ ከብዙ መቶ ሺህ በላይ የሚደርሱ ወገኖቻችን በኦነግ አክራሪዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ እያወቀ ድምፅ ያላሰማ፤በተቀነባበረ ሁኔታ በኦሮሞ ክልል ከ18 በላይ ባንኮች በኦነግና በኦዴፓ ታጣቂዎች ትብብር ሲዘረፉ ትንፍሽ ያላለ፤ድሆች ከልጆቻቸው አፍ እየነጠቁና አንጀታቸውን አሥረው ገንዘብ እየከፈሉ ለረጅም ዓመታት ጠብቀው ያገኙትን የኮንዶምኒየም ቤት፤ በጃዋር መሐመድ አስተባባሪነት፤ በቄሮ መንጋ ገጀራ ያዥነት በመዲናዋ መሀል በአዲስ አበባ መንገዶች ሳይቀር እየፎከሩ ሲያስቆሙ ጭጭ ያለ፤ ‘አፉ ቅቤ ልቡ ጩቤ’ የሆነ አስመሳይ ከሀዲ፤ መናፈሻ እገነባለሁ በማለት በሕዝብ ይቀልዳል።

በአንፃሩም ተወካይ የሌለው የአዲስ አባባ ሕዝብ በየጊዜው እየደረሰበት ያለውን መፈናቀል፤ ሕገወጥ የመሬት ነጠቃና ቅርምት፤በሕግ የበላይነት ሥርዓት ለማስያዝና የተጠቂውን ሕዝብ ድምፅ ለማሰማት፤ የከተማይቱን ኅልውና በመካድ ያለአግባብ በኦሮሞ ክልል ሥር ለማካተት እየተሠራ ያለውን ሤራ ለማክሸፍና የነዋሪውን መብት ለማስጠበቅ፤  የዜግነት ድርሻውን ለመወጣት ቀን ከሌት እየለፋ ያለውን የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ባልደራስ እንቅስቃሴ፤ እንደመፈንቅለ መንግሥት የሚያይ፤ የሰብአዊ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለመገደብና ለማፈን የተለያዩ ተልካሻ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ መሆኑ ከባነነበት ውሎ አድሯል። በዚህ ሁሉ እንደ ሠንሰለት በተቆላለፈው የማያቋርጥ ማጭበርበር በመገረም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በትዝብት ማዕበል ውስጥ እየዋኘ እጅግ በጣም አፍሮበታል፤ንቆታል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማጭበርበር የተጠቀመበት አንዱና ዋነኛው ዘዴ ደግሞ፤ በሚሠሩት ሥራ በሕዝብ ዘንድ ታላቅ ከበሬታና ሞገስ የነበራቸውን ዕውቅ ሰዎች እንደ ዕብድ ውሻ ለካክፎ ከቀጥተኛው የአገርና የሕዝብ አለኝታነታቸው ማስወጣቱ ነው። እነዚህ ሰዎች ለጊዜውም ቢሆን በይሉኝታ ታፍነው ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንደሆኑ መገመት አይከብደም። ስለሆነም አንገታቸውን ደፍተዋል፤ጸሐፊዎች ብዕራቸው ነጥፏል፤ መንግሥት ከመጥፎ ሥራው እንዲታቀብ በዘዴ ሲተቹ የነበሩትም የገቡበት ጎሬ አይታወቅም፤ አንዳንዶችም በከፍተኛ ቁዘማ ውስጥ እንደሚገኙ የውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። አንዳንዶችም ከአፈርኩ አይመልሰኝ በማለት በዚሁ እኩይ አረንቋ ውስጥ ወድቀው ኅሊናቸው ጋር እየተሟገቱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሚናቸውን በማስተካከል ወደ ሕዝብ ወገኝተኝነታቸው እንደሚመለሱ የሚያጠራጥር አይሆንም። በተለይ አንዳንዶቹ ጠንቃቃ ቢሆኑም ደፋሮች ስለሆኑ የሕዝባቸውን ሥቃይ ከሚያዩ ሞትን እንደሚመርጡ ይታመናል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ያልተረዳው ጉዳይ፤ በሕዝብ ሚዛን አንዴ ከቀለሉ ደግሞ እንደገና ለመከበርና አመኔታን ለማግኘት በጣም በጣም ፈታኝ መሆኑን ነው። ስለሆነም ‘በዐልጋ ሲሏት በአመድ’ እንደተባለችው እንስሳ፤ ከነበረበት የክብር ኮረብታ በተራ ሸፍጥና ቅሌት በየጊዜው ቁልቁል እየተንደረደረ ይገኛል። ሕዝብ ክብር ሲሰጥ ያንን ሙጥኝ በማለት፤ ዶ/ር ዓቢይ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ጸንቶ መቆም ሲገባው ያንን በመርሳት ወይም በመካድ፤በየጊዜው በሚሠራው ሥራ ቀስ በቀስ እውነተኛው ባህርዩ ፍንትው ብሎ ሲወጣ፤ በግልጽ እየታየ ባለው ዕብሪትና ማንአለብኝነት ቁልቁል እየተንሸራተተ መሆኑን ሠፊው ሕዝብ እየተመለከተ፤ ደሙ እስኪፈላ ድረስ በከፍተኛ ቁጭትና ንዴት ሆኖ እየታዘበ ነው።

እዚህ ላይ ከታላቁ መጽሐፍ ታላቅ ምሳሌ እናገኛለን። የጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ልጅ ሮብአም በአባቱ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እሥራኤላውያን ‘ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ! አባትህ የግብር ቀንበር አክብዶብን ነበርና እባክህ አቅልልን እኛም እንገዛልሃለን በማለት አቤቱታ አቀረቡለት። ንጉሥ ሮብአምም ከሦስት ቀናት በኋላ ተመለሱ እኔም አሳውቃችኋለሁ ሲል አሰናበታቸው። ከዚያም በአባቱ ዘመን የነበሩ ባለሟሎችን በዕድሜም ሆነ በልምድ እጅግ በጣም የተከበሩትን መኳንቶች አማከራቸው።

እነርሱም፤ ‘ንጉሥ ሆይ! ሕዝቡ የጠየቁህን ልመና ተቀብለህ ሸክማቸውን ብታቀልላቸው፤ ቸርነትህንም ብታሳያቸው፤ እነርሱም ሰጥ ለጥ ብለው እንደ ባሪያ ይገዙልሃል’ ሲሉ መከሩት። ከዚያም ደግሞ ዘወር አለና በዕድሜ እንደሱ ያሉ ወጣቶችንና ብላቴናዎችን ደግሞ እንዲሁ ምክር ጠየቃቸው።

በዚህ ጊዜ ‘ትንሿ ጣቴ  ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች! አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ እጨምርባችኋለሁ፤አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ’ በላቸው በማለት የበኩላቸውን መከሩት።

የእሥራኤል ሽማግሌዎችም በቀጠሯቸው መሠረት በተመለሱ ጊዜ ንጉሥ ሮብአምም የመኳንንቶችን ምክር ሳይሆን የወጣቶችን ምክር በመቀበል ይህንኑ ነገራቸው። የእሥራኤል ሽማግሌዎችም ድሮም ከዳዊት ወገን ምን ክፍል አለን? በእሴይ ዘንድስ ምን እርስት አለን? በማለት ንዴትና ሐዘን በተቀላቀለበት ሁኔታ ተመልሰው ሔዱ። በኋላም በግዛቱ ሁሉ አመጽ ተነሳበት፤ዕድሜውም አጭር ሆነ። ዜና መዋዕል ካልዕ ም.10.

ዶ/ር ዓቢይም የታላላቅ ሰዎችን ምክር አልቀበልም በማለት ሕዝብ የማይወደውንና የሚጠየፈውን የጃዋር መሐመድና የዳውድ ኢብሳን ምክር እየተቀበለ የእነርሱን አጀንዳ ለማስፈጸም በመሯሯጥ ላይ ተጠምዷል። ይህ አካሄድ ለዶ/ር ዓቢይም ሆነ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚጠቅም እንዳልሆነ ይታወቃል። ተወደደም ተጠላም የጠቅላይ ሚንስትሩ እያንዳንዷ ውሳኔና እንቅስቃሴ እስከ ወዲያኛው በታሪክ መዝገብ ስለሚጻፍ ቢያንስ ለልጆቹና ለቤተሰቦቹ ማሰብ እንዳለበት ግልጽ እንደሆነ ይገመታል። ነገር ግን ‘ፖለቲካ አእምሮን ያውራልና’ በሥልጣን ስካር ላይ ሆኖ እንዲህ ያለው የጥሞና አስተሳሰብ ሊመነጭለት አልቻለም። ሌላው ቀርቶ ሰው ሸክላ መሆኑን እስከ መርሳት ደርሷል። በባህር ዳር ያለጊዜያቸው በድንገት ለኅልፈተ ሕይወት የተዳረጉት የትግል አጋሮቹ መች እንደሚሞቱ ቢያውቁ ኖሮ ምናልባት ያችን ወቅት ለማሳለፍ እራሳቸውን ከቦታው ይሰውሩ ነበር፤ ግን ባለመወቃቸው እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ቤተሰባቸውን ጭምር ጎድተዋል።

ሕዝብ ሊያወርደው የማይችለውን አምባገነን መሪ እግዚአብሔር እንደተቆረጠ ቅጠል ከመቅጽበት ሊያጠወልገው እንደሚችል ለአፍታም መዘንጋት የለብንም። ይህንንም በዘመናችን በተደጋጋሚ የአየን ሕያው ምስክሮች ነን። ዶ/ር ዓቢይ ሕዝብን ሲያታልል እግዚአብሔርን እያታለለ መሆኑን የተረዳ አይመስልም፤ ምክንያቱም አስመሳይነት እንጂ ፈጽሞ እምነት እንደሌለው ያለጥርጥር በዚህ ያስታውቃል። እምነት ያለው ሰው አይዋሽም፤ ዶ/ር ዓቢይ ግን በአንደበቱ ማር እያዘናመ በተግባር ግን እንደ እባብ ይናደፋል።

ሟቹ ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሥልጣኑን ጠቅልሎ በያዘ ጊዜ ለዓመታት አብሮት ሲታግል የነበረውን ታምራት ላይኔን፤ስየ አብርሃን፤ ቢተው በላይን እና ሌሎችንም ሰበብ እየፈጠረና ቀን እየጠበቀ በየተራ እሥር ቤት፤ ከተታቸው፤ ብዙዎችን ደግሞ ከሥራ በማባረር ሲያሠቃይ ነበር። አቦይ ስብሐትንም ከሥልጣን በማውረድ ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸው ይነገራል። የደኅንነት ሹም የነበረውን ክንፈን እና ኃየሎም አርአያን በረቀቀ ሴራ ከማስገደል ጀምሮ ብዙ ብዙ በሕዝብ ዘንድ በግልጽ የማይታወቁ ወንጀሎችን ሲፈጽም፤ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ለእሱ ብቻ የተሰጠች አንጡራ ሀብቱ አድርጎ በማየት ለዘለዓለም የሚኖር መስሎት ነበር።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ አዋዲ (ፍትሐ ነገስት) የሚያዘውን ሕግ በመተላለፍ ፓትርያርኩን አቡነ መርቆሪዎስን ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት ትውፊት ውጭ በግፍ ወደ ባዕድ አገር በማሰደድ፤ በምትካቸው በቅድስት ማርያም መንበር ላይ የተቀመጡት አባ ጳውሎስ እንዲሁ ሞታቸውን ዘንግተው፤ዘለዓለማዊ እንደሆኑ በመቁጠር አንዱን ሲሾሙ ሌላውን በግፍ ሲያባርሩ እንደነበርም አይዘነጋም። ነገር ግን የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ ኃያሉ አምላካችን ለእኛ ለቋሚዎች መቀጣጫ ይሆኑ ዘንድና ወደፊትም ሕዝብ እንዳይበደል፤ፍርድ እንዳይገመደል፤በአጭር ቀናት ውስጥ በተመሳሳይ ወቅት በሚያስደነግጥ ሁኔታ በድንገት ሲቀሠፉ አይተናል።

ዶ/ር ዓቢይ ምንም እንኳ ለጠቅላይ ሚንስትርነት የሚያበቃ ልምድም ሆነ የዕድሜ ተሞክሮ ባይኖረውም የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ለዚህ ማዕረግ ሲበቃ ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ወደ ጎጥ አዘንብሏል። ለጊዜው ቢመስለውም ይህ አካሄድ የሚያዋጣው አይደለም። ብዙዎች አገር ወዳድ ሰዎች በሕይወታቸው የሚመኙት ታላቅ ነገር፤ ሕዝባቸውን ያለ አድልዎ በማስተዳደር ሌሎች የዓለም አገሮች ከደረሱበት የዕድገትና ብልጽግና ደረጃ ማስተካከል እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ይሁን እንጂ ምኞታቸው እውን የሚሆንላቸው በቁጥር እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። እንግዲህ ዶ/ር ዓቢይ እንዲህ ያለውን ታላቅ ዕድል አግኝቶ፤መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚባል ደረጃ ድጋፉን ሰጥቶት እያለ ለተጣለበት ኃላፊነት የማይመጥን፤ የክኅደት አካሄድ ለምን አስመረጠው? ጃዋርም ሆነ ዳውድ ኢብሣ የእርሱን ታሪክ ሊሸፍኑለት አይችሉምና በሚገባ ማሰብና ማሰላሰል በተገባው ነበር።

ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል የነበረው ቅንነትና ትህትና የተሞላበት አነጋገር እንደ ጭምብል ውልቅ ብሎ ወድቆ፤ አምባገነኖች እንደሚያደርጉት በንዴትና በዕብሪት መናገርም ጀምሯል። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ እንኳን በቋፍ ሆነው በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከቱትን ይቅርና ሐቀኛ ደጋፊዎችንም አንገት የሚያስደፋና የሚያሸሽ ስለሚሆን ሳይርቅ በቅርቡ፤ ሳይደርቅ በእርጥቡ፤ እንዲሉ አሁኑኑ ማስተካከል ይገባዋል።

በተለይ አነጋጋሪ ስለሆነው ሕገ መንግሥት፤ ጠበቃ ነኝ ብሎ ከተገቢው በላይ መከራከር የሚያዛልቅ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ለአለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲታገልለት የኖረው አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ‘ሕገ መንግሥቱ አልጠቀመንምና ይሻሻል!’ የሚል እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል። ዶ/ር ዓቢይ ለዚህ ሥልጣን የበቃውም በዚሁ በሕገ መንግሥት ምክንያት የተነሳው አመጽ በየዕለቱ እያደገና እየጠነከረ በመምጣቱ እንደሆነ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አልነበረበትም።

እርሱ ግን ከሕዝብ በተቃራኒ ተሰልፎ ይህንን አቋም መያዝ ብቻ ሳይሆን፤ ‘ለአንድ ክልል ብቻ ሲባል ሕገ መንግሥቱ አይቀየርም’ በማለት የአማራውን መብት ለማስከበር በግልጽ እንሟገታለን ያሉ ቆራጥ መሪዎቹን በአንድ ጀንበር ማጥፋቱን አረጋግጧል። ይህንንም የሴራ ፖለቲካ ለማዳፈን እየተሄደበት ያለው መንገድ መላውን አማራ እና ሠፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አስቆጥቷል።

ለማንኛውም የቆራጣ ካርታ ሃውልት አምቦ ላይ፤በተፈበረከ ታሪክ የሐሰት ሐውልት አርሲ ላይ አቁሞ በየትኛውም መለኪያ መሪያችሁ ነኝ ለማለት የሚያስችል የሞራል ልዕልና ስለሌለው ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እያንዳንዷን ውሳኔና እንቅስቃሴ በትኩረት ሊከታተል ይገባል። በተለይ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የሥርዓቱ ሰለባ የሆነው አማራ አራት ዓይና በመሆን እየተናበበ መታገል አለበት።

የአማራ አክቲቢስቶች እርስ በእርሳችሁ የጎንዮሽ ጉንተላዎችን በማቆም አቅጣጫችሁን በጋራ ጠላታችሁ ላይ ማድረግ እንደሚጠበቅባችሁ መገንዘብ ይኖርባችኋል። ችግር ካለ በውስጥ መስመር ተወያይታችሁ መፍታት ሲገባችሁ ወደአደባባይ በማውጣት ለጠላት ምቹ በር መክፈት የለባችሁም። ሲጀመር፤ እንዲህ ያለው ክፍተት የሚመነጨው በአማራ ስም ሠርገው በሚገቡ የጠላት ሠራዊት እንደሆነ መረዳት ብልኅነት መሆኑን መጠቆም አስፈላጊ ይሆናል።

‘በማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ’ እንዲሉ አሁን ላለበት የሥልጣን ኮርቻ ላይ እንዲፈናጠጥ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች ዋነኛው የሕገ መንግሥቱ መሻሻል አስፈላጊነት ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገፍቶ የመጣ ጥያቄ በመሆኑ ነበር። ነገር ግን ‘ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ’ እንዲሉ በታሪክ አጋጣሚ በኢሃዴግ ውስጥ በተፈጠረ ክፍተት ለዚህ ደረጃ የበቃ ቢሆንም በየትኛውም መመዘኛ ከእርሱ በላይ ችሎታና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን የሉም ማለት እንዳልሆነ ማወቅ ተገቢ ነው።

መጀመሪያም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፉን ሲቸረው ዶ/ር ዓቢይ ማን እንደሆነ ጠፍቶት አይደለም፤ ለነበረው የወያኔ ሥርዓት ዋና አገልጋይ በመሆን ብዙ ብዙ ወንጀሎችን ሲፈጽም የኖረ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ግን ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! በማለት በጠቅላይ ሚንስትርነት በዓለ ሹመቱ ላይ ለፓርላማ  እንደገለጸው የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ የሞከረ በመሆኑ እስኪ ጊዜ ሰጥተን እንየው በማለት ሚዛን ላይ አስቀመጠው። ሆኖም ብዙ ጊዜ ሳይቆይ በተግባር በየጊዜው እየቀለለ ተገኝቷል።

ሰውን መሸንገልም ሆነ ማታለል ቀላል ነው። እግዚአብሔርን ግን ማታለል ፈጽሞ አይቻልምና ዶ/ር ዓቢይ ረጋ ብሎ ቢያስብ መልካም ነው። ጸሐፊው እንደሚረዳው ከሆነ ለስሙ የሚጨነቅ ሰው እንዳልሆነ የሚያሳብቀው ደግሞ፤ የሚናገረውና የሚተገብረው ጉዳይ አራቦና ቆቦ መሆናቸው ነው። የዶ/ር ዓቢይ ታሪክ እንዴት እንደሚጻፍ ከአሁኑ ቢያስብበት መልካም ነበር፤ ቢያንስ ትውልድ ቀጣይ ስለሆነ ለልጆቹ ሲል። የእነጃዋር ምክር እንኳን ከሕዝብ ከፈጣሪም የሚያጣላ ነውና አማካሪዎቹን በጥንቃቄ መምረጥ አለበት የሚል ምክር መሠንዘር ተገቢ ይሆናል።

ስለሆነም አማራው ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! እያለ በልበ ሙሉነት ከአስተሳሰብ ልዕልና ላይ ላለመውረድ ሲፍጨረጨር፤ ሌሎች በጣም በወረድውና በተናቀው አስተሳሰብ በዘር ሲደራጁ፤ በንቀት ችላ ሲል ቆይቶ ኅልውናው አደጋ ላይ ሲወድቅ በመባነኑ በመጨረሻዋ ሰዓት ቢሆንም መደራጀት በመጀመሩ፤ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላው ሁሉም የዘውግ ድርጅቶች የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸው በመሆናቸው፤ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ገብተው መንቀጥቀጥ ጀምረዋል። ከዚህም ፍርሃት የተነሳ አማራውን አመራር ለማሳጣት እጅግ በጣም በረቀቀ ዘዴ በርካታ መሪዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ መስዋዕት እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህ ማለት ትግሉን ለማዳከምና ለማዳፈን ታቅዶ የተደረገ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ አማራው ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ መልኩ ትግሉን ማፋፋም ይጠበቅበታል።

በመጨረሻዋ ቀን በዚያች ዕለት፤ በሠገነት ያለ ወደ ታች አይውረድ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ ይሆናል፤ ያችን ቀን ግን ማንም አያውቃትም፤ ማቴዎስ 24 ይህ አባባል ለዓለም ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ሰው ዕለተ ሞት የተጠቀሰ መሆኑን ማጤን ይገባል።

አማራ መንፈስ ነው እንኳን መሣሪያ ታጥቆ ብዕርና ወረቀት መያዙ ከታወቀ ጠላቶቹ ሁሉ ይርዳሉ። አማራ! የኢትዮጵያ ቃል ኪዳን የሠረጸው፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ሕዝብም ስለሆነ በጸሎቱ ብቻ ጣላቶቹን እንደ ጉም ያተናል፤ እንደጢስም ያበናቸዋል። እንግዲህ አማራው በአራቱም ማዕዘን እየተሠነዘረብህ ያለውን ጥቃት ለመከላከል ሁሉም እንደየስጦታውና እንደ አቅሙ በጾም፤ በጸሎት፤ በፖለቲካውም ሆነ በነፍጥ ሁለገብ ትግልህን አፋፍም። ጸሎቱ “ፈጣሪ አምላክ ሆይ! አንተን የሚፈራ ለሕዝብህ የሚራራ፤ ሐቀኛ መሪ ስጠን!” የሚል መሆን አለበት። ለመሆኑ ዶ/ር ዓቢይ ስንት ዓመት በሕይወት ትኖራለህ?  ማስተዋሉን ይስጥህ!

3 COMMENTS

  1. የአማራ ጥያቄ ሕገመንግሥት ያልተሳተፍኩበት ስለሆነ አይመለከተኝም ነው:: አንድን ብሔር ነጥሎ ባይታወር ባደረገ ሕገ መንግሥት ተዳኝ ማለት አምባገነንነትን እንጂ ዲሞክራሲያዊነትን አይገልጽም:: ለአንድ ክልል ተብሎ ሕገ መንግሥት አይለወጥም የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር አግላይ ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ነው ብሎ አማራው ይጠራኛል ብሎ እያሰበ ከሆነ በብዙ ረገድ ስቷል:: አማራው በከለላችሁለት ክልል ብቻውን ቁጥሩ የትየለሌ ነው:: አማራው በየክልል ቁጥሩ በጣም ብዙ ነው:: ከዚህም በላይ አማራ ከሁሉም ብሔር ጋር የተዳቀለ ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ቁጥሩ በኢትዮጵያ ስፍር ቁጥር የለውም ወይም ኢትዮጵያ ነው:: ዛሬ አማራ በዓለም ዘሩ እንደጎመን ዘር ተበትኖ ለአሜሪካን መንግሥት ምርጫ ሳይቀር ወሳኝ ድምጽ ለመሆን የበቃ ዘር ነው:: የአማራን ቁጥር ያሳነሳችሁ መስሏችሁ በፈጠራችሁት ክልል ልትወስኑት ቢዳዳችሁም የአማራ ኃይማኖቱና ማተቡ ከብዙው ኢትዮያዊ ወንድሙና እህቱ ጋር ያጋመደውና ያቆራኘው ስለሆነ አማራን አጠቃለሁ የምትል ስሁት ሁላ ጠላትህ በጉያህ መሆኑን እወቀው:: አማራ መንፈስ ነው የሚባለው ለዚህ ነው::

  2. ጹሁፍህ ለሆነ ብሄር ያደላ እንደሆነ ያስታውቅብሃል ስልጣንም ፈላጊ እንደሆንክ ያስታውቅብሃል ዶ/ር አብይን የመተቸት መብት ቢኖርህም ይህን ያህል ትችት ይገባዋል ብዬ አላምንም ሌላው ደግሞ ስለ ጁሃር ስለ ቄሮ ብዙ አውርተህ ስለ ፋኖ የግንቦት 7 አመራሮች ላይ ያደረጉትን አላማውራትህ ትክክለኛ ማንነትህን አጋልጦብሃል ለማንኛውም እይታህ ሁሉ ዶ/ር አብይ ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ እይታህ ተንሸዋራል ትችትህ ብዙ አይነስጥም

  3. ጹሁፍህ ለሆነ ብሄር ያደላ እንደሆነ ያስታውቅብሃል ስልጣንም ፈላጊ እንደሆንክ ያስታውቅብሃል ዶ/ር አብይን የመተቸት መብት ቢኖርህም ይህን ያህል ትችት ይገባዋል ብዬ አላምንም ሌላው ደግሞ ስለ ጁሃር ስለ ቄሮ ብዙ አውርተህ ስለ ፋኖ የግንቦት 7 አመራሮች ላይ ያደረጉትን አላማውራትህ ትክክለኛ ማንነትህን አጋልጦብሃል ለማንኛውም እይታህ ሁሉ ዶ/ር አብይ ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ እይታህ ተንሸዋራል ትችትህ ብዙ አይመስጥም ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.